ፌስቡክ ሞቴን ቀጥታ ካላስተላልፍኩ ያለውን ሰው አገደ

አሌይን ኮክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ግዙፉ ማሕበራዊ ድርአምባ ፌስቡክ በማይድን በሽታ የተያዘው ፈረንሳዊው ግለሰብ ሞቴን ቀጥታ ላስልተላልፍ ማለቱን ተከትሎ በፍፁም አይሆንም ብሏል።

አሌይን ኮክ የተሰኘው የ57 ዓመት ግለሰብ በዚች ምድር ላይ ያለውን የመጨረሻ ቀን በፌስቡክ ለማስተላለፍ አቅዷል።

ሰውዬው ይህን ማድረግ ያሰበው ቅዳሜ ዕለት ነበር። ኮክ፤ ምግብ፣ መጠጥና መድኃኒት አልወስድም በማለት ነበር ፍፃሜውን ለማቅረብ ያሰበው።

ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮን ሰውዬው ከዚህ በፊት ‘የሞት መድኃኒት ይሰጠኝ’ ብሎ የጠየቀውን ጥያቄ ውድቅ አድርገው ነበር።

ኮክ፤ ፈረንሳይ ውስጥ በማይድን በሽታ የሚታመሙ ሰዎች በፈቃዳቸው መሞት እንዲችሉ ይፈቅዳላቸው ሲል ይከራከራል።

የካቶሊክ ቤተክርስትያንን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ የፈቃድ ሞት [ዩታኔዚያ] መፈቀድ የለበትም፤ የሞራል ስብዕና ዝቅጠት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

“ነፃ የመውጫ ጊዜዬ ደርሷል፤ እመኑኝ ደስተኛ ነኝ” ሲል ኮክ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።

ግለሰቡ የመጨረሻዬ ያለውን ምግብ ቅዳሜ ጥዋት በልቷል።

ቀጣይ ቀናት ከባድ እንደሚሆኑ አውቃለሁ ነገር ግን ውሳኔዬ ይህ ነው፤ ደግሞም እርጋታ ላይ ነኝ” ብሏል ከሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ በላከው መልዕክቱ።

ፈረንሳዊው ግለሰብ የደም ቧምቧውን [አርተሪስ] ግድግዳዎች አንድ ላይ በሚያጣብቅ በሽታ ክፉኛ እየተሰቃየ ይገኛል።

ፌስቡክ ግን ሰውዬው ሞቴን ቀጥታ ላስተላልፍ ማለቱን አልተቀበለውም። ድርጅቱ ይህ ራስን የማጥፋት ተግባር ነው፤ ይህን አናስተላልፍም ብሏል።

ፌስቡክ “ግለሰቡ ሓሰቡን በድርጊት ለመግለፅ ያደረገውን ሙከራ ብናደንቅም ባለሙያ ካማከርን በኋላ ጥያቄውን ውድቅ አድርገናል “ብሏል።

“ሕጋችን ራስን የማጥፋት ሙከራዎችን እንዳናሳይ ያግደናል።”

ኮክ፤ ፌስቡክ ጥያቄዬን ውድቅ ያደረገው እስከ ጳጉሜ 3/2012 ባለው ጊዜ ነው ብሏል። ስለዚህም ደጋፊዎቹ ድርጅቱ ላይ ጫና እንዲያሳድሩና ውሳኔውን እንዲያስቀይሩ ጥሪ አቅርቧል።

ሰውዬው ባለፈው ሐምሌ ለፕሬዝደንት ማክሮን “በክብር እንድሞት ይፍቀዱልኝ” ሲል ደብዳቤ ፅፎ ነበር።

ፕሬዝደንቱ በበኩላቸው በደብዳቤው የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀው ነገር ግን ውሳኔው ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ተፈፃሚ ሊያደርጉለት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ዩታኔዚያ [በበሽተኞች ፈቃድ የሚፈፀም ሞት] ፈረንሳይ ውስጥ አከራካሪ ርዕስ ነው። በርካቶች ሰዎች በፈቃዳቸው በክብር ሊሞቱ ይገባል ይላሉ።

በተለይ የሐይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ ድርጊቱ ወንጀል መሆን አለበት ሲሉ ይሞግታሉ።