ኮሮናቫይረስ፡ “ጀግኖች ሆነን ነበር፤ አሁን ግን ተረሳን"- የጣልያን ሀኪሞች

የጣሊያን ጤና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, PAOLO MIRANDA

ጣልያን በኮቪድ-19 ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ናት። የአገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም ያደረጉት ተጋድሎ አስመስግኗቸዋል።

አሁን ግን እነዚህ የአገሪቱ ባለውለታዎች ተዘንግተዋል።

ሎምባርዲ በበሽታው ሳቢያ ከመላው ዓለም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ግዛት ናት። የህክምና ባለሙያዎች ሎምባርዲን ሊታደጓት እየሞከሩ ነው።

ፓውሎ ሚራንዳ የጽኑ ህሙማን ክፍል ነርስ ነው። “ብስጩ ሆኛለሁ፤ ከሰው ጋርም እጋጫለሁ” ይላል።

ከሳምንታት በፊት በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ያለውን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎች አንስቶ ነበር።

“የደረሰብንን መቼም መዘንጋት አልፈልግም። በቅርቡ ታሪክ ይሆናል። ከጠላት ጋር እየተዋጋን ነበር። አሁን መለስ ብዬ ለማሰብ ጊዜ ሳገኝ አቅጣጫ ቢስነት ይሰማኛል” ሲል ነርሱ ስሜቱን ያጋራል።

በጣልያን ሕይወት ወደ ቀደመ ገጽታዋ ቀስ በቀስ እየተመለሰች ነው። አገሪቱ እንቅስቃሴ በመጀመር ደረጃ ሁለት ላይ ትገኛለች። ነርሱ የሚያነሳቸው ፎቶዎች ይህንን ደረጃ ለማሳየት ያለሙ ናቸው።

“አደገኛው ጊዜ እየሰከነ ቢሆንም በጨለማ እንደተዋጥን ይሰማናል። ቁስለኞች እንደሆንን ይሰማኛል። ያየነው ነገር በሙላ አብሮን ይኖራል” ይላል።

አስፈሪ ቅዠቶች

የፓውሎን ስሜት የጽኑ ህሙማን ክፍል ነርስ ሞኒካ ማሪዎቲም ትጋራለች።

“ነገሮች ካለፈው ወቅት እየባሱ መጥተዋል። ያኔ በሽታውን እየተዋጋን ነበር። አሁን መለስ ብዬ ስመለከት ግራ እጋባለሁ” ትላለች።

በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ቀን ከሌት በሚሠሩበት ወቅት ለማሰብ ጊዜ አልነበራቸውም። አሁን ግን ያለፉት ወራት ሰቆቃ ተደራርቦ እየተሰማቸው ነው።

“ያየነው ሁሉ አብሮን ይኖራል። መተኛት አልችልም። በክፉ ቅዠትም እሰቃያለሁ። በየሌሊቱ አስር ጊዜ ልቤ እየመታ፣ ትንፋሽ አጥሮኝ እባንናለሁ”

የነርሷ የሥራ ባልደረባ ኤሊሳ ፒዜራ ወረርሽኙ እጅግ አስጊ በነበረበት ወቅት ብርቱ ነበረች። አሁን ግን ዝላለች።

ምግብ የማብሰል፣ ቤቷን የማጽዳት ጉልበትም የላትም። ሥራ በሌላት ቀን ተቀምጣ ትውላለች።

“ከዚህ ወዲያ በነርስነት መቀጠል የምፈልግ አይመስለኝም”

ሌላዋ ነርስ ማርቲና በንዲቲ ቤተሰቦቿንና ጓደኞቿን በበሽታው የምታስይዝ ስለሚመስላት እስካሁን ከማናቸውም ጋር አልተገናኘችም። ከባሌቤቷ ጋርም በተለያየ ክፍል ይኖራሉ።

“ከቤት ስወጣ ስለሚጨንቀኝ ተመልሼ እገባለሁ። ከዚህ ወዲያ በነርስነት መቀጠል የምፈልግ አይመስለኝም” ትላለች።

ነርሷ፤ “ካለፉት ስድስት ዓመታት በበለጠ ባለፉት ሁለት ወራት ሰው ሲሞት አይቻለሁ” ስትል ያሳለፈችውን ትገልጻለች።

አንድ አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በኮቪድ-19 ክፉኛ በተጠቁ አካባቢዎች ይሠሩ የነበሩ 70 በመቶ የሚሆኑ የጣልያን ነርሶች አሁን ላይ ተዳክመዋል።

