አሜሪካ፡ "እኔ ብሆንስ?" የፍሎይድ ሞት የቀሰቀሰው የአፍሪካ አሜሪካዊያን ምሬት

"ትንፋሽ እያጠረኝ ነው። እባክህ ከአንገቴ ላይ ተነስ። መተንፈስ አልቻልኩም" ጆርጅ ፍሎይድ የተሰኘው ጥቁር አሜሪካዊ ያሰማቸው የመጨረሻ ቃላት።

ከዚህ ክስተት በኋላ ሚኒያፖሊስ በተሰኘችው ከተማ ተቃውሞ ደርቶባታል። 'የጥቁር ሕዝቦች ሕይወት ዋጋ አለው'፤ 'መተንፈስ አልቻልኩም'፤ 'ዘረኝነት ይብቃ' እና መሰል መፈክሮችን ያነገቡ አሜሪካውያን ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። ለምን?

የ46 ዓመቱ ጆርጅ ፍሎይድ ዕለተ ሰኞ ነው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዳለ ሕይወቱ ያለፈው። ግለሰቡ የጦር መሳሪያ አልያዘም። ጩቤም ሆነ ዱላ እጁ ላይ አይታይም። ነገር ግን በነጭ አሜሪካውያን ፖሊሶች ተከቧል።

አንደኛው ፖሊስ ፍሎይድን አስተኝቶ በጉልበቱ አንገቱ ላይ ቆሟል። ይሄኔ ነው ፍሎይድ "ትንፋሽ እያጠረኝ ነው። እባክህ ከአንገቴ ላይ ተነስ። መተንፈስ አልቻልኩም" ሲል መማጸን የጀመረው።

ጩኸቱ ግን ሰሚ አላገኘም።

ይህ ሁሉ ሲሆን ታድያ የዓይን እማኞች ሁኔታውን በስልካቸው ካሜራ ይቀርፁ ነበር። በሥፍራው የነበሩ ሰዎች በስልካቸው ያስቀሯቸው ቪድዮች በስፋት ከተሰራጩ በኋላ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ አራት ፖሊሶች ከሥራቸው እንዲታገዱ ተደርገዋል። የሚኒያፖሊስ ከንቲባም አደባባይ ወጥተው 'ጥቁር መሆን የሞት ቅጣት መሆን የለበትም' ሲሉ ተደምጠዋል።

አራቱ ፖሊሶች ወደ ሥፍራው የመጡት የሐሰተኛ ገንዘብ እንቅስቃሴ ተስተውሏል የሚል ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ነው። ፖሊስ እንደሚለው ፍሎይድ ከፖሊስ መኪና ገሸሽ እንዲል ቢጠየቅም እምቢኝ ብሏል፤ ይሄኔ ነው በቁጥጥር ሥር ልናውለው የተገደድነው ብለዋል።

ምንም እንኳ በዓይን እማኞች የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፖሊስ ግለሰቡን እንዴት አድርጎ በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው ባያሳዩም፤ ፍሎይድ ከመሬት ተጣብቆ ሕይወቱን ለማዳን ፖሊስን ሲማፀን ግን ያሳያሉ።

መንገደኞች ፖሊስ ከጥቁር አሜሪካዊው አንገት ላይ እንዲነሳ ሲማፀኑም ይሰማል። ፍሎይድ ግን "ትንፋሽ እያጠረኝ ነው"፤ "እባክህ አትግደለኝ" ከማለት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም።

የፍሎይድ ልመና ያልበገረው ፖሊስ የግለሰቡ አንገት ላይ ቆሞ መንገደኞችን ሥፍራውን ለቀው እንዲሄዱ ያዛል። በመሃል ፍሎይድ መንፈራገጥ አቆመ፤ አምቡላንስም ተጠራ። ነገር ግን ፍሎይድ እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ። የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ሰለባም ሆነ።

የአሜሪካ ወንጀል መርማሪ ተቋም ኤፍቢአይ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው 'እኔ ነኝ ገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያዘዝኩት' ይላሉ። ነገር ግን አገራቸው ጥቁር ሰው በሰቀቀን የሚኖርባት ሆናለች።

