ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ፖሊሶች ነፍስ አጥፍተው የማይከሰሱት ለምንድነው?
አሜሪካ ውስጥ "ሰማይ አይታረስ፣ ፖሊስ አይከሰስ" የሚል አባባል ቢኖር ተገቢ ይመስላል። በዚያ አገር ፖሊስ አልፎ አልፎ ካልሆነ ነፍስ በእጁ አጥፍቶም አይከሰስም የሚለው ስሞታ በስፋት ይነገራል።
እርግጥ ነው ቁጣን የቀሰቀሰው የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ይለይ ይሆናል።
ተጠርጣሪው ነጭ ፖሊስ ዴሪክም ተከሷል፤ አብረውት የነበሩት ሌሎች ሦስት ፖሊሶችም ከብዙ ውትወታና ተቃውሞ በኋላ እንዲሁ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ይህ ማለት ግን አብዛኞቹ ጥቁር አሜሪካዊያን ተስፋ እንደሚያደርጉት በግድያው የተከሰሱት ፖሊሶች ጥፋተኛ ሆነው ከባድ ቅጣት ይቀምሳሉ ማለት ላይሆን ይችላል።
የጆርጅ ፍሎይድ የመጨረሻዎች ደቂቃዎች በቪዲዮ ተቀረጹ እንጂ ክስተቱ ለአሜሪካ ብርቅ አይደለም።
በአሜሪካ በየዓመቱ ብዙ ንጹሐን ዜጎች በፖሊስ ይገደላሉ። ሟቾቹ ደግሞ በብዛት ጥቁሮችና ስፖኒሾች ናቸው።
በአመዛኙ ገዳይ ፖሊሶች ከሥራ ይባረሩ ይሆናል እንጂ መደበኛ ክስ ተከፍቶባቸው ይፈርድባቸዋል ለማለት ያስቸግራል።
አሐዞች የሚመሰክሩትም ይህንኑ ነው።
በአሜሪካ በየዓመቱ በአማካይ 1200 ዜጎች በፖሊሶች ይገደላሉ።
ከእነዚህ ግድያዎች ውስጥ ታዲያ 99 ከመቶ የሚሆኑት ገዳይ ፖሊሶቹ ጭራሽ ክስ እንኳ ሳይቀርብባቸው፤ የፍርድ ቤት ደጅ እንኳ ሳይረግጡ ነው የሚታለፉት። ለምን?
ኳሊፋይድ ኢሚዩኒቲ፡ ለአሜሪካ ፖሊሶች ከለላ የሚሰጠው ሕግ
በአሜሪካ ሕግ ጸጥታ አስከባሪዎች ከወንጀል ክስም ሆነ ከፍትሐ ብሔር ክስ የሚጠብቃቸው ፍጹም ልዩ የሆነ የሕግ ከለላ አላቸው። በማስረጃ እናስደግፈው።
የፖሊስ እርምጃዎችን በመመዝገብ የሚታወቀው ማፒንግ ፖሊስ ቫዮለንስ ፕሮጀክት ከ2013 እስከ 2019 ድረስ በፖሊሶች የተገደሉ 7 ሺህ 666 አሜሪካዊያንንና አገዳደላቸውን ሰንዷል።
ከእነዚህ ውስጥ ታዲያ በፖሊስ ክስ የተመሰረተባቸው 99 ፋይሎች ብቻ ናቸው። ይህም ከጠቅላላው 1.3 በመቶው ብቻ መሆኑ ነው።
የሚገርመው ከእነዚህ 7 ሺህ 666 ግድያዎች ውስጥ ፖሊስ ላይ ክስ ተመስርቶ የጸጥታ ኃይል አባል አጥፊ ተደርጎ ፍርድ የተሰጠው በ25 ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው።
ይህም ማለት በእነዚህ ዓመታት ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያለው የፖሊስ ቁጥር 25 ብቻ ነው ማለት ነው።
በዋሺንግተን ካቶ ኢንስቲትዩት የወንጀል ጉዳዮች ጥናት ቡድን ምክትል ፕሬዝዳንት ክላርክ ኔይሊ እንደሚሉት ፖሊሶችን በወንጀል የመክሰስ እድሉ ጠባብ ስለሆነ አብዛኛዎቹ ክሶች የወንጀል ሳይሆኑ የካሳ ጥያቄዎች ለመሆን ተገደዋል።
ለፍትሐ ብሔር የካሳ ክስም ቢሆን አብዛኞቹ ፍርድ ቤቶች በራቸው ዝግ ነው የሚሉት ሚስተር ክላርክ ይህም የሆነው በአሜሪካ ኳሊፋይድ ኢሚዩኒቲ (Qualified Immunity Doctrine) የሚባል ነገር በመኖሩ ነው።
ኳሊፋይድ ኢሙዩኒቲ የሕግ አስከባሪዎች የሰዎችን መብት ቢገፉም እንኳ ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ልዩ መብት ነው።
