ኮሪያ ፡ “የአባቴን አፅም በሻንጣ ይዤ እትብቱ ለተቀበረበት ስፍራ አበቃሁት"

የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት የተጠናቀቀው በጎርጎሳውያኑ በ1953 ነበር። ጦርነቱ ቢጠናቀቅም 50 ሺህ የሚሆኑ የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ከቤታቸው እንደወጡ ቀርተዋል።
በሰሜን ኮሪያም በጦር እስረኝነት ህይወታቸውን ለመግፋት ተገደዋል። በርካታዎቹ በአስገዳጅ ግዞት ጉልበታቸው ተበዝብዟል፤ የተገደሉትንም ቤቱ ይቁጠራቸው።
በአሁኑ ወቅትም የአነዚህ ወታደሮች ልጆች እንደወጡ የቀሩ ወላጆቻቸው እውቅና እንዲሰጣቸው እየጠየቁ እንደሆነ በኮሪያ የቢቢሲ ዘጋቢ ሰቢን ኪም ፅፏል።

ምንም ጭንቅላቷን ብታስጨንቀው፣ ብትለፋም ሊ አባቷና ወንድሟ ላይ ሦስት ጥይት ከተተኮሰባቸው በኋላ ስለነበረው ነገር ምንም አታስታውስም።
ወቅቱ ከሦስት አሰርት ዓመታት በፊት ነበር፤ እድሜዋም በሰላሳዎቹ ውስጥ ነበር የሚገኘው። ወንድሟና አባቷ ከመገደላቸው በፊት ስለነበረው ግን ትናንት የነበረ ያህል ታስታውሳለች።
የፀጥታ ኃይሎች እየጎተቱ በሰሜን ኮሪያ ገጠራማ ቦታ ወደሚገኝ ስታዲየም ወሰዷት። ከእንጨት ድልድይ ስር በሚገኝ ስፍራም በማታውቀው ምክንያት እንድትቀመጥ አስገደዷት። ሕዝቡም ተሰበሰ፤ አንድ የጭነት መኪና ቆመ። ሁለት ሰዎችም ከጭነት መኪናው እንዲወርዱ ተደረጉ። አባቷና ወንድሟ ነበሩ።
"ከቆመ እንጨት ጋር አብረው አሰሯቸው። አገራቸውን የከዱ ባንዳዎች፣ ሰላዮች ፀረ-ሕዝብ እያሉ ይሰድቧቸው ነበር" በማለት የምትናገረው ሊ፤ ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር ብዙ አታስታውስም "እየጮሁኩ የነበረ ይመስለኛል።"
"መንጋጋዬ ተላቀቀ፤ ጎረቤቴም ወደቤቴ ይዞኝ ሄደ።" ትላለች

