የሜላንያ ትራምፕ ሃውልት በትውልድ አገሯ ስሎቫንያ ተቃጠለ

ከእንጨት የተሰራው የአሜሪካዊት ቀዳማዊት እመቤት ሜላንያ ትራምፕ ሃውልት በትውልድ አገሯ ስሎቫንያ ከሰሞኑ ተቃጥሏል።

የሃውልቱ ቀራፂ ብራድ ዶውኒይ እንዳለው ሃውልቱን ያቃጠሉት ሰዎች አሜሪካ የነፃነት ቀኔ ነው ብላ የምታከብረውን ክብረ በዓልም ለመቃወም ነው ብሏል።

በበርሊን መቀመጫውን ያደረገው ይህ አርቲስት የሃውልቱን ቀሪ አካልም በነገታው ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ አድርጓል።

ሃውልቱንም ያቃጠሉ ግለሰቦችንም ፖሊስ እየፈለገና ምርመራ መክፈቱንም ሮይተርስ ዘግቧል።

በሃውልቱ መቃጠል ዙሪያ ዋይት ሃውስ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ሃውልቱ በትውልድ ቦታዋ በስሎቫንያ ማዕከል ሰቭኒካ ይገኝ የነበረ ሲሆን ከዛፍ ግንድም ተቀርፆ ነበር የተሰራው።

ሃውልቱ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሰማያዊ ኮት ለብሳ እጆቿን ወደላይ (ወደ ሰማይ) ዘርግታም የሚያሳይ ነው። በባለፈው አመትም ሲተከል ውዝግቦችን አስከትሎ ነበር።

ቀራፂው ለሮይተርስ እንደተናገረው ሃውልቱን ያቃጠሉት ሰዎች "ለምን እና እነማን እንደሆኑ ማወቅ እፈልጋለሁ" ብሏል።

ሃውልቱ በአሜሪካ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በተለይም ስደተኞች ጋር የተያያዘ ፖሊሲን አስመልክቶ ውይይት ይከፍታል የሚል ሃሳብ እንደነበረውም ተናግሯል።

የዩጎዝላቪያ አካል በነበረችው ስሎቫንያ የተወለደችው ሜላንያ ወደ አሜሪካ የተሰደደችውም ከሁለት አስርት አመታት ነበር።

ቀዳማዊት እመቤቷ የፋሽን ሞዴል ነበረች። ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸውንም ተከትሎ የቀዳማዊት እመቤቷ ትውልድ ቦታ የበርካታ ቱሪስቶች መናኸሪያም ሆና ነበር።

በባለፈው አመትም በስሎቫኒያ መዲና ልጁብልጃና የዶናልድ ትራምፕም ከእንጨት የተሰራ ሃውልትም ቆሞ ነበር። እንደ ሜላንያ የትራምፕ ሃውልትም በርካታ ውዝግቦችን የያስነሳ ሲሆን፤ ስምንት ሜትር እርዝማኔ ያለው ይህ ሃውልትም በእሳት የወደመው ከወራት በፊት ነው።