ይህ መብት ሊነሳ የሚችለው ተጎጂው በፍጹም በማያሻማ ሁኔታ ፍርድ ቤትን ሊያሳምን የሚችል ግፍና ጥፋት በፖሊስ ሆን ተብሎ እንደተፈጸመበት ማስረዳት ሲችል ብቻ ነው።
ሚስተር ክላርክ ይህ ለተጎጂዎች ተገቢ ካሳ እንኳ ሊያስገኝ የሚችለውን የፍትሐ ብሔር ክስ ለመመስረትና ፍርድ ለማግኘት እስከዛሬ በታሪክ እንደታየው አስቸጋሪና ሩቅ ብቻም ሳይሆን የማይታሰብ ነው።
ለጊዜው ሁለት ምሳሌዎችን እንውሰድ።
በገዛ ቤቷ ገብቶ ሕጻን ልጇ ላይ የተኮሰው ፖሊስ
በ2014 አንድ ፖሊስ አሚ ኮርቢት የተባለች እናት ግቢ ውስጥ ዘሎ ይገባል። ወንጀለኛ እያሳደደ ነበር።
ስድስት ልጆቿ በግቢ ውስጥ እየተጫወቱ ፖሊሱ ሽጉጡን እንደደቀነ ሁሉም መሬት ላይ በሆዳቸው እንዲተኙ አዘዘ። ልጆቿም ይህንን አደረጉ።
በዚህ መሀል ብሩስ እያለች የምትጠራው ውሻዋ ድንገት ዘሎ በዚህ ውጥረት መሀል ገባ። ፖሊስ ውሻው ላይ አከታትሎ ተኮሰበት።
በኋላ ላይ እንደታየው ውሻው ፖሊሱ ላይ ምንም የደቀነው ስጋት አልነበረም። ብቻ ሁለት ጥይት ተኮሰበት።
ሆኖም ጥይት ውሻውን ሳተው፤ ብሩስ የተባለውን ውሻ የሳተው ጥይት ግን መሬት አላረፈም። ተወርውሮ የአሚን የ10 ዓመት ልጇን እግሩ ላይ መታው። ዳኮታ ይባላል የዚህ ልጇ ስም።
እንደ እድል ሆኖ ዳኮታ በዚያች ጥይት ባይሞትም አካል ጉዳተኛ ሆነ። በዚያ ዕድሜው ላይ በጥይት ሲመታ የደረሰው የሥነ ልቦና ጉዳት ደግሞ ለዘልዓለሙ አብሮት የሚኖር ረቂቅ ቁስል ነው። ለዚህ ፖሊስ ታዲያ ክስ አይገባውም?
እናት ፍርድ ቤት ክስ መሰረተች። ፖሊስ የገዛ ግቢዬ ውስጥ ገብቶ የ10 ዓመት ልጄን ተኩሶ አቁስሎታል ብላ የፍትሐ ብሔር ክስ መሰረተች። ፖሊስ ላይ የወንጀል ክስ የማይታሰብ ነው ብለናል።
ፍርድ ቤት ክሷን ውድቅ አደረገው።
የ8 ወር እርጉዝ ሆና አስፋልት ለአስፋልት በፖሊስ የተጎተተችው ማላይካ
ማላይካ ብሩክስ እርጉዝ ነበረች። ፖሊስ በድንገት ሦስት ጊዜ በፖሊስ ማደንዘዥ ዱላ ገረፋት፣ ከመኪናዋ ጎትቶ አስፋልት ላይ ጣላት፣ ከዚያ ጭንቅላቷን ቁልቁል ደፍቶ የፊጥኝ አሰራት።
ይህ ሁሉ ሲሆን የ11 ዓመት ልጇ ቆሞ ይመከለት ነበር።
እርሷም የ8 ወር ነፍሰ ጡር ነበረች።
ይህን ሁሉ የተደረገቸው ከተገቢው ፍጥነት በላይ መኪናሽን አሽከርክረሻል ተብላ ነው። እርሷም የክስ ወረቀት ለመውሰድ ፍቃደኛ አልሆነችም። የክስ ወረቀት ከወሰደች ለጥፋተኝነቷ ማስረጃ ተደርጎ እንዳይቀርብባት ሰግታለች።
ኋላ ላይ ለደረሰባት ግፍና እንግልት ፖሊሱን ፍርድ ቤት ከሰሰችው። ፍርድ ቤቱም ክሷን ውድቅ አደረገው።
ማላይካ ከስንትና ስንት እንግልት በኋላ፤ 10 ዓመት መንከራተት በኋላ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጪ የ45 ሺህ ዶላር ካሳ ስምምነት አድርጋ ጉዳዩ በዚሁ ተቋጨ።
ሚስተር ክላርክ እንደሚሉት ፍርድ ቤት በፖሊስ ላይ የሚመሰረትን ክስ ወደ ፊት ለመውሰድ እጅግ ግልጽ የሆነና የማያሻማ ጥፋት መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃን ይሻል። ያ ማስረጃ ከሌለ ፖሊስ ምንም ዓይነት ጥፋት ቢሰራ እጅ በኪስ አድርጎ ከፍርድ ቤት አዳራሽ ይወጣል።
የጆርጅ ፍሎይድ ገዳይ ይፈረድበት ይሆን?
