ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድሮይድ ስልኮችን እያሸበረ ያለው ፎቶ
በርካታ የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች አንድ ያማረ ተፈጥሮ የሚያሳይ ፎቶ ከጫኑ በኋላ የስልካቸው ስክሪን እየቀባጠረ እንደሆነ በማኅበራዊ ድር-አምባዎቻቸው እያሳወቁ ነው።
ፎቶው ያማረ ነው።
ያማረ ሐይቅ፣ ጉም ሰንጥቆ የሚያበራ የጠዋት ፀሐይ። በፀደይ ወራት የደመቁ የዛፍ ቅርንጫፎች።
ይህን ፎቶ በአንድም ይሁን በሌላ አግኝተው የስልካቸው ግድግዳ ላይ የለጠፉ ሰዎች ግን ቀናቸው እንደ ፎቶው አላማረም። በተለይ ደግሞ ሳምሰንግ እና የጉግል ፒክስል ስልኮች ይህን ፎቶ አታሳዩን እያሉ ነው።
ነገሩ ወዲህ ነው። ይህን ፎቶ የስልክዎ ግድግዳ [ዎልፔፐር] ካደረጉ ስክሪኑ ሲያሻው ይጠፋል፤ ሲያሻው ይበራል። አንዳንድ ስልኮች ደግሞ ያላቸው ፋይል ጠፍቶ እንደ አዲስ ካልተከፈቱ ላይሰሩ ይችላሉ።
ቢቢሲ ይህን ፎቶ ስልክዎ ላይ እንዲጭኑ አይመክርም።
ሳምሰንግ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጥገና አደርጋለሁ ጠብቁኝ ብሏል። ቢቢሲ ጉግልን ምን ልታደርጉ አሰባችሁ ብሎ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
የቴክኖሎጂ ጋዜጠኛው ቦግዳን ፔትሮቫን ምንም እንኳ በፎቶ መልክ የመጣው ቫይረስ የእርሱን ሁዋዌ 20 ፕሮ ስልክ ባያጠቃም ጉግል ፒክስል 2 ስልኩን እንዳመሰቃቀለው ይናገራል።
"የተባለውን ፎቶ የስልኬ ግድግዳ አድርጌ ከለጠፍኩ በኋላ ስልኬ ወዲያውኑ መቀባጠር ጀመረ። ስክሪኑ ይበራል ይጠፋል። ምንም ልጠቀመው አልቻልኩም።"
ስልኩን 'በሴፍ ሞድ' [ስልኩ ከጠፋ በኋላ የመክፈቻ ቁልፉንና የድምፅ መጨሪያውን በጋራ በመጫን] ለመክፈት ያደርጉት ሙከራም አልተሳካም ይላል ጋዜጠኛው።
አንድሮይድ የተሰኘው የሳምሰንግና መሰል ስልኮች አንቀሳቃሽ ሶፍትዌር 11ኛው አዲስ ዘመናዊ ምርት በዚህ ሳምንት ሊለቅ ታስቦ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ሰበበኛ ፎቶ ምክንያት እንዲዘገይ ተደርጓል።
ፎቶው ምን ዓይነት ቫይረስ እንዳዘለ የሚያመለክት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ነገር ግን ኬን ሙንሮ እና ዴቭ ሎጅ የተሰኙት የቴክኖሎጂ ሰዎች ለቢቢሲ እንዲህ ሲሉ ግምታቸውን ያስረዳሉ።
''ፎቶግራፎች ከጊዜ ጊዜ ጥራታቸው እየጨመረ ነው። ስልኮች ፎቶ የሚቀበሉት ሁሉን ነገር አመዛዝነው ነው። እንደየስልኩ ዓይነት የአንድ ፎቶ ቀለማት ሊለያዩ ይችላሉ። አንዳንድ ስልኮች ፎቶው በትክክል ከሚያሳየው ቀለም የተለዩ ቀለማት ሊያንፀባርቁ ይችላሉ። ምናልባት ይህ ፎቶ እና ችግር እየተከሰተባቸው ያሉ ስልኮች የቀለማት አለመጣጣም አጋጥሟቸው ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ስልክ ሊጎዳው ይችላል።''
ተንታኞቹ ይህን ይበሉ እንጂ ፎቶው ስልኮች ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ምን እንደሆነ እስካሁን አልተረጋገጠም።