ኮሮናቫይረስ ፡ ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ታዳጊዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አለባቸው ተባለ

ጭምብል ያጠለቁ ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ የጤና መመሪያ አውጥቷል።

መመሪያው ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ታዳጊዎች ባሉበት አገር አሊያም አካባቢ ለአዋቂዎች በሚመከረው መሰረት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ይገባቸዋል ይላል።

ህፃናት ቫይረሱን እንዴት ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ብዙም የሚታወቅ ነገር እንደሌለ የገለፀው ድርጅቱ፤ ነገር ግን ልክ እንደ አዋቂዎች ሁሉ ታዳጊዎችም በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የሚያመላክቱ መረጃዎችን ጠቅሷል።

ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደሌለባቸው መክሯል።

እስካሁን ዓለማችን ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ከሆነ ቢያንስ 23 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

አብዛኞቹም የተመዘገቡት በአሜሪካ፣ ብራዚል እና ሕንድ ነው።

ይሁን እንጂ በቂ ምርመራ ባለመደረጉና የበሽታው ምልክት የማይታይባቸው ሰዎች በመኖራቸው ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ይታመናል።

በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በደቡብ ኮሪያ ፣ በአውሮፓ ሕብረት አገራት እና በሊባኖስ በድጋሜ እያገረሸ ነው ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም በጎርጎሮሳዊያኑ 1918 የተከሰተውንና በአገራችን 'የኅዳር በሽታ' ተብሎ የሚጠራው 'የስፔን ጉንፋን' በሁለት ዓመት መጥፋቱን ገልፀው፤ ኮቪድ-19ም በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠፋ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ከፍተኛ የሳይንስ አማካሪ ግን ኮቪድ-19 በጭራሽ ላይጠፋ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ምክንያታቸው ደግሞ የዓለም የሕዝብ ብዛትና እንቅስቀሴ ከ100 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር አይመሳሰልም፤ የሰዎች እንቅስቃሴም በሽታውን ያዛምተዋል የሚል ነው።

በመሆኑም አማካሪው "በሽታው እንደ ሌሎች በሽታዎች አብሮን ሊኖር ይችላል፤ ሰዎችም በተወሰነ ጊዜ ልዩነት መደበኛ ክትባት ሊያስፈልጋቸው ይችላል" ብለዋል።

ድርጅቱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን በተመለከተ ለህፃናት ያወጣው መመሪያ ምን ይላል?

ድርጅቱ በድረ ገፁ ላይ ባተመው መመሪያ ላይ የህፃናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀምን በሦስት የዕድሜ ክልሎች ከፍሎ ተመልክቶታል።

  • ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ህፃናት፡ ልክ እንደ አዋቂዎች ሁሉ በዚህ ዕድሜ ክልል ያሉ ህፃናት በተለይ ቢያንስ አንድ ሜትር አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይቻልባቸውና የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
  • በ6 እና በ11 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ህፃናት፡ በአካባቢያቸው ያለው የቫይረሱ ሥርጭት ሁኔታ እና ህፃናቱ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የዕድሜ ባለፀጎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ህፃናት የአፍና አፍንጫ እንዲያደርጉ ድርጅቱ ይመክራል። ይሁን እንጂ ሲያደርጉም ሆነ ሲያወልቁ በወላጆቻቸው ክትትል ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስቧል።
  • 5 እና ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት፡ በመደበኛ ሁኔታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የለባቸውም።

ይሁን እንጅ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆናቸው ህፃናት ትምህርት ቤት ውስጥ የአፍና መሸፈኛ መጠቀም ይኖርባቸው እንደሆነ ድርጅቱ በመመሪያው ላይ ያለው ነገር የለም።

ምን አልባት አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀምር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ደንብ ሊሆን ይችላል።

ፈረንሳይ በቅርቡ ከ11 ዓመት በላይ ያሉ ሕፃናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምን አስገዳጅ አድርጋለች። ምንም እንኳን የመንግሥት መመሪያ ባይሆንም በዩናይትድ ኪንግደምም የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ወስነዋል።

ከዚህም ባሻገር ድርጅቱ መምህራን የቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ሁሉም ከ60 ዓመት በታች የሆነና በጥሩ ጤንነት ላይ ያለ አዋቂ ሰው ቢያንስ አንድ ሜትር አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ካልቻለ ከጨርቅ የተሰሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን መጠቀም አለባቸው ብሏል።

ይህ በተለይ ከህፃናት ጋር ለሚሰሩና ከህፃናት ጋር የቅርብ ግንኙነት ላላቸው ግለሰቦች በጣም ወሳኝ ነው።

ከ60 ዓመት በላይ የሆኑና የጤና እክል ያለባቸው አረጋዊያንም የሕክምና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ [medical masks] ማድረግ እንደሚገባቸው ድርጅቱ መክሯል።