ሚስተር ክላርክ እንደሚሉት ለፖሊስ በሕግ የተሰጠው ልዩ መብት "ኳሊፋይድ ኢሙኒቲ" (Qualified immunity) የሟች ጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦች ተገቢውን ፍትህ እንዳያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል።
"ኳሊፋይድ ኢሚይኒቲ" ቀደም ሲል እንዳብራራነው በአሜሪካ የጸጥታ አስከባሪዎች ሕግን ለማስከበር ሲሉ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ተጠያቂነት ሊመጣባቸው አይገባም ሲል የሚደነግግና ለፖሊሶች ከለላ የሚሰጥ ልዩ መብት ነው።
ፖሊሶቹ ተጠያቂ የሚሆኑት በግልጽ የተቀመጡ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን በማያሻማ ሁኔታ ጥሰው ሲገኙ ብቻ ነው።
"የጆርጅ ፍሎይድ ጠበቆች አንድ ነገር ካገኙ ብቻ ክሳቸው ዋጋ ያገኛል" ይላሉ ሚስተር ክላርክ።
". . . ይኸውም ከዚህ በፊት በፍርድ ቤት የተወሰነ ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ ፍርድ የተሰጠበት ጉዳይ ካለ. . . ማለትም አንድ ፖሊስ አንድ ተጠርጣሪ ላይ አንገቱ ላይ ቆሞ ትንፋሹ እስኪቆም ድረስ አፍኖ መግደሉ ሕጋዊ አይደለም" የሚል ውሳኔ ካላገኙ በስተቀር ክሱ ውድቅ ይሆንባቸዋል።
ለምን ቢባል ፍርድ ቤቱ የኳሊፋይድ ኢሚዩኒቲ መርህን በመጥቀስ "እንዲህ ያለ ክስ የጸጥታ አስከባሪዎች ተከሰውበት አያውቁም፤ ስለዚህ ፖሊስ ላለመከሰስም ልዩ መብቱን ፍርድ ቤቱ ይጠብቅለታል ብሎ ጉዳዩን ይዘጋዋል" ይላሉ።
የጆርጅ ፍሎይድ ገዳይ ፖሊስ ነጻ ሰው ሆኖ ያለምንም ፍርድ ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ዕድል መኖሩ ለብዙዎች እጅግ አስገራሚ ጉዳይ ነው።
ቢቢሲ ለዚህ ጥንቅር የአሜሪካ ብሔራዊ ፖሊሶች ማኅበርን ሐሳብ ለማካተት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ይህ ጽሑፍ እስኪታተም ድረስ ምላሸ ማግኘት አልቻለም።
ሆኖም የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ማይክል ማኬል ከዚህ ቀደም በዚሁ ጉዳይ እንተናገሩት "ጆርጅ ፍሎይድ ላይ የሆነው ነገር በሕግም፣ በሞራልም፣ ይቅር የሚባል አይደለም።"
የሕግ ማሻሻያ ካልተደረገ ያ ሁሉ ተቃውሞ ውሃ ይበላዋል
ብዙ ዜጎች በተቃውሞና በመፈክር ሕግ ሸብረክ እንደሚል ያስባሉ። ሆኖም የሕግ ማሻሻያና የፍትሕ ሥርዓት ለውጥ እስከሌለ ድረስ ፖሊሶች ያጠፉትን ቢያጠፉም ጥቁሮች እየሞቱ ይቀጥላሉ።
ታዲያ ምን ይደረግ?
