ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ እና ጉግል ለሚያወጡት ዜና እንዲከፍሉ ሊገደዱ ነው
የአውስትራሊያ መንግሥት ፌስቡክ እና ጉግል ለዜና እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ረቂቅ ሐሳብ አቀረበ።
የግምጃ ቤት ኃላፊው ጆሽ ፍራይደርንበርግ እንዳሉት "በዓለም ግንባር ቀደም የሆነው ይህ ረቂቅ፤ አሳታሚዎች እኩል የመወዳደርያ ሜዳ እንዲያገኙ ያግዛል።"
ዘንድሮ በርካታ የዜና ተቋሞች ገቢያቸው በመቀነሱ ሳቢያ ተዘግተዋል፤ ሠራተኛ ለመቀነስ የተገደዱም አሉ።
ፌስቡክ እና ጉግል ረቂቁን አጥብቀው ተቃውመውታል። በዚህም ሳቢያ ከአውስትራሊያ ገበያ ሊወጡ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የግምጃ ቤት ኃላፊው በበኩላቸው፤ ረቂቁ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል።
ረቂቁ ከጸደቀ፤ ለዜና የማይከፍሉ የቴክኖሎጂ ተቋሞች በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ረቂቁ ምን ይዟል?
የአውስትራሊያው የውድድር እና ሸማቾች ኮሚሽን፤ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ለዜና እንዲከፍሉ ሐሳብ ቢያቀርብም መጠኑን አልወሰነም።
የዜና ተቋሞች ተጣምረው ከቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር ዋጋውን እንዲደራደሩ ነው የሚፈልገው። በዚህም አንድ ዜና በጉግል ወይም በፌስቡክ ገጽ ሲወጣ ይከፈልበታል ማለት ነው።
በድርድር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ የውድድርና ሸማቾች ኮሚሽን እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ጣልቃ ይገባሉ።
የቴክኖሎጂ ተቋሞች ለአልጎሪዝም የሚያስከፍሉትን ለመገናኛ ብዙሃን ማስታወቅ እንዳለባቸውም ረቂቁ ይጠቁማል።
አንድ የቴክኖሎጂ ተቋም ለሚፈጽመው ጥሰት የሚጣልበት ቅጣት እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል።
ረቂቁ አሁን ያተኮረው ፌስቡክ እና ጉግል ላይ ቢሆንም፤ ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋሞች ላይም ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል።
ባለ ድርሻ አካላት ምን አሉ?
የግምጃ ቤት ኃላፊው “ለአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን የወደፊት እጣ ፈንታ ሲባል ለውጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ረቂቅ ሕጉ፤ በመላው ዓለም ያሉ መንግሥታት የሕግ አውጪዎችን ትኩረት እንደሚያገኝም ተስፋ አላቸው።
የአገሪቱ ግዙፍ መገናኛ ብዙሃን ረቂቁን ይደግፋሉ።
ኒውስ ክሮፕ የተባለው ሚዲያ ዋና ኃላፊ ማይክል ሚለር እንዳሉት፤ የቴክኖሎጂ ተቋሞች “በነጻ የሚበሉበት” ጊዜ ሊያከትም ነው።
የጉግል የአገር ውስጥ ኃላፊ ሜል ሲልቪያ "ድርጅታችን በረቂቁ በጣም ተበሳጭቷል" ብለው፤ ሐሳቡ ፈጠራ ላይ ጫና እንደሚያሳድርም ተናግረዋል።
"የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለአውስትራሊያ ዲጂታል ምጣኔ ሐብት ስጋት ነው። ለአውስትራሊያውን የምንሰጠው አገልግሎት ላይም ጫና ያሳድራል” ብለዋል።
ፌስቡክ ለዜና እንዲከፍል የሚጠየቅ ከሆነ ከገጹ ላይ የአውስትራሊያ ዜናዎችን እንደሚያስወግድ ገልጿል።
ረቂቁ ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ለአንድ ወር የምክክር ጊዜ ክፍት ነው።
ከነሐሴ በኋላ ለምክር ቤት እንደሚቀርብ የግምጃ ቤት ኃላፊው ተናግረዋል። ረቂቅ ሕጉ ከጸደቀ፤ በድጋሚ የሚከለሰው ከዓመት በኋላ ይሆናል።