ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ ክትባቱን ለአሜሪካ ቀድማ ለመሸጥ ፍላጎት የላትም
ለፈረንሳዩ ግዙፉ የመድኃኒት ኩባንያ ሳኖፊ፤ የኮቪድ-19 ክትባትን መስራት ከቻለ ለአሜሪካ ገበያ ቀድሞ መስጠት "ተቀባይነት እንደሌለው" የፈረንሳይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ።
በሳኖፊ ከፍተኛ የበላይ ኃላፊ ፓል ሁድሰን "የአሜሪካ መንግሥት ምርምሩ ላይ ቀድሞ ኢንቨስት በማድረጉ በብዛት ቀድሞ የማዘዝ መብት አለው" ብለው ነበር።
በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ ቤተ ሙከራዎች ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ምርምር እያደረጉ ቢሆንም ክትባቱን ለማምረት ግን ዓመታት ይወስዳል እየተባለ ነው።
ምክትል የገንዘብ ሚኒስትሩ አግነስ ፓኔር ሩናቼር "ለእኛ ለዚህኛው አገር እና ለዚህኛው አገር ቅድሚያ መስጠት የሚለው ከገንዘብ አንፃር ተቀባይነት የለውም" ብለዋል ለፈረንሳዩ ሬዲዮ።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ሕብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን ለመጨመር ያለመ ጉባኤ ተካሂዶ ስምንት ቢሊየን ዶላር ከአርባ አገራትና ከለጋሽ አገራት ማግኘት ተችሏል።
የተገኘው ገንዘብ የኮሮናቫይረስ ክትባትና ሕክምናን ለማግኘት ይውላል ተብሏል።
ጉባዔውን ያዘጋጀችው ዩናይትድ ኪንግደም ስትሆን አሜሪካና ሩሲያ አልተሳተፉበትም።
የአውሮፓ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ስቴፋን ዲ ኬርስማይከር "የኮቪድ-19 ክትባት የዓለም አቀፍ ንብረት፣ ሁሉም ሊጠቀምበት እና ዓለም አቀፋዊ መሆን አለበት" ማለታቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ዓለም አቀፍ ትብብር
ሳኖፊ በኮቪድ-19 ላይ የሚያደርገውን ምርምር አሜሪካው ባዩሜዲካል አድቫንስድ ሪሰርች እና ዴቬሎፕመንት ባለስልጣን (ባርዳ ) በገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሳኖፊ የሚያደርገውን ምርምር ለማገዝ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ የታክስ ክሬዲት እየተቀበለ ነው።
ሐሙስ ዕለት በፈረንሳይ የሳኖፊ ኃላፊ፤ ኦሊቨር ቦጊሎት እንዳሉት "ዓላማችን ክትባቱን ለአሜሪካ፣ ለፈረንሳይ እንዲሁም ለአውሮፓ በተመሳሳይ ወቅት ማቅረብ ነው" ብለው ነበር።
ለፈረንሳይ ዜና ቻናል ቢኤፍኤም ቲቪ ሲናገሩም ይህ ሊሆን የሚቻለው "አውሮፓውያን እንደ አሜሪካውያን ሁሉ በፍጥነት መሥራት ከቻሉ ነው" እንዲሁም አሜሪካ መንግሥት "በርካታ መቶ ሚሊዮኖች" ለመመደብ ቃል መግባቱን ተናግረዋል።
ባለፈው ወር ሳኖፊ ከብሪታኒያው ግላክሶስሚዝክላይን (ጂኤስኬ) በክትባቱ ላይ ለመስራት የተጣመሩ ሲሆን እስካሁን ድረስ ሙከራ አልተጀመረም።
የሳኖፊ ክትባት ምርምር የበላይ ኃላፊ፤ ጆን ሺፈር እንዳሉት ደግሞ "እየተጠቀምን ያለነው ለኢንፍሉዌንዛ የሰራነውን ቴክኖሎጂ ነው። ይህንኑ ኮቪድ-19 አምጪ ለሆነው ቫይረስ እየተጠቀምንበት ነው" ብለዋል።