የፎቶው ባለመብት, ICRC / HANDOUT
የተረሱት እስረኞች
የሊ አባት የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በሰሜን ኮሪያ ከቀሩት አምሳ ሺህ የጦር እስረኞች መካከል አንዱ ነበሩ።
ከእነዚህም መካከል በግዳጅ የግንባታ ሥራዎች ላይና በማዕድን ቁፋሮ የተሰማሩ እንዲሁም የሰሜን ኮሪያን ጦር እንዲቀላቀሉም ከፍቃዳቸው ውጭ የተወሰነባቸው ነበሩ።
የጦርነቱን ማብቂያ ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የጦር እስረኞችን እንዲቀያየሩ ያለመ ከመሆኑ አንፃር፤ ደቡብ ኮሪያውያንም የጦር እስረኞች ወደ አገራቸው እንሄዳለን የሚል ተስፋን ሰንቀው ነበር።
ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊትም የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሲንግማን ሪ በአገራቸው በቁጥጥር ስር የነበሩ 25 ሺህ የሚጠጉ ሰሜን ኮሪያውያን የጦር እስረኞችን ወደ አገራቸው ላኩ። በዚህም የተኩስ አቁሙንም በማወጅ በጦርነቱ መቀጠል እንደማይፈልጉ አሳዩ።
ፕሬዚዳንቱ ዋነኛ አላማቸውም የነበረው የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱን ኮሪያዎች በደቡብ ኮሪያ ስር በማድረግ አንድ አገር ያደርጋቸዋል የሚልም ተስፋ ነበራቸው።
ሆኖም እሳቸው እንዳሰቡት ሳይሆን ደቡብ ኮሪያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የጦር እስረኞችን መልቀቋ በሰሜን ኮሪያ የሚገኙ የጦር እስረኞችን ሁኔታ አወሳሰበው። ሰሜን ኮሪያ በምላሹ የለቀቀቻቸው በጣም ጥቂት የሚባሉ የጦር እስረኞችን ነበር።
ደቡብ ኮሪያም የጦር እስረኞቹን እርግፍ አድርጋ ተወቻቸው። በዓመታት ውስጥ ሦስት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንቶች ከሰሜን ኮሪያ መሪዎች ጋር ቢገናኙም የጦር እስረኞቹ ሁኔታ እንደ አጀንዳ ተነስቶ አያውቅም።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሊ ቤተሰቦች በሰሜን ኮሪያውያን ዘንድ እንደ ባንዳ ነበር የሚታዩት። የሊ አባት በደቡባ ኮሪያ የተወለዱ ሲሆን በኮሪያ ጦርነትም ከተባበሩት መንግሥታት ጥምር ኃይል ጎን በመቆምም ከሰሜን ኮሪያ በተቃራኒ ተሰልፈው ተዋግተዋል።
ይህም ሁኔታ በሰሜን ኮሪያ ዘንድ ጥቁር ነጥብ እንዲጣል አደረገባቸው።
የቤተሰቡ በአቅም ዝቅተኛ መሆን በኑሯቸው ከፍተኛ ልፋትን እንዲጋፈጡ ሕይወታቸው መራራ እንዲሆን አድርጎታል። የሊ አባትም ሆነ ወንድም በከሰል ማውጫ ስፍራ ይሰሩ የነበረ ሲሆን፤ ቦታው ፈታኝ በመሆኑም በርካታ አደጋዎችም ያጋጥማል።
የሊ አባት ሁለቱ አገራት አንድ ሲሆኑ ወደ ቤታቸው የመሄድ ህልምንም ሰንቀው ነበር።
ከሥራ በኋላም ሁልጊዜም ልጆቻቸውን ሰብስበው የልጅነት ሕይወታቸውን ይነግሯቸው ነበር። በደስታ የተሞላ፣ ለምለሟና ወተትና ማር ይፈስባታል ስለሚሏቸው ደቡብ ኮሪያ ይተርኩላቸው ነበር።
ከቻሉም ወደ ደቡብ ኮሪያ እንዲያመልጡም ይመክራቸው ነበር "ሜዳልያ ይጠብቀኛል እናንተም የጀግና ልጅ ተብላችሁ፣ ትከብራላችሁ" ይለን ነበር ትላለች።
እናም የሊ ወንድም አንድ ቀን እየጠጣ እያለ ለጓደኞቹ ይህንን እቅድና አባቱ የሚያወራውን ነገር አሾለከ። አንደኛ ጓደኛው ይህን ወሬ ለሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት አስታወቀ። በወራትም ውስጥ የሊ አባትና ወንድሞቿ ተገደሉ።
በጎርጎሳውያኑ 2004 ሊ አምልጣ ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመግባት ቻለች።
አባቷ በደቡብ ኮሪያ እንደ ጀግና እታያለሁ ብሎ እንዳሰቡት ሳይሆን ማንም ያስታወሳቸውም ሆነ ከቁብ የቆጠራቸው ሰው አልነበረም።
የጦር እስረኞቹን ለመመለስ ጥረትም አልተደረገም። ወታደሮቹ በሰሜን ኮሪያ ውስጥ ኑሯቸው ስቃይ፣ ሲኦልም ነው ማለት ይቻላል።
የአገሪቱ ጠላት ተደርገው ይታዩ ነበር። በሰሜን ኮሪያ ማኅበረሰብ ውስጥ ባለው የኑሪ መደብ ደረጃ ውስጥ "ሶንግበን" በሚል ስያሜ ዝቅተኛና የመጨረሻ ስፍራም ነው የተሰጣቸው።
ይህ ሁኔታ ለጦር እስረኞቹ ብቻ ሳይሆን መከራውና ጦሱ ለልጆቻቸውም ተረፈ። የከፍተኛ ትምህርት ደረጃን መከታተልም አይችሉም ሥራም በፈለጉበት ዘርፍ ተሰማርተውም የመስራት ዕድል አይሰጣቸውም።
ቾይ በትምህርቷ ጎበዝና ኮከብ የምትባልም ተማሪ ነበረች። ሆኖም በአባቷ ምክንያት ዩኒቨርስቲ የመማር ህልሟ ተጨናገፈ።
በአንድ ወቅትም አባቷን ከፍ ዝቅ አድርጋ ስለገጠማት ነገር በቁጣ "አድሃሪ ቆሻሻ ነህ። ለምን ወደ አገርህ አትመለስም?" በማለት ዘለፈቻቸው።
አባቷም ጮክ ብለው አልተናገሯትም፤ በምላሹ አገራቸው እነሱን ለማስመለስ ደካማ ናት አሉ። ከስምንት ዓመት በፊት ቾይ ቤተሰቦቿን ትታ ወደ ደቡብ ኮሪያ ሸሸች።
"አባቴ ወደ ደቡብ ኮሪያ መምጣት ይፈልግ ነበር። በሕይወቴ የምወደውና የማደንቀው ሰው መምጣት ቢፈልግም መምጣት አልቻለም። ለዚያም ነው ልጆቼንና ባለቤቴን ትቼ የመጣሁት" ትላለች።
የቾይ አባት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቢሞቱም በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ይፋዊ መረጃ እንደሚያሳየው በጦርነቱ ወቅት እንደሞቱ እንጂ በጦር እስረኝነት በግዞተኝነት እንደሞቱ አይደለም የሚያሳየው።

