ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሲንጋፖር ዜጋ በአሜሪካ ለቻይና ሲሰልል እንደነበረ አመነ
የሲንጋፖር ዜጋ የሆነው ግለሰብ በአሜሪካ ለቻይና ሲሰልል እንደነበረ አመነ።
ጁን ዌይ ዬኦ የተባለው ግለሰብ የፖለቲካ አማካሪ ድርጅቱን ተጠቅሞ በአሜሪካ ለቻይና የደህንነት ተቋም ሲሰራ እንበረ አምኗል ሲሉ የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ከሰሞኑ በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው እሰጣ ገባ አይሏል።
አሜሪካ በሂውስተን የሚገኘውን የቻይና ቆንስላ መዝጋቷን ተከትሎ ለዚሁ ምላሽ እንዲሆን ቻይናም በቼንግዱ የሚገኘውን የአሜሪካ ቆንስላ እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፔዮ ቆንስላውን ለመዝጋት የተወሰነው ቻይና የአሜሪካን አዕምሯዊ ንብረት ‘እየሰረቀች’ ስለሆነ ነው ብለዋል።
የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ግን ይህ ሁሉ የአሜሪካ እርምጃ የሚመነጨው ‘ከቻይና ጠል ውሸቶች ነው’ ብለዋል።
አሜሪካ በሂውስተን የሚገኘው የቻይና ቆንስላ እንዲዘጋ የሰጠችው ቀነ ገደብ ሲጠናቀቅ የአሜሪካ ጸጥታ ኃይሎች የቆንስላውን በር ከፍተው ወደ ቆንስላው ቅጥር ግቢ ሲገቡ ታይተዋል።
የቆንስላው ሰራተኞች እቃቸውን ሸክፈው ሲወጡም ተስተውሏል። ቆንስላው በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ተዘግቧል።
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከቻይና መንግሥት ጋር በንግድ፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በሆንግ ኮንግ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ሲጋጭ ይስተዋላል።
ስለ ሲንጋፖሩ ዜጋ የሚታወቀው ምንድን ነው?
ጁን ዌይ ዬኦ ወይም ዲክሰን ዩኦ ተብሎ የሚታወቀው ግለሰብ ትናንት በአሜሪካው የፌደራል ፍርድ ቤት ለቻይና መሰለሉን አምኖ ጥፋተኛ ነኝ ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።
እአአ 2019 ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለው ጁን ዌይ ዬኦ ከእአአ 2015 እስከ 2019 ድረስ ለቻይና መንግሥት ሲሰልል መቆየቱን ማመኑን የአሜሪካ ፍትህ ተቋም አስታውቋል።
ግለሰቡ በቀላሉ ማግኘት የማይቻሉ መረጃዎችን እየሰበሰበ ለቻይና ሲያቀብል ነበር ተብሏል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ባመለከተችበት ወቅት ከቻይና ጦር ጋር ግነኙነት የለኝም ብላ ዋሽታ የነበረችው ቻይናዊት ተመራማሪ በቁጥጥር ሥር መዋሏን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ጁዓን ታነግ የተባለችው የ37 ዓመት ተመራማሪ ቪዛ ማጭበርበር በሚል ወንጀል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ክስ ከተመሰረተባቸው አራት ቻይናውያን መካከል አንዷ ናት።
በጁዓን ላይ የቀረበው ክስ በቻይና ህዝቦች ነጻነት ጦር ውስጥ የነበራትን ተሳትፎ የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ባመለከተችበት ወቅት ደብቃለች የሚል ነው።
የአሜሪካው ኤፍቢአይ ጁዓን የወታደር ዩኒፎርም ለብሳ የሚያሳይ ምስል አግኝቷል።