ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊቢያ ጦርነት፡ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ሊቢያ ውስጥ ጥቃት መፈፀሟን ቢቢሲ አረጋገጠ
ቢቢሲ፤ ዩናይትድ አረብ ኤምቴትስ [ዩኤኢ] ሊቢያ ውስጥ በወሰደችው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት 26 ያልታጠቁ ወታደሮችን መግደሏን የሚያረጋግጥ መረጃ አግኝቷል።
ጥቃቱ የተፈፀመው ባለፈው ጥር ሲሆን በሊቢያዋ መዲና ትሪፖሊ በሚገኝ አንድ የወታደር ማሠልጠና ካምፕ ላይ ነበር።
በወቅቱ ትሪፖሊ እራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ብሎ በሚጠራው ኀዓይል ከበባ ውስጥ ነበረች።
ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ግን ጥቃቱን አልፈፀምኩም ስትል ታስተባብላለች።
ኤምሬትስ ጥቃቱ የተሰነዘረው በአገሪቱ ወታደሮች ነው ብትልም ወታደራዊ ካምፑ ላይ የወረደው ሚሳኤል 'ብሉ አሮው' የተሰኘ ቻይና ሰራሽ መሣሪያ እንደሆና መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ቢቢሲ አፍሪካ አይ እና የቢቢሲ አረብኛ የዘገባ ክፍል ባልደረቦች ማረጋገጥ እንደቻሉት ዊንግ ሉንግ ሁለት [Wing Loong II] የተባለው ሰው አልባ አነስተኛ በራሪ [ድሮን] በወቅቱ ሊቢያ ውስጥ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው አል ካዲም በተባለው ካምፕ ውስጥ ብቻ ነው።
ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ ሊቢያ ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደራዊ እርምጃ ወስጄ አላውቅም ስትል ታስተባብላለች። ነገር ግን ሊቢያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎችን እንደምትደግፍ ትናገራለች።
ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥባለች።
ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት 50 ያክል ታዳጊ ወታደሮች በደቡባዊ ትሪፖሊ በሚገኝ አንድ ካምፕ ውስጥ ልምምድ በማድረግ ላይ ነበሩ።
ያለምንም ማስጠንቀቂያ ማሠልጠኛ ማዕከሉ ላይ የወረደው ሚሳዔል 26 ታዳጊ ሠልጣኞችን ሲገድል በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል። በወቅቱ ወታደሮች ያልታጠቁ እንደነበሩ ተነግሯል።
ከተረፉት መካከል የ20 ዓመቱ አብዱል ሞዊን አንዱ ነው።
"የነበረውን ሁኔታ በቃላት ለመግለፅ ከባድ ነው" ሲል ለቢቢሲ የተፈጠረውን ያስረዳል። "ሁሉም በየቦታው ወድቆ ሲያቃስት ነበር። ሰውነታቸው የተበታተነ ጓደኞቼን አይቻለሁ፤ በጣም አሰቃቂ ነበር።"
ጥቃቱ ከደረሰ ሰባት ወራት ቢያልፉትም ለደረሰው አደጋ ኃላፊነት የወሰደ ማንም አካል የለም።
የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ጄኔራል ካሊፋ ሃፍጣር በወቅቱ ስለጥቃቱ ምንም እንደማይውቁ ጥቅሰው፤ ምናልባት እዚያ ካምፑ ውስጥ በተነሳ ጠብ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ነበር።
ቢቢሲ ምን አገኘ?
ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ጥቃቱ የተፈፀመው እጅግ በረቀቀ የጦር መሣሪያ ነው።
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የተገኙ ምስሎችን የመረመረው ቢቢሲ፤ 'ብሉ አሮው 7' የተባለው ሚሳዔል ጥቅም ላይ እንደዋለ ማረጋገጥ ችሏል። አልፎም ዊንግ ሉንግ 2 የተባለው ድሮን ሚሳዔሉን ተሸክሞ ጥቃቱን እንዳደረሰ ማረጋገጥ ችለናል።
በወቅቱ ይህ ድሮን ይንቀሳቀስበት የነበረው ብቸኛው ካምፕ አል ካዲም የተሰኘው ሲሆን ይህ ወታደራዊ ኃይል በጄኔራል ሃፍጣር ቁጥጥር ሥር ያለ ነው።
ቢቢሲም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ያገኙት ማስረጃ እንደሚጠቁመው እዚህ ካምፕ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድሮኖች ንብረትነታቸው የዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ ነው።
ባለፈው ዓመት ኤምሬትስ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉትን ሚሳዔሎችና ድሮኖች ወደ ሊቢያ ልካለች ሲል የተባበሩት መንግሥታት መውቀሱ አይዘነጋም።
ሌላኛው ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ግብፅ ከሊቢያ ድንበር ጋር የሚያዋስናትን ስትራቴጂካዊ ቦታ ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ እንድትጠቀምበት ፈቃዳለች።
አልፎም የግብፅ ንብረት ያልሆኑ የጦር ጄቶች በግብፅ አየር ሲንቀሳቀሱና ሲዲ ባራኒ በተሰኘው የግብፅ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ማረፋቸውን የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል። እኒህ የጦር ጄቶች የኤምሬትስ ንብረት መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
የግብፅ መንግሥትም ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
በሊቢያ ጉዳይ እጃቸውን ጣልቃ ያስገቡት ግብፅና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ብቻ አይደሉም። ቱርክም ሊቢያ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታትን ስምምነት የሚጥስ ተግባር መፈፀሟ ተረጋግጧል።
በቱርክ መንግሥት ድጋፍ የሚያገኘውና በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው መንግሥት የጄኔራል ሃፍጣሪን ጦር ከትሪፖሊ ማስወጣት ችሏል።