አሜሪካ፡ የዶናልድ ትራምፕ፡ ጋዜጣዊ መግለጫ በተኩስ ምክንያት ተቋረጠ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዕለታዊውን የኮቪድ-19 ማብራሪያ በመስጠት ላይ ሳሉ ከዋይት ሐውስ ደጅ በተሰማ ተኩስ ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫውን አቋርጠው በጠባቂዎቻቸው ታጅበው መውጣታቸው ተነገረ።

የፕሬዝዳንቱን ደኅንነት የሚጠብቀው የልዩ ጥበቃ ዘብ መኮንን ድንገት ጋዜጣዊ መግለጫውን አቋርጦ ወደ መድረክ በመውጣት ዶናልድ ትራምፕን ከክፍሉ ውሰጥ እንዲወጡ ተደርገዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ውስጥ የነበሩ ጋዜጠኞችም ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ካሜራቸውን ወደ ደጅ በማድረግ ሲከታተሉ ነበር።

ከአፍታ ቆይታ በኋላ ወደ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል የተመለሱት ትራምፕ "ተፈጥሮ የነበረው ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ውሏል" ብለዋል።

"አንድ ሰው እዚህ ደጅ ተተኩሶበት ነበር፤ ለዚያ ነው መግለጫዬ የተቋረጠው" ብለዋል ለሪፖርተሮች።

ፕሬዝዳንቱ ውዝግብ በማይጠፋው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሳሉ ነበር አንድ የልዩ ጥበቃ ዘብ መኮንን ወደ መድረኩ ፈጠን ብሎ በመውጣት ዶናልድ ትራምፕን በጆሯቸው አንዳች ነገር ሹክ ካላቸው በኋላ ቀልጠፍ ብሎ ወደ ጓሮ ይዟቸው የሄደው።

ትራምፕ ክፍሉን ሲለቁ "ነው እንዴ?" "ምን ተፈጠረ?" የሚሉ ቃላትን ሲናገሩ በክፍሉ የነበሩ ካሜራዎች ቀርጸው አስቀርተዋቸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በልዩ ጥበቃ ዘብ ታጅበው ገለል የተደረጉት ለስምንት ደቂቃዎች ያህል ነበር።

ሲመለሱ ምን እንደተከሰተ የተጠየቁት ትራምፕ "የልዩ ጥበቃ አባል አንድን ተጠርጣሪ ተኩሶ እንደመታውና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደ" እንደሚያውቁ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ትራምፕ አያይዘውም ለደኅንነታቸው ጠብ እርግፍ ያሉትን ጠባቂዎቻቸውን ቅልጥፍናና ሙያዊ ሥነምግባር አወድሰው አመስግነዋል።

ትራምፕን በነገር መተንኮስ ከሚወዱት ጋዜጠኞች አንዱ "ክቡር ፕሬዝዳንት፣ ወደ ጓሮ ሲወሰዱ በጣም ደንግጠው ነበር ወይ?" ብሎ የጠየቃቸው ሲሆን፣ "እርሳቸውም ቆጣ ብለው፣ የደነገጥኩ እመስላለሁ?" ሲሉ መልሰውለታል።