በኬንያ ማደጎ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመው አሜሪካዊ ጥፋተኛ መሆኑን አመነ

የፎቶው ባለመብት, YouTube
በኬንያ የሚገኙ ማደጎ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመው አሜሪካዊ ጥፋተኝነቱን አመነ። የክርስቲያን ሚሲዮናዊ ነኝ የሚለው ግለሰብ በማደጎ የሚገኙ ሴቶች ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም ክስ የተመሰረተበትም በአሜሪካ ነው።
የ61 አመቱ ግሪጎሪ ዶው በአራት ወንጀሎችም ተከሷል።
ግለሰቡ አቋቁሞት የነበረው ማደጎ ቤት ከጎርጎሳውያኑ 2008- 2017 ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር ተብሏል።
የፌደራል ቢሮ ምርመራ (ኤፍቢአይ) ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ግለሰቡን ሲመረምሩት ነበር።
በምዕራብ ኬንያ በሚገኝ ቦታ የተቋቋመው ማደጎ ቤቱ ፔንስይልቫኒያ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያንም የገንዘብ ድጎማ ይደረግለት እንደነበር የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
ጥቃት አድርሶባቸዋል የተባሉት ሶስት ሴት ህፃናት የ11፣ 12ና 13 አመት መሆናቸውም ጭምር ተዘግቧል።
"ክርስቲያን ነኝ በሚልም ሽፋን ልጆቹ 'አባዬ' (ዳድ) እያሉ እንዲጠሩትም ያዛቸው ነበር። እንደ አባት ህፃናቱን ከመንከባከብ ይልቅ ትንሽነታቸውን በመጠቀም እንዲሁም መጠጊያ የላቸውም በማለት ጥቃት አድርሶባቸዋል" ሲል የአሜሪካ የፍትህ ቢሮ በመግለጫው አትቷል።
ግለሰቡ ከኬንያ ጠፍቶ ወደ አሜሪካ የተመለሰውም ያደረሰው ጥቃት ይፋ ሲሆን እንደሆነ መግለጫው አክሎ ገልጿል።
ኤፍቢአይ ያገኘውን መረጃ ይዞም ከኬንያ መንግሥት ጋር ሲመረምሩት ቆይተው ባለፈው አመት ነው ክስ የተመሰረተበት
"ግሪጎሪ ሃይማኖቱን ሽፋን በማድረግ ወንጀል ፈፅሟል፤ ህፃናቱ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሌላ ሃገር ስለፈፀመው በአሜሪካ ምንም የማይሆን ወይም ግድ የማይሰጣቸው መስሎት ነበር። ግን ተሳስቷል" በማለት አቃቤ ህግ ዊልያም ማክስዌይን ተናግረዋል።
አቃቤ ህጉ እንደተናገሩትም ግለሰቡ ኬንያ ከመሄዱ በፊትም ከዚህ ቀደም በአሜሪካ በፈፀመው ወሲባዊ ጥቃት በማስጠንቀቂያ እንዲሁም ለአስር አመት ያህልም "ህፃናት ደፋሪ" በሚልም ስም እንዲመዘብ ተደርጎ ነበር።
በሚቀጥለው አመት ጥቅምት ወር ላይም እንደሚፈረድበትም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።












