የጉግል፣ የፌስቡክ የአፕልና የአማዞን ሥራ አስፈጻሚዎች ቃላቸው ሊሰጡ ነው

አራቱ የዓለም ግዙፍ ኩባንያ ባለቤቶችና ሊቃነ መናብርት በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርበው ቃላቸውን ይሰጣሉ፣ ይመረመራሉ። ይህ የሚሆነው ነገ ረቡዕ በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ነው።

ይህ በታሪክ ውስጥ ሆኖ የማያውቅ አጋጣሚ ነው።

የፌስቡኩ ማርክ ዙከርበርግ፣ የጎግል አለቃ ሰንዳር ፒቻይ፣ የአፕል ኩባንያ ሊቀመንበር ቲም ኩክ እና የአማዞን ኩባንያ ሊቀመንበርና መሥራች የዓለም ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ናቸው፤ ምክር ቤት ቀርበው በጥያቄ የሚፋጠጡት።

ከአራቱ ኃያላን መሀል ጄፍ ቤዞስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሲቀርብ ይህ የመጀመርያው ይሆናል። ሌሎቹ ከዚህ ቀደም ቢቀርቡም በአንድነት አብረው ለጥያቄ ሲጠሩ ግን ይህ በታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል።

ምክር ቤቱ ግዙፎቹን ኩባንያዎች ለጥያቄ የጠራቸው ከሚገባው በላይ ግዙፍ መሆናቸውና ይህም ግዝፈታቸው ምናልባት ሊያስከትል የሚችለውን የንግድ ተወዳዳሪነት አለመኖር ጉዳት ለመገምገም ነው።

ምርመራው በዚህ ወቅት እንዲጠራ ያደረገው አንዱ ምክንያት በርካታ የዓለም ንግድ እየተብረከረከ ባለበት ሰዓት እነዚህ ኩባንያዎች ግን ከዕለት ዕለት እያበጡ መምጣታቸው የፈጠረው ጥያቄ ነው።

አራቱ ግዙፍ የዓለም ኩባንያዎች የሚያንቀሳቅሱት ሀብት ከ5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይገመታል።

በርካታ የንግድ ተቋማት በእነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ቅሬታ አላቸው። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት ከነገ ጀምሮ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ይደመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቁጥር አንድ ቢሊየነሩ ጄፍ ቤዞስ ለምክር ቤቱ የሚያቀርበውን ንግግር ከወዲሁ በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርቶታል።

"ደንበኞቻችን ለምርቶች ያላቸው ፍቅር ለዚህ አብቅቶናል፤ ትልልቅ ተግባር እንድንፈጽም ያደረገንም ይኸው ነው። 10 ሰዎች እያለን ምን መስራት እንደምንችል አውቅ ነበር፣ አንድ ሺህ ስንሆን ከዚያም 10 ሺህ ስንሆን ምን ማድረግ እንደነበረብን አውቅ ነበር፤ አሁን ከሚሊዮን በላይ ስንሆን ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለብን አውቃለሁ" ብሏል ቤዞስ ቀደም ብሎ ባሰፈረው የመግቢያ ንግግሩ።

"አማዞን መመርመር እንዳለበት ይሰማኛል። ሁሉም ግዙፍ ተቋም ሊመረመር ይገባል። የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ሊፈተሹ ይገባል። የእኛ ኃላፊነት እነዚህን መጠይቆች በአስተማማኝ ሁኔታ ማለፍ መቻል ይሆናል" ብሏል ቤዞስ።

መውደቅ እስኪያቅታቸው ድረስ የገዘፉት ኩባንያዎች

በእነዚህ ኩባንያዎች ላይ ከሚነሱ ቅሬታዎች አንዱ ኩባንያዎቹ አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ኢንርኔቱን መቆጣጠራቸው ነው። መጫወቻ ሜዳው የእነርሱ መሆኑ ሌሎችን ለመጨፍለቅ ሳያስችላቸው አልቀረም።

