በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ጉዳይ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ እንደሚመሰርት ባልደራስ አስታወቀ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዘዳንት አቶ እስክንድር ነጋን በተመለከተ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ሊመሰረት መሆኑን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ ለቢቢሲ ገለጹ።

አቶ ገለታው እንዳሉት፤ ፓርቲው ክሱን የሚመሰርተው ከአቶ እስክንድር በተጨማሪ በፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና የክፍለ ከተማ አደራጅ ቀለብ ስዩም ጉዳይ ጭምርም ነው።

“በመጨረሻው የአቶ እስክንድር እና የአቶ ስንታየሁ የፍርድ ቤት ቀጠሮ፤ አቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት 15 ቀን ተሰጥቶት ነበር። ዛሬ [ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ. ም.] 17 ቀን ቢሆንም ዓቃቤ ሕግ ክስ አልመሠረተም። ስለዚህ አካልን ነጻ የማውጥት ክስ እንመሰርታለን” ሲሉ አስረድተዋል።

ዛሬ ረፋድ ላይ አቶ እስክንድር እና አቶ ስንታየሁን እንዳገኟቸው ገልጸው፤ በፓርቲው የሕግ ክፍል በኩል አካልን ነጻ የማውጣት ክሱ እንዲመሰረት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡና የፍርድ ሂደቱም በዝግ ችሎት እንዲካሄድ ሲወሰን አቶ እስክንድር በሂደቱ መሳተፍ እንደማይፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል። ጠበቃቸውንም አሰናብተው ነበር።

“ 'በከፍተኛ ወንጀል ተከሰን ለምን ችሎቱ በዝግ ይካሄዳል? ፍርድ ቤቱ ላይ አልተማመንም' ብሎ ነበር። ከዛ በኋላ በየጊዜው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲኖር በፍቃዱ ሳይሆን ፖሊስ አስገድዶ እየወሰደው ነበር” ብለዋል የሕዝብ ግንኙነቱ።

በዝግ ችሎት የምስክሮች ቃል ከተሰማ በኋላ ግን ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው 15 ቀን ክስ ባለመመሥረቱ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ለመክፈት መወሰናቸውንም አክለዋል።

አያይዘውም “የፖለቲካ እስር እንደሆነ ይታወቃል። ምስክር ተብሎ የቀረበውም አሳፋሪ ነው። ለወደፊት ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ስለሚፈራ ፓርቲውን ለማዳከም ነው። ባልደራስ ላይ ልዩ የፖለቲካ ጫና ይደረጋል” ብለዋል አቶ ገለታው።