ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት ጉባዔ፡ ኮሮናቫይረስን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ አገራት ጥያቄ ያቀርባሉ ተባለ
የምድራችን የጤና ባለሥልጣናት ዓለም ኮሮናቫይረስን በተመለከተ እስካሁን የተወሰደው እርምጃ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም ጤና ድርጅት 194 አባል አገራት ተወካዮች ዛሬና ነገ [ሰኞና ማክሰኞ] የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው በኢንተርኔት አማካይነት 73ኛ ጉባኤያቸውን ያካሂዳሉ።
በዚህም ጉባኤ ላይ በመላው ዓለም ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን በቀጠፈው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ የዓለም ጤና ድርጅትና አባል አገራቱ የወሰዱት እርምጃ ላይ ጥያቄዎች ይነሳሉ ተብሏል።
በየዓመቱ አባል አገራት በዓለም የጤና ድርጅት ጉባኤ ላይ እየተገኙ የድርጅቱን ሥራዎች በመገምገም በቀጣይ ዓመት የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ይወስናሉ።
የአውሮፓ ሕብረት ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከአውስትራሊያና ኒው ዚላንድ ጋር በመሆን ዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ስለተወሰዱ እርምጃዎች ምርመራ እንዲደረግና ከዚህ በሽታ ምን ትምህርት እንደሚወሰድ የሚነሳውን ጥያቄ በመሪነት ያቀርባል ተብሏል።
የአውሮፓ ሕብረት ቃል አቀባይም በሚደረገው ግምገማ ላይ መመለስ ያለባቸው በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
ጨምረውም "አንዱ አንዱን ለመወንጀል ጊዜው አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።
ነገር ግን በዚህ ጉባኤ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን በተመለከተ በወሰዳቸው እርምጃዎች ሳቢያ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚነሱበት ይጠበቃል።
ይህንን በተመለከተ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ዶክተር ማርጋሬት ሃሪስ እንዳሉት "ይህ ጉባኤ ሁልጊዜም በርካታ ጥያቄዎች ለድርጅቱ የሚቀርብበት ነው" ሲሉ የዘንድሮው አዲስ ነገር ሊሆን እንደማይችል አመልክተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የሁሉንም አባል አገራት ጥቅምን በእኩል ደረጃ ይወክላል ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በቻይናና በአሜሪካ መካከል ባለው ፖቲካዊ ፍጥጫ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
በዚህም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድርጅቱን በሽታውን በአግባቡ ባለመያዝና ቻይና ውስጥ የተከሰተውን ወረርሽኝ በመሸፋፈን ከከሰሱ በኋላ ባለፈው ወር ለዓለም የጤና ድርጅት ከፍተኛውን ገንዘብ የምታበረክተው አሜሪካ ድጋፏን እንድታቋርጥ ምክንያት ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም የጤና ድርጅት፤ አባል አገራቱ በጤና ጉዳዮች ላይ ያላቸውን መረጃ እንዲያጋሩ የሚያስገድድ ሥልጣን የሌለው ቢሆንም አሜሪካ ከቻይና አንጻር ድርጅቱን እየከሰሰች ነው።
በአሁኑ ጉባኤ ላይ ግን ድርጅቱ ወረርሽኞች ወደሚከሰትባቸው በመግባት ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ የሚያስችለው ተጨማሪ ሥልጣን እንዲሰጠው ጥያቄ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓለም አቀፍ የጤና ደንብ መሰረት አገራት በግዛታቸው ውስጥ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለድርጅቱ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
ዓለምን አስጨንቆ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ቻይና ውስጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ4.5 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በበሽታው ተይዘዋል።
ይህ ጉባኤም የሚካሄደው በሽታውን በተመለከተ ኃያላኑ አሜሪካና ቻይና እየተወዛገቡ ባሉበት ጊዜ ነው።