ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንዲት የቴሌቪዥን ተመልካች የላከችው መልዕክት የጋዜጠኛዋን ጤና ታደገ
የጋዜጠኛዋ አንገት እብጠት መጨመሩን ያስተዋለች ተመልካች ለጋዜጠኛዋ ያደረሰችው መልዕክት የጋዜጠኛዋን ጤና ታድጓል።
የፍሎሪዳዋ ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ፕራይስ የያዛት ካንሰር እያደገ መምጣቱን ተመልክታ መልዕክት ለላከችላት ተመልካቿ ምስጋናዋን አቅርባለች።
“ባለፈው ወር ከአንድ ተመልካች የኢሜይል መልዕክት ደረሶኝ ነበር” ስትል ለአንድ የፍሎሪዳ ግዛት ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘጋቢነት የምትሠራው ቪክቶሪያ ፕራይስ ጽፋለች።
“አንገቴ ላይ እብጠት ተመልክታ ‘እኔን አስታወስሽኝ’ ስትል ጻፈችልኝ” ብላለች ዘጋቢዋ።
“የእሷ ካንስር ነበር። የእኔም ካንሰር ሆኖ ተገኝቷል” ብላለች ዘጋቢዋ ቪክቶሪያ ፕራይስ። ህክምናዋን ለመከታተል ሥራ ማቆሟንም ጋዜጠኛዋ ተናግራለች።
በስም ያልተጠቀሰውችው የኢሜይል መልዕክቱን የላከችላትን ሴትን እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ ያለችው ጋዜጠኛወዋ፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በሙሉ ትኩረት እየዘገበች ለራሷ ጤና ትኩረት ሳትሰጥ መቆየቷን ተናግራለች።
“የክፍለ ዘመናችን ጉዳይ የሆነውን ኮሮናቫይረስ በምዘግብበት ወቅት የእኔ ጤና አነስተኛ ትኩረት ልሰጠው የምችለው ነገር ነበር” ብላለች።
ከተመልካቿ መልዕክት ከደረሳት በኋላ ወደ ጤና ተቋም የሄደችው ቪክቶሪያ፤ የጉሮሮ ካንስር እንዳለባት እና አንገቷ ላይ ያለው እብጠት በቀዶ ጥገና መወገድ እንዳለበት ተነግሯታል።
“ዶክተሮቹ አንገቴ ላይ ያለው እጢ እያደገ ስለሆነ በአስቸኳይ መነሳት እንዳለበት ነግረውኛል። የፊታችን ሰኞ የቀዶ ህክምና አደርጋለሁ” ብላለች።
“ኢሜይሉ ባይደርሰኝ ኖሮ፣ ወደ ህክምን አልሄድም ነበር። ካንሰሩ አድጎ እጅግ አሰፈሪ ነገር ይከሰት ነበር” ስልት ጋዜጠኛዋ ጽፋለች።
ተመልካቾች በቴሌቪዥን የሚመለከቷቸው ጋዜጠኞች የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ሲያሳስቡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
የቢቢሲውን ስፖርት ጋዜጠኛ ማርክ ላውረንሰንን የስፖርት ዘገባዎች ይመለከት የነበረ አንድ የጤና ባለሙያ ላውረንሰን ምርመራ እንዲያደርግ በጠቆመው መሠረት ላውረንሰን የካንሰር ህክምና እንዲጀምር አድርጎታል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ታሬክ ኤል ሙሳ የተባለው ጋዜጠኛ አንድ ነርስ አንገቱ ላይ ያስተዋለችውን እብጠት በተመለከተ ባደረሰችው ጥቆማ መሠረት ጋዜጠኛው ባደረገው ምርመራ ሁለተኛ ደረጃ ደርሶ ከነረው የጉሮሮ ካንሰር መዳን ችሏል።