ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ተቃውሞዎቹ እውነተኛ የለውጥ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ" ባራክ ኦባማ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የጆርድ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች ፖሊስ ማሻሻያ እንዲያደርግ እውነተኛ የለውጥ መነሻዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናገሩ፡፡
የቀድሞ ፕሬዚደንቱ፤ የተቃውሞ ሰልፎች ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን የፖሊስ አሰራሮች እና በአገሪቷ ሰፊ የወንጀል ፍትህ ሥርዓትን የማሻሻል ችግሮች እውነተኛና ሕጋዊ ስጋቶችን ይወክላሉ ብለዋል፡፡
ኦባማ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ያመሰገኑ ሲሆን "እነርሱ የእኛን ክብርና ድጋፍ ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡ ሆኖም ግጭት የቀሰቀሱ የተወሰኑ ሰዎችን ድርጊት አውግዘዋል፡፡
ሰዎች ከፖለቲካና ከተቃውሞ መምረጥ የለባቸውም ያሉት ኦባማ ሁለቱንም ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
አክለውም "ግንዛቤ ለመፍጠር ማነሳሳት አለብን፤ ለለውጥ እርምጃ የሚወስዱ ዕጩዎች መምረጣችንን ለማረጋገጥ መደራጀት እና ድምጻችንን መስጠት ይገባናል፡፡" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኦባማ በመጨረሻም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዘርና አካባቢ ሳይለይ የተካሄዱ ከፍተኛ የወጣቶች እንቅስቃሴ ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
"ወደፊት በዚሁ ከቀጠልን ምክንያታዊ የሆነ ቁጣችንን ወደ ሰላማዊ፣ ዘላቂነት ያለው እና ውጤታማ ድርጊት መለወጥ እንችላለን፡፡ ይህ ጊዜ ከፍ ያሉ ሃሳቦቻችን ዳር ለማድረስ በአገራችን ረዥም ጉዞ የእውነተኛ ለውጥ ጅማሮ ሊሆን ይችላል" ብለዋል ኦባማ
ባለፈው ሳምንት በሜኔሶታ በነጭ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር በግፍ በሞተው የ46 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ምክንያት በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች በተቃውሞዎች እየተናጡ ነው።
በሌሎች የዓለም አገራት ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡ የተቃውሞ ሰልፎችም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
የግለሰቡን ሞት ተከትሎ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የጥቁሩ አሜሪካዊ ሞት ፖሊስ ኃይልን ከመጠቀሙ ጋር በፍጹም የሚያያዝ አይደለም ሲሉ መዘገብ ጀምረው ነበር። አንዳንዶች እንዲያውም የሞተው በራሱ የጤና ችግር ነው እስከማለት ደርሰው ነበር።
ይሁን እንጅ በሟች አስከሬን ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው የሕክምና ተቋም ጆርጅ ፍሎይድ የተገደለው በሰው ምክንያት ትንፋሽ አጥሮት እንደሆነ ይፋ አድርጓል።