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኳሊፋይድ ኢሚዩኒቲ የሚባለውን ለፖሊሶች ከለላ የሚሰጠውን ደንብን የሚረዳበትን መንገድ እንዲቀይር ማድረግ አንዱ መፍትሄ ነው።
የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፒስ አክት (Peace Act) የተሰኘውን ረቂቅ እንዲያጸድቁ እየወተወቱ ነው።
ሕጉ የፖሊስ አካላት እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ የሚጠቀሙት ኃይል ተመጣጣኝ እንዲሆንና ሰላማዊ በሆኑ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ የሚያዝ ነው።
ፖሊሶች የግድ እስካልሆነ ድረስ ሕግን ለማስከበር በሚል ብቻ በሰላማዊ ሁኔታ ያልተመጣጠነ ጉልበት እንዳይጠቀሙ የሚያስገድድ ረቂቅ ነው።
አንዳንድ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ለዚህ ረቂቅ ከወዲሁ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ኦዲ ኦፈር የአሜሪካ ሲቪል ሊበርቲ ዩኒየን ዳይሬክተር ናቸው።
"ሕግ ማውጣት ብቻውንም ምንም የሚፈይደው ነገር የለም" ይላሉ።
በሕግ አስከባሪዎች ዙርያ ያለው አመለካከት በአሜሪካ ካልተለወጠ ችግሩ እንደሚቀጥል ያምናሉ።
ለምሳሌ በአሜሪካ በአንዳንድ ግዛቶች ለፖሊስና ተያያዥ ጉዳዮች የሚወጣው ወጪ የግዛቱን 40 ከመቶ ወጪ ይሸፍናል።
"በዚያ ላይ የታጠቁ ፖሊሶች በአሜሪካ አስፈላጊ ባልሆኑ ቦታዎች ሁሉ ይሰማራሉ፤ ይህ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ለምሳሌ ትምህርት ቤቶች ውስጥና ሥርዓት ያጡ ተማሪዎችን ልክ ለማስገባት ሁሉ ታጣቂ ፖሊስ ይሰማራል።"
በአሜሪካ በየሦስት ሰከንዱ አንድ ሰው በፖሊስ ይታሰራል።
እንደ አሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ መረጃ ከሆነ በ2018 ብቻ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ዜጎች ብዛት 10.3 ሚሊዮን ይሆናሉ። የሚገርመው ከእነዚህ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ ሲሶዎቹ ላይ እንኳ ክስ አይመሰረትም።
ለምሳሌ ጆርጅ ፍሎይድ በቁጥጥር ሥር የዋለውና ለሞት ያበቃው በአንድ መደብር ውስጥ ሐሰተኛ ዶላር ለማስተላለፍ ሞክሯል በሚል ነበር።
ለእንደነዚህ ዓይነት ወንጀሎች የጦር መሣሪያ የታጠቀ ፖሊስ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። "ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለፖሊስና ተያያዥ ወጪዎች መመደብን ጤናማ አይደለም" ይላሉ ኦዲ ኦፈር።
ይልቅ ለፖሊስ የሚወጣው ቢሊየን ዶላር በታሪካዊ ሁኔታዎች የተነሳ ለወንጀል የቀረቡ ናቸው ለሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሰጥቶ ቁም ነገር ቢሰራበት ወንጀል ይቀንሳል።
አሁን በአሜሪካ የተቀጣጠለው ተቃውሞ በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚከስም ይጠበቃል። በጥቁር አሜሪካዊያን ላይ የሚደርሰው በደልስ?
ለዚህም ነው የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ቁጣ ከመብረዱ በፊት ብልህ የመብት ተሟጋቾች ወደ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመራ እየሰሩ የሚገኙት።
ኦዲ ኦፈር እንደሚሉት ግለሰቦችን በመክሰስ የፖሊስን የጭካኔ ወንጀል መቀነስ አይቻልም። ተቃውሞው ሲበርድ ሁሉም ነገር ወደ ቦታው ይመለሳል። ተቃውሞው ተቋማዊና መዋቅራዊ ለውጥ ካላመጣ ከንቱ ድካም ነው።