የጥናቱ ጸሐፊ ዶ/ር ሰሪና ባሬሎ “ይህ ወቅት ለዶክተሮችና ለነርሶች ከባድ ነው” ትላለች።

የሰው ልጆች አደጋ ውስጥ ሲሆኑ ጭንቀትን መቆጣጠር የሚያስችል ንጥረ ነገር በአካላቸው ይመረታል። ሆኖም ግን ያሳለፍነውን ቆም ብሎ ለማሰብ ጊዜ ስናገኝ ጭንቀት ሊከተል እንደሚችል አጥኚዋ ታስረዳለች።

“ጀግኖች ሆነን ነበር፤ አሁን ግን ረሱን”

ዶክተሯ ብዙ የህክምና ባለሙያዎች ከአደጋ በኋላ የሚመጣ ጭንቀት ወይም በእንግሊዘኛው post-traumatic stress disorder (PTSD) ይገጥማቸዋል ብላ ትሰጋለች።

የበሽታው ምልክት ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላም ሊታይ ይችላል። የጤና ባለሙያዎች ከዚህ በኋላ ሥራቸው ላይ ማተኮር ሊከብዳቸውም ይችላል።

በመላው ዓለም ዶክተሮችና ነርሶች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ኮሮናቫይረስን በመዋጋታቸው ተሞግሰዋል። ጀግኖችም ተብለዋል። በጣልያን ግን ተቸሯቸው የነበረው ፍቅር እየተሸረሸረ ይመስላል።

ሞኒካ እንደምትለው፤ “ሞትን ፈርተው ሳለ ጀግና አድርገውን ነበር። አሁን ግን ረስተውናል። አሁን ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ሰዎች እንቆጠራለን”።

በቱራን ነርሶች እርስ በራሳቸው ተሳስረው፣ የቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክ ለብሰው ተቃውሞ አካሂደው ነበር። ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ለጤና ባለሙያዎች ትኩረት እንዳልተሰጠ ገልጸዋል። በቂ የሀኪሞች መገልገያ ወይም PPE እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል።

የተቃውሞ ሰልፉ ሲካሄድ “መጋቢት ላይ ጀግና ነበርን፤ አሁን ግን ዘንግታችሁናል” ስትል አንድ ነርስ በድምፅ ማጉያ ተናግራለች።

ለሥራቸው ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸው ነበር። እስካሁን ግን ምንም አላገኙም።

ቢያንስ 163 ሀኪሞችና 40 ነርሶች ኮቪድ-19ን ሲዋጉ ሕይወታቸውን አጥተዋል። አራቱ ራሳቸውን ነው ያጠፉት።

በርካታ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ቢከፈልም፤ ወረርሽኙ ያልተከሰተ ያህል ችላ ተብለዋል።

በአረጋውያን እንክብካቤ መስጫ ትሠራ የነበረችው ዶ/ር ኤሊሳ ናኒኖ “በቁጣ ነድጃለሁ” ትላለች።

እንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ ሲላላ፤ ሰዎች አካላዊ ርቀት ሳይጠብቁ፣ ጭምብል ሳያደርጉ ሲበሉና ሲጠጡ አስተውላለች።

“የሚያረጉት ነገር እኔንና የሥራ ባልደረቦቼን የሚያዋርድ ነው። የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ እየጣላችሁ ነው ብዬ ልጮህባቸው እፈልጋለሁ።”

በእርግጥ የጤና ባለሙያዎቹ ከሕዝቡ ያገኙት ድጋፍ ወረርሽኙን ለማለፍ እንዳገዛቸው አይክዱም። “ጀግና ነኝ አልልም። ግን ድጋፉ ጠቃሚ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጓል” ይላል ነርስ ፓውሎ።

ተመራማሪዋ ዶ/ር ሰሪና፤ የህክምና ባለሙያዎችን ከጭንቀት ለመታደግ የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልጋል ይላሉ።

ኮሮና
Banner

“ዶክተሮችና ነርሶች ያደረጉልንን መርሳት የለብንም” ሲሉም ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።