ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አረብ ኤሜሬቶች የአረቡ ዓለም የመጀመሪያ የሆነውን የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ሥራ አስጀመረች
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የአረቡ ዓለም የመጀመሪያ የሆነው የኒውክሌር ማብለያ ጣቢያ ሥራ አስጀምረች።
በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ ለማስጀመር እቅድ ተይዞለት የነበረው የኒውክሌር ጣቢያ ከሶስት ዓመታት መዘግየት በኋላ የደቡብ ኮሪያ ቴክኖሎጂ ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ባራካሃ የሚል ስያሜ የተሰጠው የኒውክሌር ጣቢያው በነዳጅ ሃብቷ ለበለጸገችው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች (ዩኤኢ) ሌላ የገቢ አማራጭ ይሆናታል ተብሏል።
ዩኤኢ ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ማርስ በማቅናት በባህረ ሰላጤው አገራት በህዋ ምርመራ ፈር ቀዳጅ መሆኗ ይታወሳል። ዩኤኢ ከዚህም በተጨማሪ ከጸሃይ ብርሃን ኃይል ለማመንጨት ከፍተኛ ገንዘብ መድባ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
በርካቶች ግን የባርካሃ ኒውክለር ማብለያ ጣቢያ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄያቸውን እያነሱ ይገኛሉ። ይህን የኒውክለር ጣቢያ ለመመስረት፣ ለማንቀሳቀስ እና የሚያስገኘውን ጥቅም ከጸሃይ ብርሃን ኃይል ጋር በማነጻጸር የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ፕሮጄክቱን የሚተቹ በርካቶች ናቸው።
ኳታር ግን ከጸሃይ ብርሃን የሚገኘው ኃይል በአነስተኛ ዋጋ ከኒውክለር የተሻለ ኃይል ያስገኛል በማለት ግንባታው አስፈላጊ አይደለም ስትል ትከራከራለች።
በቀጠናው የዩኤኢ እና ሳኡዲ አረቢያ ተቀናቃኝ የሆነችው ኳታር፤ ባራካሃ የኒውክለር ጣቢያ “ለቀጠናው ሰለም፣ ደህንነት እና ከባቢያዊ አየር ስጋት ነው” ብላ ነበር።
ዩኤኢ ይህን የኒውክለር ማብላያ ጣቢያ እየገነባች ያለችው ከኳታር ድንበር አቅራቢያ ላይ ነው። ሌላኛዋ ከባህራ ሰላጤ አገራት በቅርበ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢራን ነች።
ኢራን በኒውክለር ማብለያ ጣቢያዋ ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባት እንደምትገኝ ይታወቃል።
የዓለም አቀፉ የኒውክለር አማካሪ ቡድን ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር ፖል ዶርፍማን ከአንድ ዓመት በፊት “ኒውክለር ማብላያ ጣቢያ በባህረ ሰላጤው አገራት መካከል የሚኖረውን ፖለቲከዊ ግነኙነት ከባድ ያደርገዋል። አዲስ የኒውክለር ማብላያ ጣቢያ የኒውክለር ጦር መሳሪያ ባለቤት ማድረግ ይችላል” ብለው ጽፋው ነበር።
ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ፕሮጄክት በባህረ ሰላጤው አገራት የሬዲዮ አክቲቭ ብክለት ሊያስከትል እንደሚችልም ተነግሯል።
ይሁን እንጂ የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ የኒውክር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ባወጣው መግለጫ፤ በከባቢያው አየር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ “ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ጥንቃቄዎችን እተገብራለሁ” ብሏል።
ኮርፖሬሽኑ ጨምሮ እንዳለው፤ ፕሮጄክቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ የዩኤኢን 25 በመቶ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ይሸፍናል፤ 21 ሚሊዮን ቶን የካርበን ልቀትን ይቀንሳል። ይህ ማለት በየዓመቱ 3.2 ሚሊዮን መኪኖችን ከመንገድ ማንሳት ነው።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የዩኤኢን ባርካሃ ፕሮጄክት ሲደግፍ መቆየቱ ተነግሯል። የአቡ ዳቢ መሪ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ዛይድ በትዊተር ገጻቸው የፕሮጄክቱ ሥራ መጀመሩን በማስመልክት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።