ኮሮናቫይረስ፡ ተስፋ የተጣለበት የኮሮናቫይረስ ክትባት በሰው ላይ ሙከራው ተጀመረ

የመጀመሪያው በሰው ላይ የሚደረግ የኮሮናቫይረስ ክትባት አውሮፓ ውስጥ ተጀምሯል።

ኦክስፎርድ ውስጥ የተጀመረው ይህ ሙከራ በሁለት በጎ ፈቃደኞች ላይ ይጀመር እንጂ 800 ሰዎች ይሳተፉበታል።

ከ800 በጎ ፈቃደኞች መካከል ግማሹ የኮሮናቫይረስ ክትባት እንደሚሰጣቸው ሲነገር የተቀሩት ደግሞ የማጅራት ገትር መከላከይ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ነገር ግን በጎ ፈቃደኞቹ የትኛውን ክትባት እንደወሰዱ አይነገራቸውም።

ክትባቱ በኦክስፎርድ ዩነቨርሲቲ ባለሙያዎች በሦስት ወራት የበለፀገ ነው።

ምርምሩን የመሩት ፕሮፌሰር ሳራህ ጊልበርት በክትባቱ ከፍተኛ የራስ መተማመን እንዳላቸው ይናገራሉ።

"እርግጥ ነው ሰዎች ላይ መሞከር አለብን። በትክክል መሥራቱንም ማረጋገጥ ይኖርብናል። አልፎም ሰዎች በኮሮናቫይረስ መልሰው አለመያዛቸውን ማረጋገጥ ግድ ይላል። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ሕዝብ ሊሠራጭ የሚችለው።"

ወደ ሰው እንዳይተላለፍ የተደረገው ይህ ክትባት ከቺምፓንዚ ከተገኘ ደካማ ጉንፋን የተሠራ ነው።

የምርምር ቡድኑ ከዚህ በፊት ሜርስ የተሰኘ ሌላ ዓይነት ኮሮናቫይረስን የሚከላከል መድኃኒት ሠርቶ ውጤታማ ሆኗል።

ክትባቱ እንደሚሠራ የሚታወቀው ሙከራ ከተደረገባቸው ሰዎች ምን ያክሉ ላይ ውጤታማ ሆኗል የሚለው ሲለይ ነው። ነገር ግን ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ከመጣ ሙከራ የሚደርግባቸው ሰዎች ቁጥር ሊቀንስ ይችላል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድ ሙከራውን ለማጣደፍ እየተሯሯጡ እንደሆነ ይናገራሉ።

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት 5 ሺህ ሰዎች ላይ ሙከራው እንደሚቀጥልና ሙከራ የሚደርግባቸው ሰዎች የዕድሜ ገደብ እንደማይኖረው ታውቋል። ቢሆንም ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች የመከላከል አቅማቸው የደከመ ስለሆነ ተጨማሪ ምርመራ ይደርግባቸዋል።

የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ከአውሮፓ አልፎ አፍሪካ ውስጥም የክትባት ሙከራ የማድረግ ሐሳብ አላቸው። የመጀመሪያዋ ሃገር ደግሞ ኬንያ ልትሆን ትችላለች።

ምንም እንኳ በጎ ፈቃደኞችን ሆን ብሎ ኮሮናቫይረስ በማስያዝ እነሱ ላይ ክትባቱ ይሥራ አይሥራ መሞከር ቢቻልም ይህ የሙያውን ሥነ-ምግባር የሚፃረር ነው።

ነገር ግን ክትባቱ ውጤታማነቱ አስተማማኝ የሚባል ደረጃ ላይ ከደረሰ ይህንን ማድረግ እንደሚጀምሩ ፕሮፌሰር አንድሪው ያስረዳሉ።

ክትባቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እየተሞከረ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ማስመር ይፈልጋሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ. . .

በሌላ በኩል ተስፋ ተጥሎበት የነበረ አንድ መድኃኒት በመጀመሪያ የክሊኒክ ሙከራው እንደከሸፈ የዓለም ጤና ድርጅት በስህተት ያተመው አንድ ዕትም አሳብቋል።

መድኃኒቱ ቻይና ውስጥ ሲሆን የተሞከረው እንደታሰበው የተሞከረባቸውን ሰዎች የመከላከል አቅም ማሳደግ አልቻለም።

ቢሆንም መድኃኒቱን የሠራው የአሜሪካ ድርጅት በስህተት የታተመው መረጃ ጥናቱን አልተረዳውም ይላል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃውን ከድረ-ገፁ ላይ አውርዶታል። መረጃው የተሟላ ስላልሆነ ነው ያወርድኩትም ሲል ማብራሪያ ሰጥቷል።