ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማሊ፡ተመድን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች የማሊን መፈንቅለ መንግሥት አወገዙ
በዚህ ሳምንት በማሊ የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አገራት እያወገዙት ይገኛሉ።
መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ከስልጣናቸው እንዲለቁ ተገደዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትና የቀጠናው ድርጅቶች በወታደራዊው ሃይል በቁጥጥር ስር ያሉት ፕሬዚዳንቱ እንዲለቀቁና ህገ መንግሥታዊው ስርዓት መስፈን እንዳለበት ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።
ወታደሮቹ በበኩላቸው አገሪቷ የባሰ ጦስና ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ለመከላከልም ነው እያሉ ይገኛሉ። የሲቪል አስተዳደር በቅርቡም እንደሚመሰርቱና አዲስ ምርጫም እንደሚካሄድ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያላት ማሊ ግዛቷ የሰሃራ በረሃንም የተወሰነ የሚሸፍን ሲሆን በተደጋጋሚም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶችን አስተናግዳለች። በአሁኑም ወቅት አገሪቷ የአክራሪ ፅንፈኞች ጥቃትና የብሄር ግጭቶችንም ለማረጋጋት እየጣረች ትገኛለች።
ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬታ ከሁለት አመት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫን አሸንፈው በስልጣን ላይ ይገኛሉ።
ነገር ግን ከጥቂት ወራት በፊት በሃገሪቱ ውስጥ ባለው ሙስና፣ የምጣኔ ኃብት ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍልና አወዛጋቢ የምርጫ ህግን በተመለከተ በርካቶች ተቃውሟቸውን በጎዳናዎች እያሰሙ ይገኛሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ሰራዊት ፅንፈኛ አክራሪዎች ጋር በሚያደርገው እልህ አስጨራሺ ትግል የሚከፈላቸው ክፍያ ትንሽ መሆኑ ቁጣን ፈጥሯል።
መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ ማሊ ከአፍሪካ ህብረት አባልነቷ ታግዳለች። "ይህ ያረጀ ያፈጀ ነው ተቀባይነት የለውም" ብሏል
"ምንም አይነት ቀውስ በአገሪቷ ውስጥ ሲፈጠር የህዝቡን ፈቃድ ለመፈፀም ነው በሚል ወታደራዊ መፈቅለ መንግሥቶች ይካሄዳሉ። እንዲህ አይነት ምላሽ ተቀባይነት የለውም" በማለት የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ኮሚሸነር ስማይል ቸርጉ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም ተናግረዋል።
አስራ አምስት አባላት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በበኩሉ መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም አገራት ድንበሮቻቸውን እንዲዘጉ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ማንኛውንም የገንዘብ እንቅስቃሴም የገደበ ሲሆን ከማህበረሰቡም የውሳኔ ሰጭነት ቦታ እንድትገለል ወስኗል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ በትዊተር ገፃቸው አውግዘውታል። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ጠይቀው "ሽብርተኝነትን መዋጋትና ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት የማይነጣጠሉ ናቸው" ብለዋል።