የኩዌቱ ኢሚር ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-ሳባህ ሆስፒታል መግባታቸው ተነገረ

የኩዌቱ ኢሚር ሼህ ሳባህ አል-አህመድ አል-ሳባህ በጤና እክል በአገሪቱ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጋቸው ተነገረ።

ኢሚሩ ሆስፒታል መግባታቸውን ተከትሎ አልጋ ወራሽ ሼህ ናዋፍ አል-አህመድ አል-ሳባህ በጊዜያዊነት የተለያዩ ኃላፊነቶችን ይዘው ኩዌትን ይመራሉ ተብሏል።

የአገሪቱ መንግሥት የ91 ዓመቱ የኩዌት ኢሚር ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-ሳባህ ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያስነገረ ሲሆን፤ የገጠማቸው የጤና እክል ለክፉ የሚሰጣቸው እንዳልሆነ ጨምሮ ጠቅሷል።

በቴሌቪዥን ጣቢያው በቀረበው ሪፖርት ላይ ኢሚሩ "በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ" ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

ከአንድ ዓመት በፊትም ኢሚሩ የጤና ችግር አጋጥሟቸው እንደነበረ ተነግሯል። ለሥራ ጉብኝት ወደ አሜሪካ አቅንተው ሳሉ ህመም አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደው ነበር።

ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-ሳባህ የባህረ ሰላጤ አገራትን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ይወደሳሉ።

ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-ሳባህ እአአ 2006 ላይ የኩዌት ኢሚር ከመሆናቸው በፊት የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር እና ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ለብዙ ዓመት አገልግለዋል።