የዊል ስሚዝ ባለቤት ስለነበራት የፍቅር ግንኙነት በቀጥታ ስርጭት ላይ ተናገረች

ጃዳ ፒንኬት ስሚዝ ኦውገስት አልሲና ከተሰኘ የራፐ ሙዚቀኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደነበራት በቀጥታ የፌስቡክ ስርጭት ለባለቤቷ ዊል ስሚዝ ይፋ ማድረጓ አነጋጋሪ ሆኗል።

ሬድ ቴብል ቶል በተሰኘው የፌስቡክ ቀጥታ ስርጭቷ ላይ ነው ወ/ሮ ፒንኬት ለባለቤቷ ምስጢሩን የዘረገፈችው።

ነገር ግን፤ ጃዳ ፒንኬት ከአልሲና ጋር ግንኙነት የነበራት ከዊል ስሚዝ ጋር ተቆራርጠው ሳለ እንደነበር ይፋ አድርጋለች።

"ከዚያ በኋላ ተለያይተናል" ስትል ነገሩ በጊዜው እንደተቋጨ አሳውቃለች። "ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ከኦውገስት ጋር የተለየ ግንኙነት ነው ያለን" ብላለች።

"በወቅቱ ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበርኩም። ልቤ ተሰብሮ ነበር" ስትል የነበረችበትን ሁኔታ ገልፃለች።

ዊል እና ጃዳ ፒንኬት ስሚዝ ከአውሮፓውያኑ 1997 ጀምሮ በትዳር ኖረዋል። ሁለት ልጆችም አፍርተዋል። ጥንዶቹ በቅርቡ ተለያይተው እንደገና እንደተጣመሩ ይፋ አድርገው ነበር።

ጥንዶቹ፤ ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ላይ እየተነዙ የተለያዩ አወዛጋቢ ወሬዎችን ለማጥራት ነው ሐቁን ለመናገር የወሰንነው ብለዋል።

የማኅበራዊ ድር-አምባ ተጠቃሚዎች ስለ ጥንዶቹ ትዳር ማውራት የጀመሩት ኦውገስት የተሰኘው 'ራፐር' አንድ የራድዮ ዝግጅት ላይ ቀርቦ ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ከተናገረ ወዲህ ነው።

ኦውገስት አልሲና ከጃዳ ፒንኬት ጋር የነበረውረውን ግንኙነት ዊል ስሚዝ እንደሚያውቅና ይህ ደግሞ ጥንዶቹ በይፋ ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የተዛባ ነገር ፈጥሮ እንደነበር ተናግሯል።

ጃዳ ፒንኬት ስሚዝ የአጭር ጊዜ የፍቅር ጓደኛዋ ኦውገስት ትዳሯ ላይ ችግር እፈጥራለሁ የሚል ስጋት እንነበረው ትናገራለች። ነገር ግን "እኔና አንተ በፈቃደኝነት ስለሆነ የተለያየነው እሱ ምንም አላጠፋም" ስትል ለባለቤቷ ተናግራለች።

ዊል ስሚዝ፤ ምንም እንኳ ተለያይተው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ባለቤቷ ለምን ወደ ሌላ ወንደ እንደሄደች ጠይቋታል።

"በቃ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እፈልግ ነበር" ብላ ስትመለስ ዊል ስሚዝ በመስማማት ፊቱን ሲነቀነቅ በምስሉ ላይ ይታያል።

ጥንዶቹ ወደ ትዳራቸው ከተመለሱ በኋላ ፍቅራቸው "ገደብ የለሽ" መሆኑን ወ/ሮ ስሚዝ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ አስታውቃለች።

በስርጭቱ መጨረሻ ላይ ጥንዶቹ አይበሉባቸው ካገጫጩ በኋላ "አብረን እንጓዛለን፤ አብረን እንሞታለን። ትዳር እስከ መቃብር" ሲሉ ተደምጠዋል።