ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሚኒሶታ የጥቁር አሜሪካዊውን ሞት ተከትሎ ቁጣ ገንፍሏል
በሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ሚኒያፖሊስ ከተማ በነጭ ፖሊስ በግፍ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊ ድርጊት ለመኮነን ሺዎች አደባባይ ወጥተዋል።
ትናንትናና ዛሬ በርካታ ሱቆች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ ቢሮዎች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል፤ አንዳንዶቹም እሳት ነዶባቸዋል።
ለምን ንብረት ታወድማላችሁ በሚል የተጠየቀ አንድ ተቃዋሚ፣
‹‹ምን እንድናደርግ ነው የምትፈልገው? እንዴት ነበር ድርጊቱን መቃወም የነበረብን? እየገደሉን እኮ ነው ያሉት፤ ነገሮች እስኪስተካከሉ ጊዜ ይወስዳሉ ይሉናል፤ ጊዜው አብቅቷል የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን›› ሲል ተናግሯል።
ሰኞ ልብ የሚነካው የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በማኅበራዊ ገጾች ከተሰራጨ በኋላ ከማክሰኞ ጀምሮ የተቃውሞው መጠን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ባለመሄዱ የአሜሪካ ናሽናል ጋርድ (ልዩ ኃይል) ወደ ሚኒያፖሊስ ከተማ እንዲገባና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ተቃውሞዎችን እንዲቆጣጠር ታዟል፡፡
የ46 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ጀርጅ ፍሎይድ ባለፈው ሰኞ ነበር አንድ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ተጭኖት እየተሰቃየ እንዲሞት ያደረገው፡፡
ይህ ለደቂቃዎች በመንገደኞች የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምሥል እንዳስረዳው ጆርጅ ፍሎይድ ፖሊሱን ‹‹እባክህን መተንፈስ አቃተኝ፤ እባክህን አትግደለኝ›› እያለ ሲማጸነው ያሳያል፡፡
ጆርጅ ፍሎይድ በጊዜው የታጠቀው መሣሪያ አልነበረም፡፡
በአሜሪካ የጥቁር ነፍስ ዋጋ ስንት ነው? በሚል ተቃውሞዎች ሲደረጉ ረዥም ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በተለይም ነጭ ፖሊሶች በጥቁሮች ላይ ያለ በቂ ምክንያት የሚወስዱት ያልተመጣጠነ እርምጃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
በቅርብ ጊዜ እንኳ በተመሳሳይ በጠራራ ፀሐይ የተገደሉት አህመድ አርበሪ በጆርጂያ እንዲሁም ብሬኖና ቴይለር በኬንታኪ ይጠቀሳሉ፡፡
በሜኒያፖሊስ ተቃውሞው ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ በከተማው ከንቲባ ጥያቄ መሰረት የሜኔሶታ ክፍለ ግዛት ገዥ ቲም ዋልትዝ ናሽናል ጋርድ (ልዩ ኃይል) ወደ ስፍራው እንዲንቀሳቀስ ፈቅዷል፡፡
የክፍለ ግዛቷ ገዥ ቲም እንደሚለው ተቃውሞን ተከትሎ በዛች ከተማ የተፋፋመው ዝርፍያና ውንብድና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማዋን ነዋሪዎች ንብረትም ለጉዳት የሰጠ ሆኗል፡፡
"የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ወደ ውንብድናና ዝርፍያ ሊወስደን አይገባም፡፡ የፍትህ ሥርዓት እና አሠራር ለውጥን ነው መጠየቅ የሚኖርብን" ሲል ለከተማዋ ነዋሪዎች የሰላም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ የጥቁሩ ሞት እንዳሳዘናቸው ገልጸው ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ እንዲከፍት ጠይቀዋል፡፡
ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት ጋር ተያይዞ አንገቱ ላይ በጉልበቱ የቆመበትን ነጭ ፖሊስ ጨምሮ ሌሎች ሦስት ተባባሪ ፖሊሶች ከሥራቸው እንዲባረሩ ብቻ ተደርጓል፡፡
በጎርጎሳውያኑ 2014 በበኒውዮርክ ከተማ ኤሪክ ጋርነር የተባለ ጥቁር ወጣት በተመሳሳይ በነጭ ፖሊስ ማጅራቱን የፊጢኝ ተቆልፎ ትንፋሽ አጥሮት እንዲሞት መደረጉ በመላው አሜሪካ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡ ኤሪክ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ፖሊሱን ይማጸን ነበር፡፡
ይህ የኤሪክ ሞት "የጥቁሮች ነፍስ ዋጋ ስንት ነው?" (ብላክ ላይቭስ ማተር) የሚለውን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ አቀጣጥሎት ቆይቷል፡፡
ከሜኔሶታ ሚኒያፖሊስ ባሻገር አሁን ተቃውሞ የበረታባቸው የአሜሪካ ከተሞች ኢሊኖይስ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያና ቴኔሲ ናቸው፡፡
በሁሉም ከተሞች እየተስተጋባ የሚገኘው መፈክር ጆርጅ ፍሎይድ ከመሞቱ ከደቂቃዎች በፊት ይናገር የነበረው ቃል ነው፤ "መተንፈስ አልቻልኩም!"