በደቡብ አፍሪካ ሠዓት እላፊ ሲታወጅ የአልኮል ሽያጭ በድጋሚ ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ደቡብ አፍሪካ ከሳምንታት በፊት አንስታው የነበረውን የአልኮል ሽያጭ ክልከላ መልሳ ተግባራዊ ያደረገች ሲሆን የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር አዳዲስ ገደቦችንም ይፋ አድርጋለች።
አሁን በደቡብ አፍሪካ የምሽት የሰዓት ዕላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን በተጨማሪም ከቤት ውጪ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ግዴታ ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዳሉት ለሁለተኛ ጊዜ የተጣለው የአልኮል ሽያጭ ክልከላ በአገሪቱ የጤና አገልግሎት ላይ ያለውን ጫና ይቀንሰዋል።
መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአጠቃላይ በአገሪቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ250 ሺህ ማለፉን ተከትሎ ነው።
በደቡብ አፍሪካ እስካሁን በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አሃዝ ከ4 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን በመንግሥት ግምት እስከ ጥር ወር ድረስ ቁጥሩ እስከ 50 ሺህ ሊደርስ ይችላል ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ውስጥ በበሽታው ክፉኛ የተጠቃች አገር ስትሆን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከዚህ ቀደም ከታየው ሁሉ በበለጠ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳናንቱ ባደረጉት ንግግር አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ በሽታውን ለመከላከል ማድረግ ያለበትን እያከናወነ ሲሆን "አንዳንዶች ግን እራሳቸውንና ሌሎችን ከበሽታው ለመጠበቅ ማድረግ ያለባቸው እየፈጸሙ አይደለም" ሲሉ ወቅሰዋል።
ፕሬዝዳናቱ እንዳስታወቁት አዲስ የተጣሉት እገዳዎች እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ ተግባራዊ ሆነው ይቆያሉ።
ደቡብ አፍሪካ 28 ሺህ የሆስፒታል አልጋዎችን ለኮሮናቫይረስ ህክምና ዝግጁ አድርጋለች። ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ "አሳሳቢ" ያሉት ነርሶችን፣ ዶክተሮችንና የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎችን ጨምሮ 12 ሺህ የሚደርሱ የጤና ባለሙያዎች እጥረት በአገሪቱ እንዳለ ተናግረዋል።
የአልኮል መጠጥ ሽያጭ ክልከላው በድጋሚ ተግባራዊ የሆነው ጸብን፣ የቤት ውስጥ ጥቃትንና የቅዳሜና እሁድ ከልክ ያለፈ የመጠጥ ልማድን ለመቆጣጠር ሲሆን፤ ቀደም ሲል ለሦስት ወራት ተጥሎ የነበረው ተመሳሳይ ዕገዳ የተነሳው ከሳምንታት በፊት ነበር።
ሐኪሞችና ፖሊሶች እንደሚሉት ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው ክልከላ በድንገተኛ ሁኔታ ወደ ሆስፒታል በሚገቡ ሰዎች ቁጥር ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንዲታይ አድርጎ ነበር።
ነገር ግን በአገሪቱ የሚገኙ የቢራና የወይን አምራች ፋብሪካዎች በአልኮል መጠጦች ላይ ተጥሎ የነበረው ክልከላ ከሥራ ውጪ አድርጎናል በማለት ሲያማርሩ ቆይተዋል።


















