ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማሊ፡ በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት የማሊ ፕሬዚዳንት ለህክምና ወደ አቡዳቢ ሄዱ
ከባለፈው ወር በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተወገዱት የማሊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ታመው ለህክምና ወደ አቡዳቢ ሄደዋል።
የ75 አመቱ ፕሬዚዳንት በደም ዝውውር መታወክ (ስትሮክ) ታመው በትናትንትናው ዕለት ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መዲና አቡዳቢ ማቅናታቸውን የአገሪቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ስልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ወደ ሲቪል አስተዳደር የሚደረገው ሽግግር ላይ ውይይት እያደረጉ ይገኛል።
ወታደራዊ ኃይሉ ከሁለት አመት በኋላ ስልጣን እለቃለሁ ቢልም የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ከዚያ ቀደም ብሎ የስልጣን ርክክብ ማድረጉ ያስፈልጋል እያሉ ነው።
ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈባቸውን የተቃውሞ ሰልፎች መርተዋል።
በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ህግን በተመለከተ ተቃውሞን ከማሰማት ባለፈ የሁሉም መሰረታዊ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ በመፈንቅለ መንግሥት ወርደዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች ሲያወግዙት የአፍሪካ ህብረት ደግሞ ከአባልነት አግዷታል።
በርካታ ማሊያውያንን ደግሞ አስደስቷል፤ ጮቤ የረገጡ ማሊያውያን በየጎዳናው በመውጣት ደስታቸውንም ገልፀዋል።
ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ለተወሰነ ጊዜያትም በወታደራዊ ኃይሉ ቁጥጥር ስር የነበሩ ቢሆንም በኋላ ግን ነፃ ወጥተዋል።
በዚህ ሳምንት ሃሙስ በደም ዝውውር መታወክ ለሁለት ቀናት ያህል በመዲናዋ ባማኮ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው ለበለጠ ህክምና ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ማቅናታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምም ለ15 ቀናት ያህል ይቆያሉ ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ወደ አቡዳቢ ሊሄዱ የቻሉትም ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ተወካዮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ከመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑንም የምዕራብ አፍሪካ ዘጋቢ ሴይዲና አሊዎኔ ድጂጎ ዘግባለች።
በአመራራቸው ላይ ወንጀል ፈፅመዋል ተብሎ ወደ ፍርድ የሚቀርቡም ከሆነ ፕሬዚዳንቱ እንደሚመለሱም ኢኮዋስ ከወታደራዊው ኃይል ጋር መነጋገሩንም ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።
ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በ1960ዎቹ ነፃነቷን በተቀዳጀችው ማሊ በነዚህ አመታተትም አራት ያህል መፈንቅለ መንግሥቶች ተካሂደዋል
ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያላት ማሊ ግዛቷ የሰሃራ በረሃንም የተወሰነ የሚሸፍን ሲሆን የፈረንሳይ ወታደሮችን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች አክራሪ ፅንፈኝነትን እንዋጋለን በሚልም ሰራዊት አስፍረውባታል።
ወታደራዊው ኃይልም እነዚህን ኃይሎች ለመዋጋት አለም አቀፍ ስምምነቱን እንደሚያከብር ቃል ገብቷል።