አሜሪካ ምድረ ገነት አይደለችም፤ አሜሪካ የእኩልነት መገለጫ አይደለችም፤ አሜሪካ ነፃነት የሚታፈስባት አይደለችም፤ በተለይ ደግሞ ቆዳው ለጠቆረ ሰው ይላሉ ይህ መሰል ድርጊት ደጋግሞ የገጠማቸው አፍሪካ አሜሪካዊያን።

እርግጥ ነው በርካቶች ሕይወታቸውን የቀየሩባት ናት፤ ልዕለ ኃይልነቷም የሚካድ አይደለም። አሜሪካ ስታስነጥስ የተቀረው ዓለም 'ይማርሽ' የሚለው ወዶ አይደለም። ነገር ግን አሜሪካ ቆዳ ትለያለች። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰቱት የጥቁር አሜሪካውያን ግድያዎች ለዚህ ምስክር ናቸውም ይላሉ።

ጥቁር አሜሪካውያን የፖሊስ ጭካኔ ሰለባ ሲሆኑ ፍሎይድ የመጀመሪያው አይደለም፤ የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው። ከዊል ስሚዝ እስከ ጄሚ ፎክስ፣ ቢዮንሴ፣ ጀስቲን ቢበር፣ ከካርዲ ቢ እስከ ወጣቱ ጥቁር እንግሊዛዊ ተዋናይ ጆን ቦዬጋ ምሬታቸውን አሰምተዋል።

ጥቁሮች ላይ የሚደርሰው ዘረኝነት ይብቃ ብለዋል። ዊል ስሚዝ በአንድ ወቅት ያለውን ልብ ይሏል፡ 'ዘረኝነት አሜሪካ ውስጥ ተፋፍሟል ብላችሁ እንዳትታለሉ፤ በተንቃሳቀሽ ስልክ ምክንያት የአደባባይ ምስጢር ሆነ እንጂ ሁሌም ነበር።'

የፍሎይድ መገደል ያስቆጣቸው አሜሪካውያን ሚኒያፖሊስን በእሳት አጋይተዋታል። ሱቆች ተዘርፈዋል፤ ሕንፃዎች ተቃጥለዋል። ፍትህ ለፍሎይድ የሚል መፈክር የያዙ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፤ የአስለቃሽ ጭስ ሲሳይ ሆነዋል።

ተቃውሞውን የሚያስተባብሩ ሰዎች፤ በሺህ የሚቆጠሩት ሰልፈኞች ሰላማዊ እንዲሆኑና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ርቀታቸው እንዲጠብቁ ቢመክሩም ሰሚ አላገኙም።

ሲቢኤስ የተሰኘው ቴሌቪዥን ጣብያ ላይ የቀረበ አንድ ሰልፈኛ "በጣም አስቀያሚ ነው። ፖሊሶች ኑሯችንን ምንኛ እያከበዱት እንዳለ ሊያውቁት ይገባል" ሲል ተደምጧል።

ሚኒያፖሊስ በርካታ ጥቁሮች የሚኖሩባት ከተማ ናት። በኢትዮጵያዊያንም ዘንድ ታዋቂ ናት። ለዚህም ይመስላል ነዋሪነታቸውን አሜረካ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በማኅበራዊ ድር-አምባዎች ድምፃቸው እያሰሙ የሚገኙት።

ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚሰማው ድምፅ ግን "እኔ ብሆንስ?" የሚለው ነው። ለጥቁር አሜሪካውያን እኒህ ሁለቱ ቃላት ትልቅ ትርጉም አላቸው።

አሜሪካ፤ ከዘመነ ማልኮም ኤክስ፤ ተቃውሞን በእንብርክክ እያሰማ እስካለው ካፐርኒክ ለጥቁሮች ጆሮ ለመስጠት ዳድታለች። የቆዳዎ ቀለም እንደኔ ከሆነ ነገ የፖሊስ ጭካኔ ሰለባ ላለመሆንም ምንም ማስረገጫ የለም። "እኔ ብሆንስ?" ማለት ይሄኔ አይደል?