ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማሊ፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ማሊያውያንን ሲያስደስት ጎረቤት አገራትን አስቆጥቷል
በዚህ ሳምንት የተደረገው የማሊ መፈንቅለ መንግሥት በርካታ ማሊያውያንን አስደስቷል፤ ጮቤ የረገጡ ማሊያውያን በየጎዳናው በመውጣት ደስታቸውንም በመግለፅ ላይ ናቸው።
ነገር ግን በመፈንቅለ መንግሥቱ ደስተኛ ያልሆኑት በርካቶች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች ሲያወግዙት የአፍሪካ ህብረት ደግሞ ከአባልነት አግዷታል።
ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያላት ማሊ ግዛቷ የሰሃራ በረሃንም የተወሰነ የሚሸፍን ሲሆን የፈረንሳይ ወታደሮችን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች አክራሪ ፅንፈኝነትን እንዋጋለን በሚልም ሰራዊት አስፍረውባታል።
የወታደራዊው ኃይል ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታን ጨምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦቡዎ ሲሴ፣ የብሔራዊ ጉባኤ ቃል አቀባይ የሆነው የፕሬዚዳንቱ ልጅ፣ የውጭ ጉዳይና የገንዘብ ሚኒስትሮችም በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ፕሬዚዳንቱን በግዞት ወደ ውጭ አገርም ለመላክ አንዳንድ ድርድሮች እንደተጀመሩ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
ማሊ አባል የሆነችበትና አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በበኩሉ ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያን አስተላልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ አገራት ድንበሮቻቸውን እንዲዘጉ አድርጓል፤ ማንኛውንም የገንዘብ እንቅስቃሴም የገደበ ሲሆን ከማህበረሰቡም የውሳኔ ሰጭነት ቦታ እንድትገለል ወስኗል።
መፈንቅለ መንግሥቱንም ተከትሎ የ75 አመቱ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ከስልጣን መልቀቃቸውንም አጠር ባለው የቴሌቪዥን መግለጫቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን መግለጫ የሰጡትም ከመዲናዋ ባማኮ 15 ኪሎ ሜትር ራቅ ብላ በምትገኘው ካቲ የጦር ሰፈር ሲሆን በዚያኑ እለትም ነው በወታደራዊው ኃይል ወደ ስፍራው የተወሰዱት።
ለባለፉት ሁለት ወራት ያህል የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ህዝብ የተሳተፈባቸውን የተቃውሞ ሰልፎች መርተዋል።
በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ሙስና፣ የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ህግን በተመለከተ ተቃውሞን ከማሰማት ባለፈ የሁሉም መሰረታዊ ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ነበር።
እነዚህን የተቃውሞ ሰልፎች በዋነኝነት ሲያስተባብሩ የነበሩት ኢማም ማህሙድ ዲኮም ነበሩ። ኢኮዋስ በአሸማጋይነትም በመግባት ህዝቡ የሚጠይቃቸውን ማሻሻያዎች ፕሬዚዳንቱ ተግባራዊ እንዲያደርጉም ሞክሯል።
በዚህም ሁኔታ እያለ ነው የወታደራዊውን ኃይል የሚመሩ ኮሎኔሎችና ጄኔራሎች ተሰባስበው የፕሬዚዳንቱን ስልጣን ለማሳጠር የወሰኑት።
ሆኖም ኢ-ህገ መንግሥታዊ በሆነ ሁኔታ የስልጣን መገርሰስን ኢኮዋስ አይቀበለውም። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን መፈንቅለ መንግሥቱን ከመሩት ወታደሮች ጋር ለመወያየትም ወደ ባማኮ ከሰሞኑ ያመራሉ ተብሏል። ውይይታቸውም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልም እየተነገረ ነው።
ሆኖም ማሊያውያን በተለይም በደቡብና ማዕከላዊ ማሊ የሚኖሩ ማሊያውያን የፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መውረድ አስፈንድቋል። አስተዳደራቸው በርካታ የሙስና ቅሌቶችን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን የመስረተ ልማቶች ችግር ብዙዎችን አስመርሯል። በተለይም አርሶ አደሮች የማዳበሪያ እጥረት ማጋጠሙ ቀውስን አስከትሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ሰራዊት ፅንፈኛ አክራሪዎች ጋር በሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሚከፈላቸው ክፍያ ትንሽ መሆኑ ቁጣን ፈጥሯል።
በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት የወጡ መመሪያዎች የበርካታ ማሊያውያንን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ በከተተበት ወቅት የፕሬዚዳንቱ ልጅና የፓርላማው መከላከያ ኮሚቴ ሊቀመንበር ካሪም ኬይታ በቅንጡ መርከብ ሲዝናና የሚያሳይ ፎቶ መውጣቱ ብዙዎችን አበሳጭቷል።
ፎቶው የአሁንም ይሁን የቀድሞ ካሪም ኬይታ የህዝብን ገንዘብ አልተጠቀምኩም ቢልም በበርካቶች መሬት ላይ ካለው እውነታን የማይገባውና አገሪቷ ያለችበትን ቀውስ ያልተረዳ ነው በሚልም ውግዘት ደርሶበታል።