"ለፖሊስ በመደወሌ የጎረቤቴ ልጅ ህይወት ተቀጠፈ"

በቴክሳስ ግዛት ፎርት ወርዝ ከተማ ነዋሪ የሆው ጄምስ ስሚዝ በተቻለ መጠን ከፖሊሶች ጋር ምንም ግንኙነት እንዳይኖረውም ብዙ ጥሯል።

አንዳንድ ጊዜ ግን ያው አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም እና በአንድ ምሽትም ግዴታ ፖሊስ ጋር የሚያስደውለው አጋጣሚ ተፈጠረ።

በጣም መሽቷል ግን ጎረቤቱ ግን በሯ እንደተከፈተ ነው። ምን ሁና ይሆን? በሚል ፖሊስ ጋር ደወለ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ተኩስ ሰማ፤ ቀጥሎም የጎረቤቱ የ28 ዓመት ሴት ልጅ አስከሬን በቃሬዛ ሲወጣ አየ።

በጣም ተረበሸ። ተናደደ፣ ደከመው፣ አመመው፤ ምን እንደሚያስብ ሁሉ ግራ ገባው። ከዚያ በኋላ ማንኛውም ጥቁር ሰው በፖሊስ ሲገደል አታቲና ጄፈርሰንን የተገደለችበትን መጥፎ ጊዜ ያስታውሰዋል።

"ከፀፀት ጋር አብሬ ነው የምኖረው፤ በሚቀጥሉት ዓመታትም መቼም ቢሆን ሊቀለኝ የማይችለውን ሸክም ተሸክሜ ነው የምኖረው፤ እንደ ሰማይ ያህልም ከብዶኛል" በማለትም የሚናገረው ጄምስ ፖሊስ ጋር የደወለበትንም ምሽት ይረግማል።

ጥቅምት 12 ቀን፣ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ተኩል ነበር። የጎረቤቱ በር እንደተከፈተና መብራትም እየበራ ነው ብለው የቀሰቀሱት የእህቱና የወንድሙ ልጆች ናቸው።

ጎረቤቱና የቤቱ ባለቤት ዮላንዳ ካር የልብ ህመምተኛ ስትሆን፤ በቅርብ ጊዜም ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል በተደጋጋሚ ከመግባቷ አንፃር አንድ ነገር ሆና ይሆን በሚልም ተጨነቀ።

ከግቢው ወጥቶ መንገዱ ላይ ሆኖ ሲያይ በግቢዋ ውስጥ የአትክልት መኮትኮቻ ቁሳቁሶቹ በቦታቸው ናቸው፤ ሶኬቶቹም አለመነቀላቸው ግራ አጋብቶት ፖሊስ ደኅንነቷን እንዲያረጋግጥ በሚል ስልክ ደወለ።

ያሰበው ፖሊስ መጥቶ በሩን አንኳኩቶ ቤተሰቡ ደህና መሆናቸውን ይጠይቃል በሚልም ግምት ነበር። ጄምስ ያላወቀው ግን ጎረቤቱ ዮላንዳ በዚያ ምሽት ሆስፒታል ነበረች። እናም ልጇ አታቲያናና የልጅ ልጇ ቪዲዮ እየተጫወቱ እየጠበቋት ነበር።

ፖሊስ ሲደርስም ጄምስ በቤቱ ትዩዩ ቆሞ ነበር።

አሮን ዲን የተባለው አንደኛው ፖሊስ ሽጉጡን አውጥቶ ወደ በሩ ተጠጋ፣ በመቀጠልም ቤቱን በመዞር በአትክልት ስፍራው በኩል በጓሮ በር ወደ መስኮቱ ተጠጋ። ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላ የተኩስ ድምፅ ተሰማ።

"ተኩሱ እንደተሰማም ' እንዳታስመልጣቸው ስትል ድምጿን ሰማሁት" ብሏል ጄምስ።

በመቀጠልም ምን እየተከናወነ እንደሆነም አልገባውም፤ ነገር ግን በርካታ ፖሊሶች መጥተው ጎዳናውን ሞሉት፤ በአካባቢውም ውር ውር ማለት ጀመሩ።

