ለዓመታት የሶሪያን ጦርነት በምስጢር ፎቶ ያነሳው ጋዜጠኛ

ስሙ አቡድ ሀማም ነው። ማንነቱን ሳይገልጽ ለዓመታት በመላው ዓለም ላሉ መገናኛ ብዙሃን ስለሶርያ መረጃ ሰጥቷል።

መጀመሪያ ላይ በፎቶ አንሺነት የቀጠሩት የአገሪቱ ፐሬዝዳንትና ባለቤታቸው በሽር እና አስማ አል-አሳድ ነበሩ። ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) የድል ሰልፍ ሲያካሂድ ቪድዮ የቀረጸው አቡድ ነው።

አሁን ማንነቱን ይፋ አድርጓል።

እስኪ ራስህን ግለጽ? ሲባል “ማንነቴን የቀረጸው ዘጠኝ ዓመት የዘለቀው ጦርነት ነው” ብሎ ይመልሳል።

“ራሴን በመስታወት ሳይ መሸበቴ ይታወቀኛል። እንዲህ ያደረገኝ ጦርነቱና ጭንቀቱ ነው።”

አቡድ 45 ዓመቱ ነው። ሕይወቱ በፍርሃት የተሞላ ነው። ዓለም ስለሶርያ ጦርነት እውነታውን እንዲያውቅ ለማድረግ ለዓመታት ለፍቷል።

ፎቶ ሊገልም ሕይወት ሊያተርፍም ይችላል

ምናልባትም በሁሉም የሶርያ ኃይሎች ስር የሠራ ብቸኛው የፎቶ ጋዜጠኛ ሳይሆን አይቀርም።

በአሳድ አምባገነን ዘመን፣ በተቃዋሚው የፍሪ ሲርያን አርሚ፣ በተቀናቃኞቹ የእስልምና ቡድኖች ማለትም በጃብሀት አል-ኑስራ እና በኢስላሚክ ስቴት እንዲሁም የኩርድ አካባቢን በሚቆጣጠረው አካባቢ ስር ሠርቷል።

“ፎቶ ሊገልም ሕይወት ሊያተርፍም ይችላል” ይላል ጋዜጠኛው።

አማጽያን በደማስቆ ላይ ያደረሱትን ጥቃት የሚያሳይ ፎቶ በድብቅ ካነሳ በኋላ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ሰግቶ ነበር። ሙካሃብራት የሚባሉት ሚስጥራዊ ፖሊሶች ፎቶ ማንሳቱን ቢያውቁ ይገሉት ነበር።

ይህ የሆነው ገና አመጹ ሲቀሰቀስ ነው። ያኔ መንግሥት ስለ አማጽያኑ ወታደራዊ አቅም እንዲታወቅ አይፈልግም ነበር።

አይኤስ የአቡድን የትውልድ ከተማ ረቃ በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ፤ ድሉን በአደባባይ ሲያከብር ፎቶ እንዲያነሳ የተጠየቀው አቡድ ነበር።

ፎቶ ማንሳት የጀመረው ረቃ ሳለ ነበር። አባቱ አርሶ አደር ነበሩ።

“እውነቱን ለመናገር ያደግኩበት ማኅበረሰብና ቤተሰቤም ለጋዜጠኝነት እና ለፎቶ አንሺነትም ዋጋ አይሰጥም። ፎቶ አንሺነት የማይረባ ሥራ ነው ብለው ያምናሉ። መምህር ወይም ጠበቃ እንድሆን ነበር የሚፈልጉት።”

ታላቅ ወንድሙ የሩሲያ ካሜራ ከሰጠው በኋላ በፎቶ ፍቅር ወደቀ።

ከደማስቆ የፎቶ ትምህርት ቤት ተመርቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2011 ላይ አመጽ ሳይቀሰቀስ በፊት በአገሪቱ ብሔራዊ የዜና ተቋም ‘ሳና’ ዋና ፎቶ አንሺ ሆኖ ተቀጠረ።

ፕሬዘዳንት አል-አሳድ እና ባለቤታቸው አስማን ፎቶ ማንሳት የሥራው አካል ነበር። ጥንዶቹን ፎቶ ሲያነሳ አንድም ቀን አዋርተውት እንደማያውቁ ያስታውሳል።

“ይፋዊ ጉብኝት ሲካሄድ ፎቶ አንሺዎች በከፍተኛ ወታደሮችና የደኅንነት ኃላፊዎች እንታጀብ ነበር። በጣም ነበር የሚያስጠላኝ። እነሱን ማክበር ይጠበቅብናል። እኔ ደሞ እንደዚያ አይነት ሰው አይደለሁም።”

“ብያዝ እንደምገደል ሁሌ አስብ ነበር”

ከዘጠኝ ዓመት በፊት በሶሪያ አመጹ ተቀሰቀሰ። በዚህም አቡድ ሁለት አይነት ሕይወት ለመምራት ተገደደ። ቀን ላይ የመንግሥትን ገጽታ የሚገነባ ሥራ ይሠራል። ማታ ደግሞ ተቃውሞውን ይቀርጻል።

