"ሰንደቅ አላማችንን ነፃ ለማውጣት እንታገላለን" የአውስትራሊያ ቀደምት ህዝቦች

የአቦርጂን ሰንደቅ አላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአቦርጂን ሰንደቅ አላማ

ጥቁር፣ ቀይ ፣ ነጭ የአውስትራሊያ ቀደምት ህዝቦች (አቦርጂን) ሰንደቅ አላማ ነው።

ጥቁሩ፣ ህዝብን፤ ቀዩ ከመሬት ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲሁም ቢጫው የአለም ማዕከል የሆነችውን ፀሃይን የሚወክል ነው።

አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት መሬታቸውን ነጥቀው በርካታ ቀደምት ህዝቦችን ጨፍጭፈዋል፤ በርካቶችም በአገራቸው እንደ ባርያና ሁለተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ ሆነዋል።

ለዚያም ነው የቅኝ ግዛት፣ ወረራና "ህዝባችንን የጨፈጨፈ" ስርአት ተምሳሌት የሆነውን የአውስትራሊያን ሰንደቅ አላማ አይወክለንም የሚሉት።

ይሄ ሰንደቅ አላማ በአውስትራሊያ በሚገኙ ድልድዮች፣ ህንፃዎችና በቲሸርቶችም ላይ ማየት የተለመደ ነው።

ሰንደቅ አላማው በመጀመሪያ የተቃውሞ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን የአቦርጂን ህዝቦች መለያና በአገሪቱም ብሄራዊ ሰንደቅ አላማነት እውቅና ተሰጥቶታል።

እናም በባለፈው አመት ይህንን ሰንደቅ አላማ መጠቀምም ሆነ መያዝ እንዲያቆሙ ሲነገራቸው አብዛኛዎቹን የአቦርጂን ህዝብ ግራ ያጋባው። በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው ሰንደቅ አላማው ከቅጅና ተዛማች መብቶች ጋር ተያይዞ እክል እንደገጠመው የተረዱት።

ሁኔታው በርካታዎችን አስከፍቷል፣ አስቆጥቷል። የቀደምት ህዝቦችን ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት የሆኑት ሊንዳ በርኔ ሰንደቅ አላማውን እጃቸው ላይ ተነቅሰውታል። እናም ሰንደቅ አላማውም ሆነ ምልክቱ "ታግቷል" ብለዋል።

በከፍተኛ ሁኔታ ጫና የደረሰበት የአውስትራሊያ መንግሥትም የቅጅና ባለቤት መብቱን ሊቆጣጠር ቢፈልግም ህጋዊና ባህላዊ ችግሮች ገጥመውታል ተብሏል።

ይህ እንዴት ተፈጠረ?

ከበርካቶቹ ብሄራዊ ሰንደቅ አላማዎች ለየት ባለ ሁኔታ ይህ ሰንደቅ አላማ ባለቤትነቱ የመንግሥት አይደለም።

ባለቤትነቱ ሃሮርልድ ቶማስ የተባለ አርቲስት ነው። ይህ የአቦርጂን አርቲስት ሰንደቅ አላማውን ዲዛይን ያደረገው በጎርጎሳውያኑ 1971 በነበረው የትግል እንቅስቃሴ ነው።

አርቲስቱ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ባለሙሉ መብት ነው፤ ይህንንም መብቱን ያረጋገጠው በ90ዎቹ በተደረገ የፍርድ ሂደት ነው። ከዚያም በኋላ በባለፉት አመታት ለተለያዩ ኩባንያዎች እንደገና እንዲያመርቱም ስምምነት ላይ ደርሷል።

ከሁለት አመታት በፊት ዋም ከተባለ የልብስ አምራች ጋር አንድ ስምምነት ተፈራርመው ነበር። በዚህም ስምምነት መሰረት ኩባንያው ሰንደቅ አላማውን በልብሶች እንዲያትም፣ በተለያዩ ሚዲያዎችም ላይ እንዲጠቀም አለም አቀፍ ብቸኛ መብትም የሰጠ ነው።

የአቦርጂን ሰንደቅ አላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአቦርጂን ሰንደቅ አላማ

ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ኩባንያዎች ሳይሆን ይሔኛው ኩባንያው ይህንን ስምምነትም ለማስከበር በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሷል።

በርካታ ለትርፍ ያልቆሙ የአቦርጂን ድርጅቶችም ይህንን የተረዱት ኩባንያው ህጋዊ መፍትሄንም ጭምር በመጠቀሙ ነው።

"ሰንደቅ አላማውን የያዙ ልብሶች ሽያጭ በሶስት ቀናት ውስጥ እንዳቆም የፍርድ ቤት ማስቆሚያ ወረቀት የያዙ ጠበቆች ነገሩኝ" በማለትም የጉንዲትጅማራዋ ላውራ ቶምሰን ትናገራለች።

የአቦርጂን ሰንደቅ አላማ ያለባቸውን ቲሸርቶችን በመሸጥም ለህዝቡ የህክምና አገልግሎት እንዲውል የሚሰራ ድርጅትንም ትመራለች።

በዚህ ህጋዊ ማስፈራሪያ የተቆጣችው ላውራ "ሰንደቅ አላማውን ነፃ እናውጣ" የሚል ዘመቻን ጀምራለች። በበይነ መረብም 150 ሺህ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ችላለች። ይህም በባለፈው አመት ለፓርላማው ቀርቦ ነበር።

"አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት ሰንደቅ አላማው እንዴት የግሌ ነው ይላል? ሰንደቅ አላማው የአቦርጂን ህዝቦች ነው። የራሳቸውን ሰንደቅ አላማ ለመጠቀምስ ለምን ይከፍላሉ?" በማለት በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።

"የህዝባችን የፅናት ምልክት ነው። የአውስትራሊያ ሰንደቅ አላማ የኛ ነው ብለን አናስብም ምክንያቱም የቅኝ ግዛት፣ የወረራና የግድያ ምልክት ነው ብለን ስለምናምን አይወክለንም" ብላለች።

ሰንደቅ አላማውን ነፃ የማውጣት ዘመቻ የጀመረችው ላውራ ቶምፕሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሰንደቅ አላማውን ነፃ የማውጣት ዘመቻ የጀመረችው ላውራ ቶምፕሰን

"ሰንደቅ አላማችን ከፍ አድርገን እዚህ ስፍራ ያደረስነው እኛ ነን" የምትለው ላውራ ዋም የተባለው ኩባንያም ሰንደቅ አላማውን በነፃ እንድትጠቀም ቢፈቅድላትም እምቢተኝነቷን አሳይታለች።

የአቦርጂን ያልሆነ ኩባንያ የህዝቡ ማንነት መሰረት የሆነውን ምልከት በመዝበዝ ትርፍ ያከማቻል በማለትም ወቅሳለች።

በባለፈው አመትም የአቦርጂን ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች በሰንደቅ አላማው የተጣለውን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ተቃውሞ ተቀላቅለዋል።

በተለይም የአውስትራሊያው እግር ኳስ ሊግ ሰንደቅ አላማውን ለመጠቀም ለኩባንያው የመብት ክፍያ አልፈፅምም ማለቱ እንዲሁም የአገሪቱ ራግቢ ቡድንም በተመሳሳይ አልከፍልም ማለቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

ቡድኖቹም ሰንደቅ አላማውን ነፃ እናውጣው የሚለውን ተቃውሞ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ለአቦርጂን ህዝቦች የኩራት ምልክት የሆነው ይህንን ሰንደቅ አላማ አውስትራሊያዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ካቲ ፍሪማን የ400ና የ2000 ውድድሮችን በሲድኒ ኦሎምፒክ ካሸነፈች በኋላ የአቦርጂን እንዲሁም የአውስትራሊያን ሰንደቅ አላማ ይዛ ታይታለች።

ካቲ ፍሪማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዚህ ሳምንትም ምክር ቤቱ የሰንደቅ አላማውን ቅጅና ተዛማች መብቶች ጋር በተያያዘ እንዲጣራ ትእዛዝ አስተላልፏል።

ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቱ የህግ ባለሙያዎች የንግድ ኩባንያዎች ከአገራዊ ኩራት በፊት ትርፍን በማስቀደም ሰንደቅ አላማው ጥቅም ላይ እንዳይውል እክል ፈጥረዋል በማለትም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

መንግሥትም የተቻለውን በማድረግ ሰንደቅ አላማውን ነፃ እንዲያወጣም ጥሪያቸውን አሰምተዋል።

በአውስትራሊያ የቅጂና ተዛማች መብቶች መሰረት አርቲስቱ ሃሮልድ ቶማስም ሆነ ኩባንያው ዋም ፈቃዱንም ሆነ እንደገና ለማምረት የሚጠየቀውን ክፍያ የመጠየቅ መብት አላቸው።

በባለፈው ሳምንት የዋም መስራች ግለሰቦች ሰንደቅ አላማውን ለግል ጥቅማቸው ቢይዙት እንደማይከለክሉ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሆኖም የልብስ አምራቾች፣ ለንግድ ተግባራት ማዋልና ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙ ሰዎች በተለየ መንገድ ይታያሉ ብሏል መግለጫው።

አርቲስቱ በበኩሉ የሰንደቅ አላማውን የባለቤትነት መብት ለኩባንያው የሰጠው ለጥበብ ስራው ተገቢው ክፍያ እንዲሰጠውና በውጭ አገራት የሚገኙ ኩባንያዎችም ሆነ ድርጅቶች አጓጉል ትርፍ እንዳያጋብሱ በማለት ነው።

አርቲስቱ ቢቢሲን ለማናገር ፈቃደኛ ባይሆን ለአንድ አቦርጂን ሬድዮ በሰጠው ቃለ ምልልስ "ሰንደቅ አላማውን ሸጧል" በሚል ከፍተኘ ውግዘት እየደረሰበት እንደሆነ ነው። "ይህ ፍፁም ውሸት ነው" ማለቱንም ካማ ሬድዮ ዘግቧል። ህ

ዝቡን ክዷል የሚባለውንም ስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ብሏል።

የአውስትራሊያ ቀደምት ህዝቦች ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ኬን ዋያት እንደተናገሩት" አርቲስቱ ከየትኛው ኩባንያ ጋር የንግድ ስምምነት ይፈፅም አይፈፅም የሚለውን ጉዳይ መንግሥት መንገር አይችልም" ብለዋል።

ሆኖም የአገሪቱ ሚዲያዎች እንደዘገቡት መንግሥት የሰንደቅአላማውን መብት ከአርቲስቱ ለመግዛት ፍላጎት አሳይቷል ብለዋል።