ተኩስ ከሰማ ከስድስት ሰዓታት በኋላ ነው ምን እንደተፈጠረ ያወቀው። የጎረቤቱ ልጅ አታቲያና ጄፈርሰን እንደተገደለችም ተረዳ።

አስከሬኗን በቃሬዛ ይዘውት ወጡ። የጄምስ ቤተሰብና የዮላንዳ ጉርብትና በቅርብ ነው የጀመረው። ዮላንዳ ቤቱን የገዛችው ከአራት ዓመታት በፊት ሲሆን፤ በቤቷም በጣም ነበር የምትኮራው፤ ያለቻትን አጠራቅማ የገዛችው ቤት። የእሷንና የጄምስን ቤትም የሚለየው የአትክልት ቦታና መንገድ ነው።

ጄምስ በሰፈሩ ለረዥም ዘመናት ኖሯል። ልጆቹን እዚህ ነው ያሳደገው፤ የልጅ ልጆቹም እዚሁ ሰፈር ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ አምስት የቤተሰቡ አባላትም እንዲሁ በዚያው አካባቢ ነው የሚኖሩት። ዮላንዳ ለዚህ ሰፈር አዲስ ብትሆንም ከጄምስ ጋር እየተቀራረቡ ነበር።

ጄምስ ዮላንዳን ጠንካራ ሠራተኛ እንደሆነች ይናገራል "በህይወቷ ውስጥ ብዙ ፈተና ቢያጋጥማትም ያንን ተወጥታዋለች። ለዚያም ነው ቤት መግዛቷን እንደ ትልቅ ድል የምታየው" ብሏል። ልጇም አታቲያናም የእናቷን መታመም ተከትሎ ነው ልታስታምማት የመጣችው።

እናቷን እንዲሁም የስምንት ዓመት የወንድሟን ልጅ ከመንከባከብ በተጨማሪ ለህክምና ትምህርት ቤትም የሚሆን ገንዘብ እየቆጠበች ነበር።

ከመገደሏ ጥቂት ቀናት በፊት አካባቢያቸው ባለው መንገድ ላይ የመኪና አደጋ ተከስቶ ነበር። አታቲያናም በሩጫ ልትረዳቸው ከቤት ወጣች፤ እናም አምቡላንሱ እስኪመጣ ድረስ አብራቸው ቆየች በማለትም ቀናነቷን ያስታውሳል።

"ዶክተር የመሆን ህልም ነበራት፤ ያንን እውን ሳታደርግ ተቀጨች" ይላል።

ጄምስ አንዳንድ ጊዜ አትክልታቸውን ይኮተኩትላቸዋል፤ አታቲያናም የሚጠጣ ውሃ አምጥታ ይጫዋወቱ ነበር።

የተገደለችበት ዕለት የወንድሟን ልጅ አትክልቶቹን እንዴት መንከባከብ እንዳለበት እያሳየችው ነበር።

ከፖሊስ የተገኘው ቪዲዮ እንደሚያሳየው አሮን ዲን የተባለው ፖሊስ በጓሮ በኩል በሚገኘው መስኮት በኩል ሲሄድ የሚታይ ሲሆን፤ አታቲያናም በመስኮት በኩል ውልብ ስትል ትታያለች።

"እጅ ወደ ላይ፣ እጅሽን አሳይ" በማለት ንግግሩን ሳይጨርስ በመስኮት በኩል ተኮሰ። ፖሊስ ነኝም አላለም።

መሞቷንም ተከትሎ አሮን ዲን ከሥራ ከመባረሩ በፊት በራሱ ለቀቀ። ታህሳስ ወር ላይም በግድያም ወንጀል በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፤ ለአጭር ጊዜም በእስር ላይ ነበር። ነገር ግን የፍርድ ሂደቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዲዘገይ ተደርጓል።

የፎርት ወርዝ ፖሊስ ኃላፊ ኤድ ክራውስ "አታቲያና ጄፈርሰን ህይወቷን ያጣችበት መንገድ ምንም ትርጉም አይሰጥምም" ብለዋል።

ኃላፊው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ዕለት ስሜታዊ ሆነው የታዩ ሲሆን የአታቲያና አሟሟትም በፖሊስና በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ድልድይ አፍርሶታል ብለዋል። ለጄምስ ግን ኃላፈው ያሉትም ትርጉም ሊሰጠው አልቻለም፤ በሕግ አስከባሪዎች ላይ የነበረውን ጥቂት እምነቱንም አጥቶታል።