ፍሪ ሲሪያን አርሚ በመንግሥት ላይ በሚያካሂደው አመጽ የሶርያ መዲና ደማስቆ ላይ ጥቃት ይሰነዝር ነበር።

የሚያነሳቸውን የተቃውሞ ፎቶዎች ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚልከው ኑር ፉራት የተባለ የብዕር ስም ተጠቅሞ ነበር።

ፉራት በራቃ የሚያልፈው የኤፍራጠስ ወንዝ አረብኛ መጠሪያ ነው። አቡድ መንፈሱን ማፍታት ሲፈልግ የሚሄደው ወደዚህ ወንዝ ነው።

እስከዛሬ ድረስ ፎቶ የሚልክላቸው መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ ስሙን እንደማያውቁ ይናገራል።

ከጊዜ በኋላ ለእነዚህ መገናኛ ብዙሃን ፎቶ መላክ አስፈሪ እየሆነ መጣ።

“በድብቅ የማነሳቸውን ፎቶዎች የማስቀምጥበትን ሜሞሪ የምይዘው በኪሴ ነው። ብያዝ እንደምገደል ሁሌ አስብ ነበር።”

2013 ላይ ራቃ በአማጽያን ቁጥጥር ሥር የወደቀች የመጀመሪያዋ የሶርያ ከተማ ሆነች። አቡድም ከደማስቆ አምልጦ ረቃ ተመለሰ።

ራቃ ውስጥ ፎቶ ጋዜጠኛ መሆንም አስጊ መሆኑ ግን አልቀረለትም። አማጽያኑ የመንግሥት ቅጥረኛ ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ ብሎ ይፈራ ነበር።

“ገለልተኛ ሆኜ የምኖርበት ስልት ቀይሼ ነበር”

2014 አጋማሽ ላይ ነገሮች ተባባሱ።

“ጥቁር ሰንደቅ አላማ ያነገቡ ሰዎች በሞተር ሳይክል ሆነው ከተማው ውስጥ ይዘዋወሩ ጀመር” ሲል ያስታውሳል።

ከተማዋ ውስጥ የገቡት የአይኤስ አባላት ነበሩ። መግባታቸውን ተከትሎም በርካታ ጋዜጠኞች ከከተማዋ ሸሽተዋል።

ቀድሞው በአሳድ መንግሥት ስር ይሠራ የነበረው አቡድ ከማንም በላይ ለአደጋ ተጋላጭ ቢሆንም፤ ከተማዋን አለቀቀም። እንዲያውም ሥራውን ቀጠለ።

አይኤስ የድል ሰልፉን በካሜራው እንዲያስቀር ሲጠይቀው ከመቀበል ውጪ አማራጭ አልነበረውም። አይኤስ ለዓለም አቀፍ ተቋማት የላካቸው የፕሮፓጋንዳ ፎቶዎችም እሱ ያነሳቸው ናቸው።

አቡድ ሰዎች አንገታቸውን በሚቀሉባቸው ቀናት ከቤቱ አይወጣም ነበር።

“አይኤስን ለመደገፍ ቃል አልገባሁም። ገለልተኛ ሆኜ የምኖርበት ስልት ቀይሼ ነበር።”

ራቃ ውስጥ ከማኅበረሰብ መሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላለው ሳይታሰር እንደቀረ ያምናል። መሪዎቹ ኋላ ላይ አይኤስን ተቀላቅለዋል።

2015 ላይ ግን ሁለት የአይኤስ አባላት ሥራውን ካላቆመ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ስላስፈራሩት ራቃን ለቀቀ። ወደ ሌላ ሰሜናዊ የሶርያ ከተማ ሄዶ ጦርነቱን መዘገቡን ቀጠለ።

እስከ 2017 ወደ ራቃ አልተመለሰም። በዚያ ዓመት አሜሪካ መራሹ ጸረ አይኤስ ኃይል ከተማዋን ከሽብርተኞች ነፃ አውጥቷል።

ከተማዋ ነፃ ብትወጣም እንዳልነበረች ሆናለች።

“መጀመሪያ ከተማዋን ያየኋት ቀን ምንም መናገር አልቻኩም። በሁለተኛው ቀን ከቤት ወጥቼ ፎቶ ማንሳት ስጀምር አለቀስኩ። ከተማዋን እየዞርኩ አነባሁ።”

ለወራት ራቃን እየዞረ ፎቶ አነሳ።

ጸጥ ረጭ ባሉት ጎዳናዎች ተመላለሰ። የተበታተኑ ቤተሰቦችን አየ።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ 80 በመቶ የሚሆነው የከተማዋ ክፍል ላይመለስ ወድሟል። 90 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎቿ ደግሞ ሸሽተዋል።

ካነሳቸው ልብ የሚሰብሩ ፎቶዎች አንዱ የፈራረሰ ፎቅ ያሳያል። ፎቁ ውስጥ ከነበሩ ቤቶች በአንዱ ደማቅ ቀሚስ ተሰቅሏል። ይህ ፎቶ ለአቡድ ትርጉም አለው።

“የሰው ሕይወት እንደተጣሰ ተሰማኝ። ይህን ልብስ ሴቶች የሚያዘወትሩት ቤት ሲሆኑ ነው። ቤቱ ውስጥ ይኖር የነበረው ቤተሰብ የለም። የቤቱ ደስታ ተገፏል። ቀሚሱ ብቻውን ቀርቷል። ንፋስ ቀሚሱን ሲያወዛውዘው ዝም ብዬ አይ ነበር። ተሰቅሎ ለሞት የሚያጣጥር ሰው ነው የመሰለኝ።”

ቃን ደግማችሁ ውደዷትና ተመለሱ”

ቀስ በቀስ ከተማዋ ሕይወት ስትዘራ የአቡድ ፎቶዎችም ነፍስ ዘሩ።

ሱቆች ተከፈቱ። በኤፍራጥስ ወንዝ የሚዋኙ ሰዎችም ይታዩ ጀመር። እሱም ማንነቱን ይፋ ለማድረግ ወሰነ።

ፌስቡክ ላይ ‘አቡድ ዊዝአውት ባሪየርስ’ (አቡድ ያለ ሽፋን) በሚል ሥራዎቹን ማሳየት ጀመረ። አላማው ሰዎች ወደ ራቃ እንዲመለሱ ለማድረግ ነው።

“ከተማዬን የገጠማትን ክፉ ነገር ማሸነፊያ መንገድ ነው። ሩቅ ያሉ የራቃ ነዋሪዎች ከተማቸውን በተለየ መንገድ እንዲያዩ ማድረግ እፈልጋለሁ። ከተማችን እንደጨለመች አውቃለሁ። ቀለሟ ግራጫ ሆኗል። ግን እንዴት በቀለማት የተዋበች እንደነበረች አስታውሱ። ራቃን ደግማችሁ ውደዷትና ተመለሱ። ፎቶዎቼን ብታዩ በአሳዛኝ ምስል ውስጥ እንኳን ሕይወት ታገኛላችሁ።”

በጣም የሚኮራበት ፎቶ አንድ ደማቅ ቀለም ያለው ቀሚስ ያረገች ታዳጊን ያሳያል። ወደ ሳኡዲ አረቢያ ሄዶ የነበረና ከቤተሰቡ ጋር ለመቀላለቀል ወደ ራቃ የተመለሰ ሰው ልጅ ናት።

ግለሰቡ ፌስቡክ ላይ የአቡድን ፎቶዎች ከተመለከተ በኋላ በአካባቢው ትምህርት ቤት እንዲሠራ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ሌሎችም ፎቶውን ያዩ ሰዎች ወደ ራቃ ለመመለስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

አቡድ አሁን ከራቃ ወጥቶ በቱርክ ቁጥጥር ሥር ባለውና በግጭት በሚናጠው ሰሜናዊ ሶሪያ ውስጥ ፎቶ እያነሳ ነው። ወደ ራቃ ቢመለስ በኩርዶች የሚመራው አማጺ ቡድን የቱርክ ሰላይ ነህ እንዳይለው ይፈራል።

ብዙ አስፈሪ ነገሮችን አልፏል። ሆኖም ግን ከምዕራባውያን ጋር በመሆን ራቃን ከጽንፈኞች ያላቀቃት ቡድንም ያስፈራዋል። ሶሪያ ውስጥ ጋዜጠኛ መሆን እስከወዲያኛው ከስጋት ጋር መኖር ማለት እንደሆነ የሚያስበውም ለዚህ ነው።

“በሕይወቴ በሰላም እና በደስታ ያሳለፍኩት ጊዜ ትዝ አይለኝም። አንድ ጊዜ የአየር ድብደባ ቀርጬ ስጨርስ ከሞቱት አንዱ የአክስቴ ልጅ እንደሆነ ተነግሮኛል። ያነሳሁትን ቪድዮ ተመልሼ ስመለከተው አስክሬኑን አየሁት።”

“በጦርነቱ ሳቢያ አላገባሁም”

አቡድ እንደሚለው፤ በጦርነቱ ሳቢያ አላገባም፤ ቤተሰብ አልመሰረተም።

“45 ዓመቴ ነው። ቤተሰብ የለኝም፤ ሚስት የለኝም፤ ያሳዝናል። ይሄ ካሜራ ባይኖረኝ ሽጉጥ ይኖረኝ ነበር። እኔ ግን በመሣሪያ አላምንም። ምናልባት እንደማንኛውም ሰው ጦርነቱ ውስጥ ብገባ ኖሮ ጉዳቱ ይቀንስልኝ ነበር ብዬ አስባለሁ።”

ሶሪያ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር ፎቶ ማንሳት መቀጠል ይፈልጋል።

“በጎውንም መጥፎውንም ሁሉም ሰው እንዲያየው እፈልጋለሁ። እንደእኔ ምርጫ ቢሆን በሰላማዊ አካባቢ የዱር እንስሳትን ፎቶ አነሳ ነበር። ስዊትዘርላንድ መሄድ እመኛለሁ። ሰላምና ጸጥታው ያስፈልገኛል” ይላል አቡድ።