የአባቴን አፅም ይዤ ተመለስኩ
ሰን ምዮንግ ህዋ አባት ሲሞቱ የመጨረሻ ኑዛዜያቸው "ወደ ደቡብ ኮሪያ ከሄድሽ አፅሜን ይዘሽ ሄደሽ የተወለድኩበት ስፍራ ቅበሪኝ" ብለው ተናዘዙ።
የሰንም አባት በምርኮ ሰሜን ኮሪያ የቀሩ የደቡብ ኮሪያ ወታደር ነበሩ። የጦር ምርኮኛም ሆነው በከሰል ማውጫ ስፍራና ደን መቁረጫ ስፍራም ለአስርት ዓመታት አገልግለዋል። በዓመታት ውስጥ ወደ ቤት እንዲሄዱ የተፈቀደላቸው ለአስር ቀናት ያህል ነበር። መጨረሻም በካንሰር ሞቱ።
ለልጃቸውም "ወላጆቼን በአካል ሳላይ መሞት እንዴት መራር እንደሆነ። እትብቴ የተቀበረበት ስፍራ ወስደሽ ቅበሪኝ" አሏት።
ሰንም ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ሸሽታ ወደ ደቡብ ኮሪያ ገባች። ሆኖም የአባቷን አፅም ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመውሰድ ስምንት ዓመት ፈጅቶባታል።
እህቶቿና ወንድሞቿን የአባቷን አፅም ቆፍረው በማውጣት ደብቀው ቻይና ወደሚገኝ ደላላ እንዲልኩ ጠየቀቻቸው። ሦስት ሻንጣዎችም ተዘጋጁ። ሁለት ጓደኞቿና እራሷም ጭምር የአባቷን አፅም ይዘው ሄዱ።

የፎቶው ባለመብት, Son Myeong-hwa
ሰን ለጦር ጀግናው አባቷ እውቅና ይሰጠው ስትልም ለዓመት ያህልም ተቃውሞ አድርጋለች። ከአምስት ዓመታት በፊትም የአባቷን አፅም እንደ መጨረሻ ኑዛዜቻቸው በብሔራዊ መካነ መቃብር ተካሄደ።
"የልጅ ግዴታዬን፣ ኃላፊነቴን እንደተወጣሁ ተሰማኝ፤ ሆኖም አባቴ የመጨረሻ እስትንፋሱ የወጣችው ሰሜን ኮሪያ መሆኑ ልቤን ሰበረው" ትላለች።
ሰን የአባቷ አፅም ደቡብ ኮሪያ እንዲቀበር ቤተሰቦቿ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደከፈሉ የተረዳችው በኋላ ነው። በሰሜን ኮሪያ የሚገኙት እህቶቿና ወንድሞቿ እስር ቤት ወረዱ።
ሰን በአሁኑ ወቅት የኮሪያ ጦር ምርኮኞች ቤተሰብ ማኅበርን እየመራች ትገኛለች። ማኅበሩ በሰሜን ኮሪያ ምርኮኛ ሆነው የቀሩ ደቡብ ኮሪያውያን ወታደር ቤተሰቦች የተሻለ ሕይወትን እንዲመሩ የሚሟገት ነው።
ሰን አባቷ የቀድሞ ወታደር መሆናቸውን ለማረጋገጥ የዲኤንኤ ምርመራ ማድረግ ግዴታዋ ነበር። በዚህም መሰረት ደቡብ ኮሪያ ለቀድሞው ወታደር ያልከፈለቻቸውን ደመወዝም መቀበል ችላለች።
ምንም እንኳን በርካታ የጦር ምርኮኛ ልጆች አምልጠው ደቡብ ኮሪያ ቢገቡም ዕውቅና አልተሰጣቸውም። ሰሜን ኮሪያ በምርኮ የቀሩ ወታደሮች ሁኔታም ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ተብሎ ይታሰባል።

የፎቶው ባለመብት, Yonhap
በጣም ጥቂት የሚባሉ የቀድሞ ደቡብ ኮሪያ ወታደር ልጆች ናቸው ከሰሜን ኮሪያ አምልጠው ወደ ደቡብ ኮሪያ መግባት የቻሉት። እነዚህ ብቻ ናቸው ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ የተከፈላቸው። ሰሜን ኮሪያ የቀሩት ወታደሮች ምንም አይነት ካሳም አልተከፈላቸውም።
በዚህም ዓመት ሰንና ጠበቆቿ፤ ደቡብ ኮሪያ የጦር እስረኞቹንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ዘንግታቸዋለች፤ ይህም ኢፍትሃዊ ነው በማለት ስለጉዳዩ በሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ክስ መስርተዋል።
"ከጦር እስረኞች መወለዳችን ኑሯችንን ጨለማ አድርጎት ነበር። ደቡብ ኮሪያም አምልጠን ከመጣን በኋላ የተቀበሉን መንገድ በጣም አሳዛኝ ነው" ብላለች።















