'የአጎቴን ልጅ የቀብር ሥነ ሥርዓት በፌስቡክ ታደምኩ'

ወንበሮች በአንድ አንድ ሜትር ርቀት ተሰድረዋል። ቤተሰብ በአንድ ወገን፤ የሐይማኖት ሰዎች በሌላ ወገን ተቀምጠዋል። ሁሉም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጥልቀዋል።

የኬንያ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ቀብር እንዴት መፈፀም እንዳለበት ሕግ አውጥቷል። በዚህ ሕግ መሠረት ቀብር ላይ መገኘት የሚችሉት 15 ሰዎች ብቻ ናቸው።

የአጎቴ ልጅ ክሪስ ቀብር ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ መጠናቀቅ አለበት።

ጠዋት 1፡00 ሰዓት ሲሆን ሁላችንም ተሰባሰብን። የተሰባሰብነው ግን በቀብሩ ሥፍራ ሳይሆን በስልኮቻችንና ኮምፒውተሮቻችን ፊት ነበር። የቀብሩን ሥነ-ሥርዓት በፌስቡክ የቀጥታ ሥርጭት መታደም ጀመርን።

በመቶዎች የምንቆጠር የክሪስ ወዳጆች ሐዘናችንን ለመግለፅ በፌስቡክ አምባ ተሰልፈናል። ምክንያቱም ክሪስ መልካም ሰው ነበር። ሁሌም ተጫዋች፣ የቤተሰቡ ደስታ አድማቂ፣ ሳቁ ከሩቅ የሚሰማና ለተቸገሩ ደራሽ ነበር።

ታድያ በዚህ ቀን ለክሪስ መሆን የቻልነው በፌስቡክ ቀጥታ ሥርጭት መገኘት ብቻ ነው።

ምንም እንኳ ክሪስ የቅርብ ዘመዴ ቢሆንም አንድ ቤት ውስጥ እየቦረቅን ነው ያደግነው። ክሪስ ማለት ለእኔ ከወንድምም በላይ ነው።

ክሪስ ኪሱሙ በተባለችው የምሥራቅ ኬንያ ከተማ ይኖር ነበር። ለጥቂት ሳምንታት ከታመመ በኋላ በዕለተ ፋሲካ ነበር ህይወቱ ያለፈው። ከዚያም መንግሥት ባዘዘው መሠረት በሦስት ቀናት ወስጥ መቀበር ነበረበት።

ነገር ግን በርካታ ወዳጅ ዘመዶቹ ያለነው በመዲናዋ ናይሮቢ ነው። ከናይሮቢ መውጣትም ሆነ ወደ ናይሮቢ መግባት ደግሞ ተከልክሏል። በዚህ ምክንያት የክሪስን ቀብር መታደም አልቻልንም።

ሥነ-ሥርዓቱ አጠር ያለ ነበር። ሁሉም ነገር አጠር እንዲል ተደርጓል። ክሪስ የቤተክርስትያን የሕብረ ዝማሬ (ኳየር) ቡድን ውስጥ ከበሮ ተጫዋች ነበር። በቀብሩ ላይ ግን ማንም የሙዚቃ መሣሪያ ሊጫወትለት አለመቻሉ ያሳዝናል።

ወዳጅ ዘመዶቹ ማድረግ የቻሉት በፌስቡክ የቀጥታ ሥርጭቱ የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ስለ ክሪስ የሚያስታውሱትን መፃፍ ነው።

እንደ ወትሮው በቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝቶ መተቃቀፍና ሐዘንን መግለፅ አልተቻለም።

የወዳጅ ዘመዶቼን ቀብር እንዲህ እታደማለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ሰው ማቀፍ፣ የሰው እምባ ማበስ እንዲህ ይናፍቀኛል አላልኩም።

በጣም የሚያሳዝነው የፌስቡክ ቀጥታ ሥርጭቱ በመሃል መቋረጡ ነው። በዚህ ምክንያት የክሪስ አስከሬን አፈር ሲለብስ እንኳ ማየት አልቻልኩም።

በብዙ የአፍሪካ አገራት ቀብር ትልቅ ሥፍራ አለው። በእኔም ባሕል ሞት ትልቅ ቦታ አለው። ሰዎች ሲሞቱ በክብር መሸኘት አለባቸው። እኔ የመጣሁበት ምዕራባዊ ኬንያ ሞትና ቀብር በጣም ክብር የሚሰጣቸው ነገሮች ናቸው። አስክሬን ክቡር ነው። ቀብር ደግሞ በእርጋት የሚፈፀም ሥርዓት ነው።

በተለይ ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች የቀብር ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ሊፈጅ ይችላል። ለቅሶ፣ እሳት አንድዶ መሰባሰብ፣ ያለፉ ታሪኮችን ማውሳት የተለመዱ ናቸው።

ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ግን ይህ የሚታሰብ አይደለም። መንግሥትም አይፈቅደውም። ሰው በኮቪድ-19 ሞተም በሌላ ምክንያት ቀብሩ አጠር ያለና ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን አለበት።

የክሪስ ቀብርም እንዲሁ ነበር። ማንም መጥቶ ቤተሰቡን ማፅናናት አልቻለም። ድምፅን ከፍ አድርጎ ማልቀስም አይፈቀድም። መተቃቀፍ፣ መነካካት፣ እጅ መጨባበጥና መሳሳም ተረት ናቸው።

አካላዊ ርቀትን የሚያስከብሩ የመንግሥት ሰዎች በቀብሩ ላይ ተገኝተው ነበር።

የክሪስ አርባም አልተዘከረለትም። አንድ ሰው ከሞተ በአርባ ቀኑ እንደ አዲስ ይታሰባል። ነገር ግን ክሪስ ይህ ሊሆንለት አልቻለም።

ምናልባት ወረርሽኙ መቋጫ ሲያገኝ እንደ አዲስ ተሰባስበን ክሪስን እናስበዋለን። እስከዚያው ግን ክሪስን ቀበርኩት ለማለት አያስችለኝም።