"ከዓመት በፊት ከነበሩብን የሠላም ችግሮች በአንጻራዊነት ተላቅቀናል" አቶ ተመስገን ጥሩነህ

የአማራ ክልል ከዓመት በፊት ከነበሩበት የሠላም ችግሮች በአንጻራዊነት መላቀቁን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ "አፍራሽና ለውጥ አደናቃፊ" ያሏቸው ኃይሎች በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የጥፋት አጀንዳ እና የማንነት ጥያቄዎችን በማንሳት አለመረጋጋት ለመፍጠር መሞከራቸውን ገልጸዋል።
ጨምረውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በአንዳንድ ስፍራዎች ችግር በመፍጠር ግጭት እንዲከሰትና በሰው ህይወት እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ብለዋል።
አቶ ተመስገን ይህን የተናገሩት የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተጀመረበት ጊዜ ሲሆን፣ አቶ ተመስገን የ2012 የአስፈጻሚ አካላት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትንም አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በተለይ በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ እንደተናገሩት አፍራሽ ያሏቸው ኃይሎች "በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ የሚለቀቁ ሐሰተኛ ትርክቶችን በማሰራጨት ክልሉን ወደ ትርምስ ለማስገባት ሁሉን አቀፍ መንገዶችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል" ብለዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ከሚንቀሳቀሱት መካከል በተለይ "የቅማንት ኮሚቴ ነኝ በሚል ጥላቻን ካነገቡ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ትራንስፖርት እንዲቋረጥና በከተሞች ነውጥ እንዲሰፍን ያደረጉት ጥረት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ ተሠርቷል" ሲሉ ጠቅሰዋል።
በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰላም ለማስፈን እርቀ ሰላም እንዲፈጠር መደረጉን የገለጹት አቶ ተመስገን ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ያሏቸው 387 ሰዎች በምህረት እንዲገቡ ተደርጎ አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት ለመፍጠር ተችሏል ብለዋል።
"የፋኖን ስም በመጠቀም በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የክልሉን ሕዝብ ላይ ችግር በመፍጠር መንግሥት ሕግን ማስከበር የማይችል ለማስመሰል" መሞከሩን አስታውሰው ይህንን ችግር በዘላቂነት በሠላም ለመፍታት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር በተደረገው ጥረት 215 በምህረት ሲገቡ 405 ሠላማዊ በሆነ መንገድ እጅ ሰጥተዋል። ፈቀደኛ ያልነበሩ 686 ሰዎች ደግሞ በኃይል እጅ እንዲሰጡ መደረጉን አመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ለክልሉ ምክር ቤት እንደተናገሩት "ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ሆኖ የተለያዩ አካባቢዎችን ሲያተማርምስ የነበረውን ሕገ ወጥ ኃይል የማፍረስ ሥራም ወርቃማ ነው" ሲሉ ስኬታማነቱን ገልጸውታል።
አክለውም የክልሉ ተወላጆችን መፈናቀል፣ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በተደራጁ ቡድኖችና ግለሰቦች ሲፈጸም የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ከበስተጀርባው የጸረ ለውጥ ኃይሉ እጅ ያለበትና ሁሉንም ክልሎች የቀውስ ቀጠና ለማድረግ የታሰበ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"ለውጥ አደናቃፊው ቡድን" ያሉት ኃይል የክልሉን ሰላም ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር በመሆን አካባቢውን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ።
ይህ ኃይል "አሁንም ሕዝብን ለማደናገር ሐሰተኛ መረጃ ሆን ብሎ እየለቀቀ ለዘመናት በአብሮነት የኖረውን የቅማንትና የአማራ ሕዝብ ወደ ግጭት እንዲያመራ እየሠራ ነው" ሲሉ ከስሰዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በተጨማሪ እንደተናገሩት ለዘመናት በክፉም ሆነ በደግ አብረው የኖሩ በሥጋም ሆነ በደም የተጋመዱ "የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን ለማጋጨት በአማራ አዋሳኝ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የተለያዩ ጠብ አጫሪና የትንኮሳ ተግባራት" እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንን "ትኮሳውና ጠብ አጫሪነት ፈር ለማስያዝ የሚመለከታቸው አካላት እንዲገነዘቡና የክልሉ የትኛውንም ራስን የመከላከል ተግባር ሕዝቡ እንዲደግፍ" ጠይቀው ይህን መፈጸም ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ለምክር ቤቱ አሳውቀዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤው የ2012 ዓ.ም በጀት ሪፖርት ግምገማ፣ የሕግ የበላይነትና በሰላም ማስከበር፣ ኮቪድ-19ን በዘላቂነት መከላከል እና በሌሎችም ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች እንደሚመክር ይጠበቃል።