ይህን ግልጽ ለማድረግ ለምሳሌ አማዞን የሌሎችን ምርቶች በሚሸጥበት ድረገጽ የራሱን ምርት እያሞገሰ ያስተዋውቃል። ይህ በራስ ሜዳ እየተጫወቱ የጆተኒ በረኛን ገልብጦ ባለጋራ ላይ ጎል ማስቆጠር እንደማለት ነው።

አፕልም ከዚህ ክስ አይድንም። አፕል ኩባንያ በእርሱ ምርቶች ላይ ለሚጫኑ ለምሳሌ ስልክ ላይ የመተግበሪያ ቋት (App Store) ሼልፍ ላይ ለሚደረደሩ መተግበሪያዎች ከሽያጫቸው 30 እጅ ይቆርጥባቸዋል። ይህም ለራስ ሲቆርሱ. . . የሚያሰኘው ነው።

ገና ጀማሪ የሆኑ መተግበሪያ ፈጣሪዎች በአፕል ላይ ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች አንዱ "የሰራነውን መተግበሪያ የት ወስደን እንሽጠው ታዲያ?" የሚል ነው።

በዓለም ላይ ለዘመናዊ ስልኮች የስልክ መተግበሪያ መሰረት ልማት የሚያቀርቡት ጉግልና አፕል ናቸው።

አፕል አይኦኤስ (iOS) ሲዘረጋ ጉግል በበኩሉ አንድሮይድ (Android) የስልክ መተግበሪያዎች መሰረተ ልማት ዘርግቷል።

ይህ ማለት አዲስ መተግበሪያ ፈጣሪዎች ከሁለቱ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ሊወዳደሩ የማይችሉበትን ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ነው።

ይህ በሌላ ቋንቋ የሰፈሩን ኮብልስቶን ያነጠፍኩት እኔ ስለሆንኩ ወደዚህ ሰፈር የምትመጡ መንገደኞች ካልከፈላችሁኝ ክንፍ አውጥታችሁ ብረሩ እንጂ ኮብልስቶኔን አትርገጡ እንደማለት ይሆናል። ይህ የጉግልና የአፕል የገበያ ቁጥጥርን የሚያሳይ ምስስሎሽ ነው።

ጉግል በበኩሉ ሰዎች አንድን ነገር ፍለጋ ድረገጹን በሚያስሱበት ወቅት ለራሱና ለአጋሮቹ ምርቶች ቅድሚያ በመስጠት፣ ተወዳዳሪ ማሰሻዎችን ጠቅልሎ በመግዛትና በመጨፍለቅ ሌሎች ተወዳዳሪ ኩባንያዎችን አክስሟል በሚል ይከሰሳል።

ጉግል ከዚህ በፊት ለዚህ ድርጊቱም ቅጣት ተጥሎበትም ያውቃል።

"ቅዳው፣ ግዛው ግደለው"

አራቱ ግዙፍ የዓለማችን ኩባንያዎች ይከተሉታል የሚባለው ምስጢራዊ የንግድ ስልት በምክር ቤቱ ይነሳሉ ከሚባሉት ጥያቄዎች መካከል ይገኝበታል።

ይህ የንግድ ስልት፣ "ቅዳ፣ ግዛ፣ ግደል" በሚል ይታወቃል።

አዲስ ተወዳዳሪ ምርት ወደ ገበያ ሲመጣ ከተቻለ ተመሳሳዩን አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ ተወዳዳሪ ምርት በማምጣት ማዳከም፣ ከዚያም ድርጅቱ ሲዳከም መግዛት፣ በመጨረሻም ከገበያ ማስወጣት እነዚህ አራቱ ድርጅቶች ሁልጊዜም ይከተሉታል ተብሎ የሚታሰብ ስልት ነው።

ይህም ስልት ነው ያለተቀናቃኝ ዘወትር ትርፍ አጋባሽ ያደረጋቸው ይባላል።

አራቱ ኩባንያዎች ማለትም ፌስቡክ፣ አማዞን፣ ጉግልና አፕል የሚወዳደሯቸውን ኩባንያዎች ቶሎ ጠቅልለው በመግዛት ይታወቃሉ።

ይህ የተወዳዳሪነት ሕግን የሚጥስ አሰራር እንደሆነ ይነገራል።

አንድ ድርጅት ወደ ሞኖፖሊ አሰራር ገብቷል የሚባለው አንድ ሸማች ለአገልግሎት ወይም ለምርት ለዚያ ኩባንያ የከፈለው ዋጋ አማራጭ በማጣቱ ለመክፈል ሲገደድ ነው።

ይህ ወደ ሞኖፖሊ የመጠጋት ነገር በሌሎች ኩባንያዎች ላይ በቀላሉ ለይቶ መንቀስ እንደሚቻለው በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያን ማድረግ ከባድ ሆኗል። አንደኛው ምክንያት የጸረ ተወዳዳሪነት ሕጉ የማያሻማ ትርጉም አለመስጠቱ ነው። ይህም ሁኔታ አራቱን ድርጅቶች ለሕግ ለማቅረብ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ነጻ አገልግሎት በመስጠት ሸማችን መበዝበዝ

ለምሳሌ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ዋትስአፕ አገልግሎቶቻቸውን ለተግልጋይ የሚያቀርቡት በነጻ ነው።

ነጻ በሆነ አገልግሎት ውስጥ የሞኖፖሊን ሕግ አንስቶ ክስ መመስረት ቀላል አይሆንም።

አማዞን በበኩሉ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን ለመዘረር በምርቶቹ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ያደርጋል። በራሱ ገጽ ላይ ምርታቸውን የሚሸጡት ይህን መቋቋም ይሳናቸዋል። ምክንያቱም አማዞን በሸጡት ምርት ልክ ትርፍ ስለሚጋራቸው ነው።

ለምሳሌ የጉግል ነገረ-ማሰሻው (search engine) ነጻ ነው። ሌላው የጉግል ንብረት የሆነው ዩትዩብም እንዲሁ ነጻ አገልግሎት ነው የሚሰጠው። ለስልክ የሚሆኑ መተግበሪያዎችንም ከጉግል ለማውረድ ከሞላ ጎደል ነጻ ነው።

ይህ ታዲያ ምን ችግር አለው ይሉ ይሆናል?

ክርክሩም የሚነሳው ከዚሁ ነው። ተቺዎች እንደሚሉት እነዚህ ኩባንያዎች አገልግሎቱን ነጻ ያደረጉት ተወዳዳሪዎች ድርሽ እንዳይሉባቸው እንጂ ለጋስ ሆነው አይደለም።

በነገው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ይኸው ጉዳይ ለአራቱ ኃያል ሊቃነ መናብር ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሸማች መብትና ከኢፍትሀዊ ውድድር ጋር ከተያያዙ ጥያቄዎች ባሻገር የፌስቡኩ ማርክ ዙከርበርግ የጥላቻ ንግግሮችን ከገጹ በቶሎ ለምን እንደማያነሳ ጥያቄ ይቀርብለታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፌስቡክ በተለያዩ አገራት የጥላቻ ንግግሮችን ቸል በማለቱ ፖለቲካዊ ጥፋቶች እየደረሱ እንደሆነ ይነገራል።

የጆርጅ ፍሎይድን የግፍ ግድያ ተከትሎ ፌስቡክ በጥቁሮች ላይ ከነጭ አክራሪዎች የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮችን ቶሎ ለማንሳት ዳተኛ መሆኑ ክፉኛ ሲያስተቸው ቆይቷል።

የፌስቡክን ድርጊት ለመቃወም ግዙፍ ኩባንያዎች ማስታወቂያዎቻቸውን ከፌስቡክ ላይ ለማንሳት እስከመወሰን አድርሷቸዋል።

በነገው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፊት የሚቆመው ማርክ ዙከርበርግ "ለመሆኑ የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ምን ለማድረግ አስበኻል?" የሚል ጥያቄ ይጠብቀዋል።