"ከፖሊስ ጋር ጥሩ ግንኙነት የለንም፤ ምክንያቱም አናምናቸውም። በጭራሽ የማንገናኝም ከሆነ በህይወት የመቆየት እድላችን ከፍተኛ ነው" ይላል ጄምስ።

ጄምስ ከዚህ ክስተት በኋላ ተአምር ቢፈጠር ፖሊስ ጋር እንደማይደውል ያውቀዋል። በቅርቡ እህቱ በሰፈራቸው ውስጥ የተኩስ ድምፅ ሰምታ ፖሊስ ጋር ደውል ብትለውም እምቢ ብሏል።

"ጥቁር ካልሆንክ ነገሩን አትረዳውም" የሚለው ጄምስ በቅርቡም ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ሲያቅፉ፣ ሲንበረከኩ ቢያይም ቲያትር እንደሆነ ነው የተረዳው።

ለአስርት ዓመታትም እንዲሁ ፖሊሶች ሲያስመስሉ መቆየታቸውንም ይናገራል። በተለይም የጎረቤቱን ልጅ ከገደላት ፖሊስ ጋር ተያይዞ ያለው የፍርድ ሂደትም በርካታ ጥያቄዎችን ያጭሩበታል። የአይን እማኝ ቢሆንም ሊያናግረው የመጣ ሰው የለም።

አሟሟቷ ለሚዲያ ይፋ ባይሆን ኖሮ ምርመራ እንደማይጀመርም ተረድቷል። ያለው የፍርድ ሂደትም በከፍተኛ ሁኔታ ያናድደዋል።

ወረርሽኙን እንደ ምክንያት በመጠቀም የፍርድ ሂደቱ ለሚቀጥለው ዓመት የተራዘመ ሲሆን በወንጀል የተጠረጠረው ሰው ጥቁር ቢሆን ኖሮ፤ ክስ እንደሚመሰረትበት እንዲሁም የፍርድ ሂደቱም እንደሚፋጠን ምንም ጥርጣሬ የለውም። "ትንፋሻችንን እንደያዝን ነው፤ መተንፈስ አልቻልንም" ይላል።

በዓመታት ውስጥ በርካታ ፖሊሶች ብዙ ሰዎችን መግደላቸውን እንዲሁም ማቁሰላቸውን የተለያዩ ተቋማትና ተመራማሪዎች በአብዛኛው ከሚዲያ ከሚገኙ ሪፖርቶች መረጃ ሰብስበዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 'ማፒንግ ፖሊስ ቫዮለንስ' በተባለው ድርጅት በባለፈው ዓመት ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ 24 በመቶ ጥቁሮች ሲሆኑ፤ የጥቁሮች የሕዝብ ቁጥርም አስራ ሦስት በመቶ ብቻ ነው። ሌሎች መረጃዎችም እንደሚያሳዩት ከሌሎች ዘሮች በበለጠ ጥቁሮች በፖሊስ ሊተኮስባቸው እንዲሁም ሊገደሉ ይችላሉ።

ግድያ የፈፀሙ ፖሊሶ መከሰስም የተለመደ አይደለም። ድርጅቱ በጎርጎሳውያኑ 2013- 2019 ባለው ጊዜ 7 ሺህ 500 የሚሆኑ ሰዎች በፖሊስ ተተኩሶባቸዋል ወይም ተድለዋል ይላል። ከእነዚህም ውስጥ 71ዱ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን 23ቱ ብቻ ናቸው የተፈረደባቸው።

ጄምስም ስለ ጎረቤቱ ግድያ ለማውራት በቴሌቪዥን በቀረበበት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ያነሰ የሕዝብ ቁጥር ባለባት ፎርት ወርዝ ባለፈው ዓመት ብቻ ሰባት ሰዎች በፖሊስ መገደላቸውን ተረድቷል።

የጆርጅ ፍሎይድ ግድያንም ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ አንዳንድ አሰቃቂ ታሪኮች ለሕዝብ ይፋ ሆነዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት ክርስቶፈር ሎው የተባለው አጎቷ እንዴት በሁለት ፖሊስ ኃላፊዎች እንደተገደለ ቲፋኒ በንተን የተባለች ጥቁር ፖሊስ ተናግራለች።

ከፖሊስ የተገኘው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ክርስቶፈርን እየጎተቱ ይወስዱታል። ለማየት በሚረብሸው ቪዲዮ ላይ ክርስቶፈር ለመራመድም ሆነ ለመቆም ሲታገል ይታያል።

"አሞኛል፤ መተንፈስ አልቻልኩም፤ እየሞትኩ ነው" ቢላቸውም ፖሊሶቹ ሐዘኔታ አልነበራቸውም። አንደኛው ፖሊስም "ምራቅህ ቢነካኝ ከጭቃው ጋር ነው የማደባይህ" ሲልም ይሰማል።

ከአስራ ሦስት ደቂቃ በኋላም ክርስቶፈር መኪናው ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል። ቲፋኒ አጎቷ አሞኛል እያለ ሲማፀን ፖሊሶቹ አምቡላንስ ቢጠሩ ሞቱን ማስቀረት ይቻል እንደነበርም ታምናለች። ከግድያውም ጋር ተያይዞ አምስት ፖሊሶች ቢባረሩም ሁለቱ ከዓመት በኋላ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል።

አታቲያና ከሞተች ከሁለት ሳምንታት በኋላ አባቷ ማርክስ ጄፈርሰን በልብ ድካም ሞተ። የአታቲያና አጎት ሐዘን ወንድሙን ሐዘን እንደገደለው ያምናል።

እናቷም ዮላንዳ ካር ታማ ሆስፒታል ስለነበረች ልጇን መቅበር አልቻለችም። ከሆስፒታልም ከወጣች በኋላ የልጇን ምስል ያለበት ቲሸርት ለብሳ፣ ልቧም በሐዘን ተሰብሮ ጄምስ አግኝቷት ነበር።

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ የፎርት ወርዝ ከንቲባ ቤትሲ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ የጆርጅን ስም በመጥቀስ ሐዘናቸውን የገለፁ ሲሆን የአታቲያናን ስም ሳይጠቅሱ በማለፋቸው ጄምስን በጣም ነው ያሳዘነው።

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ ተቃውሞ ቢቀጣጠልም ለምን የአታቲያና ሞትስ ተቃውሞን እንዳላነሳሳ ይጠይቃል። "ዝም ባልን ቁጥር መረሳቷ አይቀርም፤ እንድትረሳ አልፈልግም" ይላል።

የአታቲያናንም ህይወት ለመዘከር እህቶቿና ወንድሞቿ በስሟ አንድ ፋውንዴሽን አቋቁመዋል።

ፋውንዴሽኑ ትምህርት ላይ የሚያተኩር ሲሆን የተገደለችበት ቤትም እንደ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። የፖስታ ቤት ሠራተኛ የሆነው ጄምስ ቤቱ በልጆቹ የዲግሪና የማስተርስ ምርቃት ፎቶዎች ያሸበረቀ ነው። በርካታ መልካም ነገሮችን ያየበት ቤቱ እንዲሁም ሰፈሩ ነው።

ዮላንዳም ብትሆን ከነርስነቷ ከምታገኘው ደመወዝ ልጆቿን አስተምራለች። የተደላደለ ህይወትም ለመኖር አቅዳም ነበር፤ ሳይሆን ቀርቶ ልጇን አጣች። ለዮላንዳ ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ለኖረው ጄምስም ሰፈሩ ሞትን ያስታውሰዋል። የአታትያና ሞት ከጭንቅላቱ ሊጠፋ አልቻለም። የተኩሱ ድምፅ በጭንቅላቱ ውስጥ ይሰማዋል።

በአሜሪካ ውስጥ በጥቁሮች ላይ የሚፈጸም ኢ-ፍትሃዊነት አዲስ ነገር አይደለም።

ሮበርት ጆንስ በጎርጎሳውያኑ 1992 በኒው ኦርሊያንስ ውስጥ እንግሊዛዊ ቱሪስቶችን ገድለሃል በሚል ወንጀል ተከሰሰ።

ከአራት ዓመታት በኋላ የፍርድ ሂደቱ የተካሄደ ሲሆን በዚህም ወቅት ሌላ ግለሰብ በወንጀሉ ቢፈረድበትም ሮበርት ጆንስም በተመሳሳይ ወንጀል እንዲሁ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት። ንፁህ ቢሆንም ለሃያ ሦስት ዓመታት ያህል በእስር ቆይቷል።

የፈረዱበት ዳኛ በቅርቡም የቆዳው ቀለም የህይወቱን መጥፎ እጣ ፈንታ ወስኖለታል ሲሉ ተሰምተዋል።