ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ ፡ የትግራይ ምርጫና የተቃዋሚ ፓርቲዎች የበጀት ጥያቄ
በትግራይ ክልል ሊያካሂደው ያቀደው ስድስተኛው ዙር ክልላዊ ምርጫ ጳጉሜ 4/2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።
ምርጫውን ለማካሄድ ከአራት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ የቀረ ሲሆን በዚህም መሰረት የመራጮች ምዝገባ ቀን ከነሐሴ 15 አስከ 22/2012 ዓ.ም እንደሚከናወንና ሁለት ተጨማሪ የመጨረሻ የምዝገባ ቀናትም እንዳሉ የክልሉ የምርጫ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፀሐየ መረሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው የሚያካሂዱት ቅስቀሳ ነሐሴ 29 ተጠናቆ ከአራት ቀናት በኋላ ረቡዕ ጻጉሜ 4 ድምጽ የመስጫ ቀን እንደሚሆን ተገልጿል።
በተያያዘ ዜና ሊካሄድ አራት ሳምንታት ያህል በቀረው ምርጫ ላይ የሚሳተፉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ለምርጫው እንቅስቃሴ የሚያስፈልጋቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዳላገኙ አመለከቱ።
በምርጫው የሚሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀደም ሲል በምርጫው ሥርዓት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ካነሷቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ በበጀት ጉዳይም እንዳልተስማሙ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ክልሉ የሚያካሂደውን ምርጫ እንደማያስፈጽም መግለጹን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት የምርጫውን ወጪ እንደሚሸፍን ገልጸው ነበር።
ነገር ግን ለመካሄድ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ለቀረው ምርጫ ማስፈጸምያ የክልሉ መንግሥት የመደበው ባጀት ይፋ ያልተደረገ ሲሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንቀሳቀሻ ገንዘብ አጥተው እንደተቸገሩ ገልጸዋል።
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) የውጭ ግንኙነትና የፓርቲው የምርጫ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ከበደ የክልሉ መንግሥት ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚመድበው በጀትን በአስቸኳይ እንዲለቅ ጠይቀዋል።
እስካሁን ስለበጀት ጉዳይ የተባለ ነገር የለም የሚሉት አቶ ኃይሉ፤ ነገር ግን ኮሚሽኑ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ዝርዝርና መጠን እንዲሁም ምን ላይ እንደሚያውሉት በጽሑፍ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
"እኛ በበኩላችን ኮሚሽኑ ያቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ በመግለጽ በጀት ጸድቆ በመመሪያው መሰረት ማከፋፈልና ለተባለለት አላማ መዋሉ ኦዲት ማድረግ እንዳለባቸው ነግረናቸዋል" በማለት ከኮሚሽኑ ጋር ሳይስማሙ መለያታቸውን ተናግረዋል።
የባይቶና ሊቀ መንበር አቶ ኪዳነ አመነ በበኩላቸው "ፖለቲካ ፓርቲዎች በዓመት ውስጥ መሰራት ያለባቸውን ሥራ በአንድ ወር ጨርሱ ነው የተባለው። ይህንን ለመፈጸም ደግሞ ልዩ በጀትና የሚድያ ሽፋን ያስፈልገናል" ሲል ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ግን "የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ለምርጫ ቅስቀሳ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ መጠን ጠይቁ ብለናቸዋል፥ አሁንም እንዲያቀርቡ እየጠበቅናቸው ነው" ብለዋል።
ኮሚሽነሩ ጨምረውም የበጀት ችግር አለ የሚል ነገር እንደሌለና ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚጠበቀው የወጪዎቻቸውን መጠንና ዝርዝር አቅርቡ መባላቸውን ተናግረዋል።
"ነገር ግን ከህወሓት ውጪ እስካሁን በጀቱን የጠየቀ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለምርጫ ቅስቀሳ በተመደላቸው የአየር ሰዓት በክልሉ ባሉ የመገናኛ ብዙሃን ላይ የምረጡን ዘመቻ እተጠናቀቀ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ማካሄድ ጀምረዋል።
ነገር ግን በተሻሻለው የምርጫ ሥርዓትና የምርጫ ኮሚሽን አመራሮች ላይ ያቀረቧቸው ሀሳቦች ተቀባይነት አለማግኘታቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይህንንም በተመለከተ "በፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ ህወሓት ቢሸነፍም በምክር ቤቱ ያለውን ቦታ ተጠቅሞ የፈለገው ሕግ አውጥቷል" የሚሉት የሳልሳይ ወያነው አቶ ኃይሉ ከበድ ናቸው።
በተጨማሪ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎች እንዲሁም በድምጽ ቆጠራ ላይ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ኃይሉ "የጣቢያ አመራሮች በቤተ ክርስትያን ሳይቀር ህወሓትን ምረጡ እያሉ እያዘዙ ነው" ሲሉ ይከሳሉ።
ቀደም ሲል የምርጫው ደንብ ውይይት ወቅት መገለል እንዳጋጠማቸው ገልጸው የነበሩት የዐሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ዶሪ አስገዶም በበኩላቸው በሚካሄዱት መድረኮች እንደማይጠሩና አንዳንድ አመራሮች በስልክ ጭምር ወደሚንቀሳቀሱበት የኢሮብ ወረዳ በመደወል ስማቸውን እንደሚያጠፉ ተናግረዋል።
ህወሓት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚቀርቡበትን ክሶች እንደማይቀበል በተለያየ መንገድ የገለጸ ሲሆን ቢቢሲ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን አልተሳካም።
የክልሉ ምክር ቤት አዲስ የምርጫ ሕግ እና የሥነ ምግባር ደንብን ቀደም ሲል ያጸደቀ ሲሆን የክልሉ የምርጫ ኮሚሽንም የፓርቲና የግል ተወዳዳሪዎችን መዝግቦ ወደ እንስቃሴ ገብቷል።
የትግራይ ክልል ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ተለይቶ ምርጫ ለማካሄድ የወሰነው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ኢትዮጵያ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ከተወሰነ በኋላ ነው።
ክልሉ ምርጫውን ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ እንዲያካሂድለት ቢጠይቅም ቦርዱ ቀደም ሲል በአገሪቱ ምክርቤት የተሰጠውን ውሳኔ በመጥቀስ ሂደቱን ማስፈጸም እንደማይችል ካሳወቀ በኋላ ምንም እንኳን የሕጋዊነት ጥያቄ ቢነሳበትም ክልሉ የራሱን የምርጫ ቦርድ አዋቅሮ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነው።