ቱርክ የአል ባግዳዲን እህት ያዝኩ አለች

የቀድሞው የአይ ኤስ መሪ አቡ ባካር አል ባግዳዲ እህት በሰሜናዊ ሶርያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የቱርክ ባለሥልጣኖች አሳወቁ።

የ65 ዓመቷ አዛውንት ራስሚያ አዋድ የተያዙት ሰኞ ዕለት አዛዝ በተባለ ከተማ በተካሄደ አሰሳ እንደነበርም ተገልጿል።

የቱርክ ባለሥልጣኞች ከአል ባግዳዲ እህት ስለ አይ ኤስ ጠቃሚ መረጃ ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

ባለሥልጣናቱ ራስሚያን በመጠቀም ስለ አይ ኤስ ውስጣዊ አሠራር ለማወቅ እንዳለሙ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

አል ባግዳዲ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በሚገኘው መኖሪያው በአሜሪካ ልዩ ኃይሎች መከበቡን ተከትሎ ራሱን ማጥፋቱ ይታወሳል። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአልባግዳዲ ሞት ቢኩራሩም፤ አይ ኤስ በሶሪያና በሌሎችም አገሮች አሁንም የጸጥታ ስጋት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት የትራምፕ ተቺዎች በአጽንኦት ተናግረዋል።

ስለ አል ባግዳዲ እህት እምብዛም መረጃ የለም። ቢቢሲ የታሠሩትን ሴት ማንነት ለማጣራት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።

በኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ መሰረት አልባግዳዲ አምስት ወንድሞችን ብዙ እህቶች አሉት። ከእነዚህ ምን ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ግልጽ መረጃ የለም።

ራስሚያ አዋድ የተያዙት ከባለቤታቸው፣ ከአምስት ልጆቻቸውና ከልጃቸው ባለቤት ጋር በሚኖሩበት አካባቢ እንደሆነ አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል። ከጽንፈኛ ቡድን ጋር አብረው እንደሚሰሩ ስለሚጠረጠር ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም አክሏል።

ተንታኞች ከራስሚያ ምን ያህል ጠቃሚ መረጃ እንደሚገኝ እንዲሁም ከአል ባግዳዲ ጋር ምን ያህል ጊዜ እንዳሳለፉም ግልጽ መረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።

በሀድሰን ኢንስቲትዮት የሚገኙ የሽብርተኝነት ተመራማሪ ማይክ ፕሬገንት፤ "በቅርብ ጊዜ ሊወሰዱ የታሰቡ ጥቃቶች የምታውቅ አይመስለኝም። ሆኖም አል ባግዳዲ ይተማመንባቸው የነበሩ ሕገ ወጥ ዝውውር የሚካሄድባቸውን መስመሮችን እና ታማኙ የነበሩ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ራስሚያና ቤተሰቦቻቸው ከቦታ ቦታ በሚስጥር ስለሚያዘዋውሩ የአል ባግዳዲ ተባባሪዎች መረጃ ሊገኝ እንደሚችልም ተመራማሪው ተናግረዋል። መጃው ለአሜሪካ የስለላ ሠራተኞች እና አጋሮቻቸው የአይ ኤስን የውስጥ መስመር በግልጽ የሚያሳይ ይሆናል።