ኮሮናቫይረስ ፡ ደቡብ ኮሪያ ትምህርት ቤቶች ተመልሰው እንዲዘጉ አዘዘች

ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ደቡብ ኮሪያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በዋና ከተማ ሴኡል የሚገኙ መዋዕለ ሕጻናትን ጨምሮ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በአስቸኳይ እንዲዘጉ አዘዘች።

በቅርብ ቀናት ውስጥ በዋና ከተማዋ እና በከተማዋ ዙርያ የኮሮናቫይረስ ማገርሸቱን ተከትሎ ነው ባለሥልጣናቱ እዚህ አስቸኳይ ውሳኔ ላይ የደረሱት።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 200 የሚሆኑ መምህራንና ተማሪዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ተገኝተዋል።

በዚህም የተነሳ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እስከ መስከረም 11 ድረስ ትምህርት የመስጠቱ ሂደት በርቀት እንዲቀጥል የደቡብ ኮሪያ የትምህርት ሚኒስቴር ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት በመላው አገሪቱ ወረርሽኙ መልሶ እንዳያገረሽ ስጋት አላቸው።

ዋና ከተማዋ ሴኡል 25 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል።

በርካታ ትምህርት ቤቶች በከተማዋ የሚገኙ ሲሆን ሁሉ ተማሪዎች ታዲያ ከቤት ሆነው በበይነ መረብ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ተብለዋል።

ይህ መዋዕለ ሕጻናት ያሉትንም ይጨምራል ተብሏል።

በዚህ ግዴታ ውስጥ ያልተካተቱት በታኅሣሥ ወር የዩኒቨርስቲ የመግቢያ ፈተና የሚወስዱት ብቻ ናቸው።

ከእነዚህ በተጨማሪ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተከታታዮችና በአንድ ትምህርት ቤት ከ60 ተማሪዎች በታች ያሏቸው፤ ይህንን መመርያ እንዲከተሉ አይገደዱም።

አብዛኛዎቹ የደቡብ ኮሪያ ትምህርት ቤቶች በድጋሚ የተከፈቱት ባለፉት የግንቦትና የሰኔ ወራት ሲሆን ይህም በሽታውን በተገቢው ሁኔታ መቆጣጠር በመቻሉ የሆነ ነበር።.

ደቡብ ኮሪያ እስካሁን በኮቪድ-19 ከ20ሺህ የሚያንሱ ሰዎች ነው የተያዙባት። በሞት ያጣቻቸው ዜጎቿ ደግሞ 310 ብቻ ናቸው።

አገሪቱ ቫይረሱን በመቆጣጠር ረገድ ያሳየችው ስኬታማነት ተምሳሌት ሆኖ ሲነገርላት ቆይቷል። ሆኖም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሽታው ማገርሸቱ አዲስ ስጋት ደቅኖባታል።

ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ብቻ 280 ሰዎች ተህዋሲው እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ለብዙ ጊዜያት በአገሪቱ በተህዋሲው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሳይበልጥ ቆይቶ ነበር።

ብዙዎቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ፍተሻ ሲደረግላቸው ለበሽታው የተጋለጡት ከተሳተፉባቸው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ እንደሆነ ተደርሶበታል።

ከሳምንት በፊት በሴኡል ከተማ ውስጥ የአንድ የጴንጤ ቆስጤ ቤተክርስቲያን አባላት ተሰባስበው ከተበተኑ በኋላ በዚያ መንፈሳዊ ጸሎት ላይ የታደሙ በርካቶች በበሽታው መያዛቸው ተነግሯል።

ኮሮና
Banner