የሆንግ ኮንግ ሰልፈኞች የቻይናን ደህንነት ረቂቅ ህግ ለምን ይቃወማሉ?

በሆንግ ኮንግ የቻይናን የደህንነት ህግ ተቃውመው የወጡ ሰልፈኞች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ረጭቷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ወደ ከተማዋ ማዕከል በመሄድ ተቃውሟቸውን የገለፁ ሲሆን፤ 120ዎቹም ለእስር መዳረጋቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

በሳምንቱ መጀመሪያም አካባቢ የተለያዩ ኃገራት የፖለቲካ ልኂቃን የቻይናን ረቂቅ ህግ በመተቸት መግለጫ አውጥተዋል።

ፖለቲከኞቹ "የከተማዋን የራስ አገዛዝ ነፃነት ከመጣስ በተጨማሪ ህግን የተላለፈ እንዲሁም መሰረታዊ ነፃነትንም የሚጋፋ ነው" ብለውታል።

ቻይና ያወጣችው አዲሱ የደህንነት ህግ "የሃገር ክህደት፣ መገንጠል፣ ስልጣንን መተላለፍ" በሆንግኮንግ ግዛት ውስጥ የሚከለክል ነው።

የቻይና አስተዳደር ደጋፊ ናቸው የሚባሉት የሆንግ ኮንግ መሪ ኬሪ ላም በበኩላቸው ለህጉ ረቂቅ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀው፤ የከተማዋ ነፃነትም ላይ ምንም የሚቀየር ነገር አይኖርም ብለዋል።

ሰልፈኞቹ ኮዝዌይ ቤይና ቻይ በሚባሉት የከተማዋ ማዕከሎች ላይ በዛሬው ዕለት በመገኘት መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንዲሁም መልእክቶቻችን ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

"በረቂቁ መስረት ዜጎች መንግሥትን ተችተው ቢናገሩ ወይም ቢፅፉ እንደ ወንጀል ይቆጠርባቸዋል" በማለት የ25 አመቱ ቪንሰንት ያለውን ፍራቻ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።

አድማ በታኝ ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝ እንዲሁም ውሃን በመጠቀም ሰልፈኞን ለመበተንም ሙከራ አድርገዋል።

አንዳንድ ሰልፈኞች ጃንጥላ፣ የውሃ መያዣ ፕላስቲኮች እንዲሁም የቆሻሻ ማስቀመጫዎችን በፖሊሶቹ ላይ በመወርወር መንገዶቹን ለመዝጋት ሞክረዋል።

በዛሬው ዕለት የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍም ባለፈው አመት ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለውና በግጭቶችም የተሞላ እንደሆነ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

ሰልፈኞቹም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የፊት ጭምብል አጥልቀው ነበር።

በሃገሪቷ ውስጥ የኮሮናቫይረስን ለመዛመት ስብሰባ ቢከለከልም ሰልፈኞቹ ግን አካላዊ ርቀትን ባልጠበቀ መልኩ ተቃውሟቸውን አሰምተዋልም ተብሏል።

በባለፈው አመት በሆንግ ኮንግ ዲሞክራሲን በመደገፍ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ 8ሺህ 400 ሰዎች ታስረዋል።

ቻይና ይህንን ህግ ማርቀቅ ለምን አስፈለጋት?

በቻይና የተረቀቀው ይህ ህግ ሆንግ ኮንግ "ብሔራዊ ደህንነትን ልታሻሽል ይገባል" የሚል አንቀፅ ተካቶበታል።

አክሎም "የማዕከላዊው መንግሥት የፀጥታ አካላትም የብሄራዊ ደህንነትን ለመጠበቅ በአስፈላጊው ወቅት ከህጉ ጋር የሚጣጣም ኤጀንሲዎችን ማቋቋም ይችላሉ" ይላል።

ይህ ማለት ቻይና ከከተማዋ ጎን ለጎን የራሷን የፀጥታ ኃይሎች ማሰማራት ትችላለች ማለት ነው።

የተለያዩ ሃገራት ይህንን ህግ እየተቹ ሲሆን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ያወገዙት ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያና ካናዳ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ህጉ ተግባራዊ ከሆነ እርምጃ እንደሚወስዱ ቢናገሩም፤ እርምጃው ምን ሊሆን እንደሚችል ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ሊ በበኩላቸው " አንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት ለመመለስ እየጣሩ ነው። ታሪክን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረግ ጥረት የሁለቱንም ሃገራት የዘለቀ ግንኙነት ይጎዳል እንዲሁም የአለምን መረጋጋትም አጣብቂኝ ውስጥ ያስጋባዋል" ብለዋል።