ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ፡ በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ አምስት ፓርቲዎች ተመዘገቡ
በትግራይ ክልል ይካሄዳል በተባለው ክልላዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶችና 11 የግል እጩዎች መመዝገባቸው የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በምርጫው መሳተፍ የሚፈልጉ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከሐምሌ 21/2012 እስከ ሐምሌ 23/2012 እንዲመዘገቡ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገባቸው ተገልጿል።
በዚህም መሰረት በምርጫው ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው የተመዘገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ህወሓት፣ ባየቶና፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ የትግራይ ነጻነት ድርጅትና አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ናቸው።
በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካል አንዱ የሆነው ባይቶና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተግዳሮቶች እንዳሉ በመግለጽ፤ ይህ ግን በክልሉ ከሚካሄደው ምርጫ ውጪ እንደማያደርገው ገልጿል።
ድርጅቱ እንዳለው "ከፌደራል መንግሥት የሚመጣ ጫናን እንዲሁም በትግራይ ክልል መንግሥት አማካይነት እየተደረገ ያለውን አፈና ተቋቁመን ምርጫው ላይ ለመሳተፍ ወስነናል" ሲል መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
ከዚህ ባሻገር በትግራይ ክልል ላይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት አረና ትግራይ እና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ድርጀት በበኩላቸው ክልሉ ሊያካሂድ ያቀደው ምርጫ ሕገወጥ እንደሆነ በመግለጽ እንደማይሳተፉ ቀደም ብለው ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በቅርቡ የተቋቋመው የክልሉን የምርጫ ኮሚሽን የሚመሩት ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም በሰጡት መግለጫ፤ የመራጮች ምዝገባ እና ምርጫ የሚደረግበት ዕለት የተወሰነ መሆኑን በመግለጽ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም ከዛሬ ጀምሮ ለምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶላቸው በፖሊሲያቸው ላይ ክርክር ያደርጋሉ ሲለ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ ከምርጫው በተያያዘ ኮሚሽኑ በርካታ የሚጠበቁበትን ሥራዎች ለማከናወን መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ስድስተኛው ዙር ምርጫን እንዲያስፈጽምለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ በኋላ የተናጠል ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ወስኗል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰኔ ወር ባካሄደው ስብሰባ፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት ግን ሰኔ 5/2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አሳልፎ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የክልሉን የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ፣ የምርጫ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጆችን አጽድቋል።
ይህንን ተከትሎም ሐምሌ 9/2012 ዓ.ም የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚካሄደውን ክልላዊ ምርጫ የሚያስፈጽመውን ኮሚሽን የሚመሩ አምስት ሰዎችን መሾሙ ይታወሳል።