ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስደተኞች ጉዳይ የዶናልድ ትራምፕን ሐሳብ ውድቅ አደረገ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወጣት ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ያቀደውን የዶናልድ ትራምፕ ሐሳብ የሚቃረን ውሳኔን አስተላልፏል።
በምህጻር ቃሉ "ዳካ" የሚባለው ፕሮግራም የተነደፈው በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሲሆን በልጅነታቸው ከሌላ አገር ወደ አሜሪካ የመጡ ልጆች፣ አዳጊዎችና ወጣቶችን ከአሜሪካ እንዳይባረሩ ከለላ የሚሰጥ ልዩ ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔ ነበር።
ይህን በኦባማ የተፈረመውን ልዩ ውሳኔ ሕገ ወጥ ነው በሚል እንዲሻር ዶናልድ ትራምፕ ትግል ሲያደርጉ ከርመዋል።
የታችኛው ፍርድ ቤት የዶናልድ ትራምፕን እቅድ ውድቅ በማድረጉ ጉዳዩን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲመለከተው ቆይቷል።
በትናንቱ ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለረዥም ጊዜ ካጤነው በኋላ 5 ለ 4 በሆነ ድምጽ የዶናልድ ትራምፕን ሐሳብ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ይህ ውሳኔ በልጅነታቸው ወደ አሜሪካ የመጡ በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞችን አስፈንድቋል።
'ዳካ' ምንድነው?
'ዳካ' ምህጻረ ቃል ሲሆን 'ዲፈርድ አክሽን ፎር ቻይልድሁድ አራይቫል' የሚል የፕሬዝዳንቱን መመሪያን የያዘ ሰነድ ነው።
ይህ መመሪያ በአሜሪካ ሕግ የፕሬዝዳንቱ ልዩ መመሪያ ሆኖ እስከ ታች ባሉ በሁሉም የሕግ አስፈጻሚው አካላት እንዲፈጸም የሚጠበቅ ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በተለምዶ "ሕልመኞች" የሚባሉና በልጅነታቸው ያለ ምንም ሕጋዊ ሰነድ የአሜሪካ ምድርን የረገጡ ስደተኞችን ፖሊስ ከአገር እንዳያባርራቸው የሚከለክል ልዩ መመሪያን አጽድቀውላቸዋል።
ይህ ልዩ መመሪያ ነው 'ዳካ' በመባል የሚጠራው።
በዚህ ፕሮግራም የሚካተቱት አብዛኞቹ ወጣት ስደተኞች ከሜክሲኮና ከላቲን አሜሪካ አገራት ያለ ምንም ሰነድ ወደ አሜሪካ ምድር የገቡ ናቸው።
በ2012 ኦባማ እነዚህ ሕልመኛ ወጣቶች ከአገር እንዳይባረሩ ማድረግ ብቻም ሳይሆን እንዲማሩና እንዲሰሩም ፈቅደውላቸዋል።
ኦባማ በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩ ፕሬዝዳንታዊ መመሪያ ለመፈረም የተገደዱት የስደተኞቹን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊመልስ የሚችል ማሻሻያ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ሊጸድቅላቸው ባለመቻሉ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣቸውን ተከትሎ ይህን በኦባማ የተፈረመውን ልዩ መመሪያ ለመሻርና ሕገ ወጥ ለማሰኘት ብሎም ስደተኞችን በሙሉ ጠራርጎ ከአገር ለማስወጣት በመፈለጋቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሊሄድ ችሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህን መመሪያ ሕገ ወጥ መሆኑን በፍርድ ቤት ቢያስወስኑ ኖሮ 650 ሺህ በአሜሪካ እየኖሩ ያሉ ልጆች፣ አዳጊዎችና ወጣቶች በፍጥነት ከአገር እንዲወጡ ይደረግ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተበሳጩ ሲሆን ደጋፊዎቻቸውን በድጋሚ ከመረጣችሁኝ ወግ አጥባቂ ዳኞችን እሾማለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።
"ይህ የማይረባና በፖለቲካ የተለወሰው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ራሳቸውን በኩራት ሪፐብሊካን በሚሉ አሜሪካዊያን ግንባር ላይ የተተኮሰ ጥይት ነው" ብለዋል በትዊተር ሰሌዳቸው።
በመጪው ኅዳር በድጋሚ ከመረጣችሁኝ የእኛን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ወግ አጥባቂ ዳኞችን በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ እሾማለሁ ብለዋል።
"የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እንደማይወዱኝ አያችሁልኝ አይደል?" ሲሉም ጽፈዋል ትራምፕ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ "ይበል የሚያሰኝ" ሲሉ አሞካሽተዋል።
ለደጋፊዎቻቸውም ዶናልድ ትራምፕን በመጪው ኅዳር ከዋይት ሐውስ አባረው አሜሪካንን የሚመጥናት የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ እንዲመርጡ ጥሪ አድርገዋል።
የትራምፕ ተፎካካሪ ጆ ባይደን በበኩላቸው ከተመረጡ 'ዳካ' ፕሮግራምን ቋሚ እንደሚያደርጉት ቃል ገብተዋል።