ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዜና አንባቢዋ በቀጥታ የቴሊዚዥን ስርጭት ላይ የፊት ጥርሷ ወለቀ
በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ከቴክኒክ ብልሽት ጀምሮ ብዙ ያልታሰቡ እክሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
ዩክሬናዊቷ የቴሌቪዥን ዜና አምባቢ ማሪችካ ፓዳልኮ በዚህ ሳምንት ያጋጠማት ግን የለየ ነገር ነበር። ፓዳለኮ ዜና እያነበበች ሳለ ከፊት ጥርሶቿ መካከል አንዱ ወልቋል።
ይሁን እንጂ ዜና አንባቢዋ በፍጹም እርጋታ ሳትደናገጥ በቀኝ እጇ ጥርሷን ከአፏ አውጥታ በመያዝ ምንም እንዳልተፈጠረ ዜና ማንበቧን ቀጥላለች።
"እውነት ለመናገር የተፈጠረው ነገር ማንም ሰው ሳያስተውለው ያልፋል ብዬ ነበር" ስትል በኢንስታግራም ገጿ ላይ ጽፋለች።
ፓዳልኮ ዜና እያነበበች ሳለ ጥርሷ ሲወልቅ የሚያሳየው ምስል ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት ለመሰራጨት ጊዜ አልወሰደበትም ነበር።
"ተመልካቾች ምን ያህል በአጽንኦ እንደሚመለከቱን አሳንሼ ገምችያለሁ" በማለት ዜና ስታነብ የፊት ጥሯ ሲወልቅ የሚያሳየውን ቪዲዮ አያይዛ በኢንስታግራም ገጿ ላይ አስፍራለች።
ዜና አንባቢዋ ማሪችካ ፓዳልኮ ከ10 ዓመታት በፊት በድንገተኛ አደጋ ሴት ልጇ ጥርሷ ላይ ጉዳት አደርሳባት ህክምና ተደርጎላት እንደነበረም አስታውሳለች።
ምንም እንኳ የቴሌቪዥን ጣቢያው ዜና አምባቢዋ ጥርሷ ሲወልቅ የሚያሳየውን ምስል በዩቲዩብ ላይ ባይጭነውም፤ ማሪችካ ከበርካቶች ያገኘችው ድጋፍ እና ማበረታቸው እንዳስደነቃት ተናግራለች። በዚህም በእራሷ የኢንስታግራም ገጽ ላይ ምስሉን አጋርታለች።
"በየትኛውም አይነት ሁኔታ ውስጥ፤ እርጋታ ያስፈልጋል" ካለች በኋላ ለቀጣዩ ዜና "ነገ ጠዋት እንገናኛለን" ብላለች።