ከሁለት ወራት በፊት ወደ ሕዋ የበረረችው ታክሲ ተመለሰች

ሁለት አሜሪካውያንን አሳፍራ ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ ያመራችው ታክሲ በሰላም ወደ ምድር ተመልሳለች።

ስፔስኤክስ የተሰኘው የግል ኩባንያ ንብረት የሆነችው 'ድራገን ካፕሱል'፤ ዳግ ሃርሊ እና ቦብ ቤንከን የተሰኙ የጠፈር ተመራማሪዎችን ይዛ ነው ከሕዋ ወደ ምድር በመምዘግዘግ በሜክሲኮ ሰርጥ ፍሎሪዳ አካባቢ ያረፈችው።

የሕዋ ተመራማሪዎች በሰላም ከጠፈር ወደ መሬት ሲመለሱ በአሜሪካ ታሪክ የዛሬ 45 ዓመት ከተከወነው የአፖሎ ተልዕኮ በኋላ የመጀመሪያው ነው።

ሁለቱን ጠፈርተኞች ያሳፈረችው ታክሲ ውሃ ስትነካ በዙሪያዋ የግል ጀልባዎች ነበሩ። ባለሥልጣናት ታክሲዋ አደገኛ ኬሚካል እንዳትረጭ በሚል ጀልባዎች ራቅ እንዲሉ ሲያሳስቡ ነበር።

የአሜሪካ የሕዋ ምርምር ተቋም ናሳ አለቃ ጂም ብራይደንስታይን 'በአካባቢው የግል ጀልባዎች ይኖራሉ ብለን አልገመትንም ነበር' ብለዋል።

በርካቶች የሕዋ ታክሲዋ ስታርፍ በአካባቢው ጀልባዎች መታየታቸው ስላስደነቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማሕበራዊ ድር-አምባዎች ሲጋሩ ነበር።

ጠፈርተኛ ሃርሊ 'ኩራትና ክብር ተሰምቶናል' ሲል በተልዕኮው በመሳተፉ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ወራት በፊት ታክሲዋ ስትመነጠቅ በቀጥታ ሲመለከቱ ነበር። ወደ ምድር በሰላም የተደረገው ጉዞም እንዳስደሰታቸው በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።

ለሁለቱ ተመራማሪዎችም ምስጋና ችረዋል።

የድራገን ተልዕኮ ለአሜሪካ ታሪካዊ ድል ነው። በግል መንኮራኩር ወደ ጠፈር የተደረገ የመጀመሪያው ጉዞ ሲሆን ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ጉዞዎችንም ቀላል ያደርጋቸዋል ተብሏል።

የባለሃብቱ ኢላን መስክ ንብረት የሆነችው ድራገን ለናሳ እንደምትሸጥም ታውቋል። ናሳ ለሕዋ ጉዞ ቢሊዮኖችን ከማፍሰስ ይልቅ ከግል ድርጅቶች መግዛት አዋጭ ነው ሲል አስታውቋል።

ታክሲዋ በሚቀጥለው ዓመት እንደገና ወደ ጠፈር ጉዞ ታደርጋለች።