ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በጎርፍ ምክንያት 43 ሺህ 670 ነዋሪዎች ተፈናቀሉ
በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ እስከ ዛሬ ድረስ 43 ሺህ 670 ሰዎች በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸው ተገለፀ።
የደቡብ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር፣ እንዳሻው ሽብሩ ለቢቢሲ እንደገለፁት በወረዳው ላይ 62 ሺህ ነዋሪ እንዳለ ይገመታል።
በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ ከሐምሌ 25፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው የኦሞ ወንዝ ሙላት ያስከተለው ጎርፍ ተከትሎ በውሃ የተከበቡ 19 ደሴቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን ለማውጣት በሞተር ጀልባ የታገዘ ጥረት በማድረግ 43 ሺህ 670 ቤተሰቦችን ማውጣትና በ8 ደረቃማ አካባቢዎች ማስፈር መቻሉን የወረዳው ኮሙኑኬሽን በፌስ ቡክ ገፁ ላይ አስታውቋል።
በክልሉ በስልጤ ዞን እንዲሁም ደቡብ ኦሞ ዳሰነች ወረዳ ላይ ጎርፍ ተከስቶ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተናገሩት ኃላፊው ወደፊት ዝናቡ እየጠነከረ ሲመጣ ስጋት ካለባቸው የደቡብ ኦሞ አካባቢዎች መካከል በናፀማይ፣ ኛንጋቶም ፣ እና ሀመር እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በዳሰነች ወረዳ የተፈናቀሉት ሰዎች በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረው፣ ወደ ስድስት ሺህ ሰዎች ይኖሩበት ከነበረው ሃይቅ ደሴት ላይ እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።
ለተፈናቀሉ ወገኖች የመጠለያ እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ ነው ያሉት አቶ እንዳሻው፣ በጎርፍ አደጋው ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የክልሉ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካዮች በስፍራው እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በወረዳው የኮሌራ ወረርሽኝ ይከሰታል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን በጎርፍ ምክንያት በኮሌራ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ስድስት ብቻ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ለተፈናቃዮቹ የመጠለያ ሲዘጋጅ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝመን ታሳቢ ማድረጉንም ጨምረው አስረድተዋል።
መተሃራ
የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ እንደ መተሃራ እና ወንጂ ያሉ የምስራቅ ሸዋ ከተሞች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ።
መተሃራ ከተማ ካሏት ሁለት ቀበሌዎች መካከል አንደኛውን ሙሉ በሙሉ ማጥለቅለቁን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የመተሃራ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ዲሪርሳ ለቢቢሲ፤ ይህ አይነት ጎርፍ በከተማዋ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።
በሰው ላይ የደረሰው ጉዳት እስካሁን አለመመዝገቡን ይሁን እንጂ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ከተንቲባው ጨምረው ተናግረዋል።
በጎርፍ በተጥለቀለቀው የከተማዋ ቀበሌ ወደ 20ሺህ የሚገመቱ ነዋሪዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ታደለ ተፈናቃዮችን ወደ ሌላኛው ቀበሌ እያሰፈሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ መጠኑን አሁንም እየጨመረ በመሆኑ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው ከንቲባው ተናግረዋል።
አፋር
በአፋር ክልል በሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፉ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የክልሉ የአደጋ መከላከል ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ኃላፊ አቶ ማሂ አሊ በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአሳይታ፣ አፋምቦ፣ ዱብቲ እና ዞን 3 አካባቢዎች ለተፈናቀሉት ሰዎች ከፌደራል መንግሥት፣ ከክልሎች እና ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተገኙ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በጎርፍ አደጋው እስካሁን ሰው ህይወት አለመጥፋቱን የገለጹት አቶ ማሂ ሆኖም ሰዎች ከቤታቸው ሲፈናቀሉ ምግብና መገልገያ ቁሳቁሶችን ባለመያዛቸው ለችግር ተጋልጠዋል ብለዋል።
ጎርፉ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጥጥ፣ በቆሎን ጨምሮች ከ 21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የነበሩ የደረሱ ሰብሎችን ከጥቅም ውጭ ማድረጉ ታውቋል።
ገለአሎ ወረዳ ላይ ደበል እና ገፍረሞ በሚባሉ ቀበሌዎች በውሃ የተከበቡ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ማሂ ሰዎቹን ከአካባቢዎቹ ለማውጣት ጀልባ እና ከመከላከያ ሚንስትር ደግሞ ሄሊኮፕተር ተጠይቆ እየተጠበቀ ነው።
በክልሉ አሁንም የጎርፍ ስጋት መኖሩን የጠቆሙት አቶ ማሂ አዋሽ ፈንታሌ፣ ገዋኔ፣ ገልአሎ፣ አሚበራ እና ዱለቻ በሚባሉ አካባቢዎች ከቆቃ እና ቀሰም ግድቦች በሚለቀቀው ውሃ፣ በአካባቢው እና በሌሎች አካባቢዎች እየጣለ ባለው ዝናብ ምክንያት ስጋት መኖሩን ጠቁመዋል።
ስጋት ባለባቸውን አካባቢዎች ኮማንድ ፖስት በማቋቋም የስጋት ቦታዎችን ከመለየት፣ የጥንቃቄ ሥራዎችን ከማከናወን ባለፈ ጎርፍ ተከስቶ ህብረተሰቡን ከመጉዳቱ በፊት 24 ሰዓት መረጃ ለህብረተሰቡ የሚሰጥ ቡድን ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
የተፈናቀሉ ሰዎች በ14 ጣቢያዎች ውስጥ መኖራቸውን ጠቁመው በጣቢያዎቹ ጥግግት ቢኖርም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የህክምና ባለሙያዎች እና በጎ ፈቃደኞች ትምህርት በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት ከፌደራል መንግስት በቀረበ ሔሊኮፕተር በአፋር ክልል በአደጋ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የማውጣት ሥራ ከማከናወን ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል።