ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ክትባቱ ቢገኝ አፍሪካ ከሃብታም አገራት እኩል ተጠቃሚ ትሆን ይሆን?
ከዚህ ቀደም በአፍሪካውያን ላይ ስለተሞከሩ የክትባት ዓይነቶች በርካታ አስፈሪ ታሪኮች ሲነገሩ ይሰማል። ቢሆንም ግን ተመራማሪዎች አፍሪካውያን በዚህ የክትባት ምርምር ላይ መሳተፋቸው ወሳኝ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህም ምክንያታቸው በመላው ዓለም የሚሰራ ክትባት ለማምረት የሁሉም የዓለም ሕዝቦች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ነው።
የኮሮናቫይረስ እስካሁን ድረስ ፈዋሽ መድሃኒት ወይም ክትባት ባይገኝለትም ነገር ግን ክትባት መገኘቱ የቫይረሱ ስርጭትን ለመግታትም ሆነ ሕሙማንን ለማከም ወሳኝ ሚና እንዳለው የዓለም ጤና ድርጅት ይናገራል።
አክሎም የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም በማለማመድ ቨይረሱን በመዋጋት እንዳይታመሙ ያደርጋል ይላል።
በአፍሪካ ውስጥ እስካሁን ድረስ የክትባቱ ሙከራ እየተካሄደ ያለው በደቡብ አፍሪካ ሲሆን ኬንያዊያንም ሙከራውን ለማድረግ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን የክትባት ሙከራ ጉዳይ አፍሪካውያንን እያከራከረ ነው። በክርክሩ ገበታ ከፊት የሚሰየመው ደግሞ "የቅኝት ግዛት አስተሳሰብ" የሚለው ነው።
ይህ መከራከሪያ የተሰማው ሁለት ፈረንሳውያን የሕክምና ባለሙያዎች የክትባቱን ሙከራ በአውሮፓ እና በአውስትራሊያ ስለማድረግ በቴሌቪዥን ቀርበው ሃሳብ ከሰጡ በኋላ ነው።
በዚህ የቴሌቪዥን ክርክር ላይ ታዲያ በአፍሪካም ሙከራው መደረግ እንዳለበት በመግለጽ ተስማሙ። በወቅቱ የሕክምና ባለሙያዎቹ ለክርክራቸው ያቀረቡት አስረጅ ያለ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ያለ በቂ ሕክምና በአፍሪካ እንዴት ቫይረሱ ሳይስፋፋ ቀረ የሚለው ነው።
ከዚያም ሙከራው አፍሪካ ውስጥ መደረግ እንዳለበት ሃሳብ ሰጡ። ይህ የሕክምና ባለሙያዎቹ ንግግር ግን ከተለያዩ ወገኖች ተቃውሞን አስተናግዷል።
"በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከአንድ ተመራማሪ እንዲህ አይነት አስተያየት መስማት አሳፋሪና አፀያፊ ነው" ያሉት የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ናቸው።
"ይህንን ሃሳብ በቻልነው መጠን ሁሉ እናወግዘዋለን፤ እናም የማረጋግጥላችሁ ነገር አይሆንም፤ የቅኝ ግዛት የዞረ ድምር መቆም አለበት" ነበር ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ በወቅቱ።
በዚህ እሰጥ አገባ ውስጥ ድምጻቸው የተሰማው ሌሎች ታዋቂ አፍሪካውያን ደግሞ ዲዲየር ድሮግባና ሳሙኤል ኤቶ ናቸው።
ድሮግባ በትዊተር መልዕክቱ ላይ "አፍሪካውያንን እንደ ጊኒ ፒግ መሞከሪያ ለማድረግ አትቋምጡ፤ ያስጠላል" ብሏል።
ይህ የተለያዩ ሰዎች ቁጣ መሰረተ ቢስ አይደለም። ዘረኝነትና የምጣኔ ሃብት ልዩነት በጤና ተቋማትም ውስጥ እንደሚታይ በሚገባ ተሰንዶ የተቀመጠ ነው።
የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች በአፍሪካ ለሰው ልጅም ሆነ ለሙያው ስነምግባር ግድ ሳይሰጣቸው ሙከራ ማድረጋቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ይገኛሉ።
ለምሳሌ እአአ በ1996 ግዙፉ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ፋይዘር በናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛት ካኖ የመድሃኒት ሙከራ አድርጎ ነበር።
በዚህም የተነሳ ረዥም ጊዜ የፈጀ የሕግ ክርክር ተደርጎ ግዙፉ የመድሃኒት አምራች በመድሃኒት ሙከራው ላይ ለተሳተፉ የተወሰኑ ልጆች ወላጆች ካሳ እንዲከፍል ተደርጓል።
በዚህ ምርምር ላይ በተሰጣቸው የፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት የተነሳ 11 ልጆች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል። በወቅቱ ልጆቹ በምርምር ላይ እንዲሳተፉ ኩባንያው ከቤተሰቦቹ ስላገኘው ፈቃድ ጥያቄ ተነስቶ ነበር።
ከሁለት አስርታት በኋላ፣ በኡጋንዳ ከሚገኙ ተመራማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ካትሪን ኪዮቡቱንጊ ነገሮች ስለመቀየራቸው ያስረዳሉ።
አሁን ምርምር ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ጥብቅና ግልጽ የሆነ ሂደት ማለፍ አለበት ይላሉ።
የአፍሪካ ስነ-ሕዝብ እና ምርምር ማእከል ኃላፊ ዶ/ር ኪዮቡቱንጊ "የግለሰቦችን ደህንንት ለመጠበቅ የሚሰራ ስራ አለ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እኚህ ግለሰብ ሰዎች ሙያዊ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የሙያ ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን ያስረዳሉ።
"በክትባት ሥራ ውስጥ የተሰማራ አንድ ተመራማሪ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሰዎችን የሚገድል እንዲሆን አይፈልግም" በማለትም "የሰዎች ሕይወትና የሥራ ታሪክ አደጋ ላይ ነው፤ ሰዎች በሙያቸው ላይ ከፍተኛ ጊዜና ገብዘብ አጥፍተዋል" ብለዋል።
አክለውም የግለሰቦችን ደህንንት ለመጠበቅ በአገርና በተቋማት ደረጃ የሚሰራ ሥራ መኖሩን ገልፀዋል። አገራት የመድሃኒት ምርምሮችንና ሙከራዎችን ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት እንዳሏቸው ይገልፃሉ።
"የክትባት ምርምሮችን ሁሉንም የክትባት ደህንነት ቅደመ ሁኔታዎች ሳይከተሉና ሳያሟሉ ለእርሱም ማረጋገጫ ሳያገኙ ማካሄድ አይቻልም" ሲሉ ያስረዳሉ።
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት በዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ የሚካሄዱ የመከላከልና ክትባት ምርምሮችን የሚከታተሉት ሪቻርድ ሚሂጎ ናቸው።
"በምርምር ስርዓት ውስጥ አፍሪካውያን ደህንነታቸው ባልተጠበቁ ምርቶች እንዳይጎዱ የሚያደርግ የደህንነት ጥበቃ እንዲሁም ማበረታቻዎች አሉ" ካሉ በኋላ ምርምር የሚያደርጉ አካላት ማንኛውንም መድሃኒትም ሆነ ክትባት በመሸጥም ሆነ በማምረት ውስጥ እንዲሳተፉ እንደማይፈቀድ ገልፀዋል።
ይህ ማረጋገጫ ግን የብዙ አፍሪካውያንን ልብ እንዳያሳርፍ እንቅፋት የሆነው የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻዎች ናቸው።
ጥቁር ሕዝቦችን ለማጥፋት ያለሙ ጎጂ ክትባቶች እየተሰሩ ነው የሚል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እዚህም እዚያም ይሰማል። ለምሳሌ ሰባት ሴኔጋላዊ ሕፃናት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ተሰጥቷቸው ሞቱ የሚለው የፌስቡክ ሐሰተኛ ወሬ በርካቶችን አሸብሮ ነበር።
ይህ ወሬ ደግሞ የተሰማው የፈረንሳውያኑ የሕክምና ባለሙያዎች አስተያየት ከተሰማ በኋላ መሆኑ ጉዳዩን አባብሶት ነበር። የዓለም ጤና ድርጅትም ኮሮናቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን የሐሰተኛ መረጃዎችንም መዋጋት እንደሚያስፈልግ አስታውቆ ነበር።
በአፍሪካ ያለው በቂ ትኩረት ያላገኘው ችግር ደግሞ የጤና ስርዓቱ ተገቢው ድጋፍ ሳይሰጠው መቆየቱ ነው። የአፍሪካውያን መሪዎች እአአ በ2001 የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ከዓመታዊ በጀታቸው ቢያንስ 15 በመቶ ለመመደብ ቃል ገብተው ነበር።
ነገር ግን ከ54 አፍሪካ አገራት ይህንን ማሳካት የቻሉት አምስት ብቻ ናቸው።
አፍሪካ የምሁራን እጥረት ባይኖርባትም አብዛኞቹ ወደተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ተቋማት በመሄድ ምርመራቸውን ማካሄድ ይመርጣሉ። ለዚህም ምክንያታቸው በቂ የሆነ በጀት አለመኖሩ መሆኑ ይገለፃል። በዚህም የተነሳ የአፍሪካውያን የጤና ችግሮች በሚገባ አልተዳሰሱም።
በአገራቸው የምርምር ስራቸውን ለማካሄድ የወሰኑም ቢሆኑ ደጋፊ አካላትን ለማግኘት ፈተና ይሆንባቸዋል፤ በዚህም የተነሳ በርካታ ምርምሮች በደቡብ አፍሪካና በግብጽ ብቻ ይደረጋሉ ማለት ነው።
በተጨማሪም በርካታ የክሊኒክ ሙከራቸውን አልፈው የሚወጡ መድሃኒቶች ሙከራ የሚደረግባቸው በአደጉ አገራት ይሆናል። በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ሙከራ ተደርጎላቸው ለገበያ የሚቀርቡ መድሃኒቶች በአፍሪካ ፈዋሽነታቸው አልተረጋገጠም ማለት ነው።
ምስራቅ አውሮፓ፣ እስያ እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ ምንም እንኳ የሕዝብ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሄድም የመድሃኒት ምርምርና ሙከራዎች ላይ ሲሳተፉ አይስተዋልም።
ተመራማሪዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በመላው ዓለም የሚሰራ የኮቪድ-19 ክትባት መሰራት እንዳለበት ይስማማሉ። አክለውም አፍሪካ ከምርምር ስራዎች ራሷን ማግለሏ ከዚህ ቀደም የነበራትን የመገለል ታሪክ ማስቀጠል ነው ብለዋል።
"ክትባቱ በዩናይትድ ኪንግደም ሙከራ ተደርጎበት አፍሪካውያንን ለማከም ቢውል ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም የተለያዩ ሁኔታዎች ናቸው ያሉን፣ የዘረመል ዓይነታችን ክትባቱ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል" ይላሉ ዶ/ር ኪዮቡቱንጊ።
"የተለየ ዝርያ እንዲሁም የተለየ የበሽታ ታሪክ አለን፤ በርካታ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችም የሚገኙት እዚህ አፍሪካ ውስጥ ነው"
ነገር ግን ተመራማሪዋ አሁንም ፍራቻቸው አፍሪካ ምንም ቢሆን መገለልዋ ላይቀር ይችላል የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ አህጉሪቱ አሁንም የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ላይ ችግሮች ያሉባት መሆኑ ነው።
" አፍሪካ የምትጋፈጠው ትልቁ ችግር ክትባቱ ቢገኝም ሃብታም አገራት ሁሉንም ገዝተው ለአፍሪካውያን የሚቀር ላይኖር ይችላል" ይላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተለያዩ የዓለም አገራት መሪዎች ክትባቱ ሲገኝ አገራት በእኩልነትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።