ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ ልታደርግ ጫፍ ደርሳለች
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ውጤታማ እንደሚሆኑ ከፍተኛ ተስፋ በተጣለባቸው ሁለት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ሙከራ ማድረግ ጀምረዋል።
እነዚህን ክትባቶችን የሰራው በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና ኢኖቪዩ ፋርማሱቲካል በተባለ የአሜሪካ ድርጅት ነው።
ክትባቶቹ በእንሰሳት ላይ እንዲደረግ የመጀመርያ ዙር ሙከራን አልፈዋል። ለዚህም የዓለም ጤና ድርጅት እውቅና ሰጥቶታል።ከዚያ በኋላም ሙከራው ወደ ሰው እንዲሸጋገር ፍቃድ ያገኛል ማለት ነው።
ከዚያ ቀጥሎ የአውስትራሊያ የሳይንስ ኤጀንሲ ይህ የክትባት ሙከራ በሰው ልጅ ላይ የሚያመጣውን ውጤት ይመረምራል።
በእርግጥ ሰው ልጅ የክትባት ሙከራ ሲደረግ ይህ የመጀመርያው አይሆንም። ባለፈው ወር በአሜሪካ በአንዲት ሴት ላይ የክትባት ሙከራ መደረጉ አይዘነጋም። ሆኖም ያ ሙከራ በእንሰሳት ላይ የሚካሄደውን ሙከራ የዘለለ ነበር።
ይህ የአውስትራሊያው ሙከራ ግን በእንሰሳት ላይ የተጀመረ በመሆኑ ውጤቱ አመርቂ ከሆነ በሰው ልጅ ላይ ሲካሄድ ሂደቱን ሙሉ ያደርገዋል ተብሏል።
"በቅድመ ክሊኒካል ምዕራፍ የሚደረገውን ሁሉ እያደረግን ነው የመጣነው" ብለዋል የጥናትና ምርምሩ መሪ ፐሮፌሰር።
በተመሳሳይ በመላው ዓለም ቤተ ሙከራዎች ክትባቱን ለመፍጠር ቀን ተሌት እየሰሩ ነው የሚገኙት። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ለአንድ በሽታ መድኃኒት ለማግኘት ዓለም እንዲህ በቅንጅት ሲሠራ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 20 ቤተ ሙከራዎች በተለያየ የዓለም ጥግ በሙከራ ተጠምደዋል።
ክትባቱ እንዴት ነው የሚሰራው?
የአውስታሊያ የሳይንስና ምርምር ኢንስቲትዩት እንደሚለው ይህ ሙከራ የተጀመረው ኮሮና በያዛቸው ፌሬትስ በሚባሉ በትንንሽ አጥቢ እንሰሳት ላይ ነው። ፌሬትስ አይጥና ጥንቸል አዳኝ እንሰሳት ናቸው።
እነዚህ እንሰሳት በኮሮና የሚጠቁበት መንገድ ከሰው ልጅ ጋር ተቀራራቢ ነው።
አሁን የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች ሊሞክሩ ያሉት የክትባት አይነት በዋናነት ሁለት መልክ አለው።
የመጀመርያው ቬክተር ቫክሲን ይሰኛል፤ ይህ ማለት የቫይረሱን ደካማ ቅንጣት ወደ ሰው በማስገባት የሰው ልጅ የበሽታ ተከላካይ ሠራዊት (ነጭ የደም ሴሎችን ጨምሮ) የመልሶ ማጥቃት ምላሽ እንዲሰጥ የሚያነቃቃ ሂደት ነው። ብዙ ክትባቶች በዚህ መልክ ነው የሚፈጠሩት።
ይህ እየተሞከረ ያለው በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በኩል ነው።
ሁለተኛው ክትባት በኢኖቪዮ የመድኃኒት አምራች የተዘጋጀው ነው። ይህ ደግሞ ቫይረሱን ሳይሆን የኮሮና ፕሮቲንን ቅርጽና ዓመል ሞዴል አድርጎ የሚሰራ ሲሆን ሴሎች ቫይረሱን እንዲከላከሉት የሚያነቃቃቸው ይሆናል ተብሏል።
ምርምሩን የሚመሩት ፕሮፌሰር ድሪው እንደሚሉት በርካታ መንገዶችን እየተከተሉ መሆናቸው ለስኬቱ እንዲቀርብ ይረዳል።
ክትባቱ በምን ያህል ጊዜ እውን ሊሆን ይችል ይሆን?
የፊታችን ሰኔ ወር በእንሰሳት ላይ የተሞከረው ሙከራ ውጤት ይታወቃል። ያ ስኬታማ ከሆነ ወደ ክሊኒካል የምርመራ ደረጃ ከፍ ይደረጋል።
የዚያ ውጤት ከታየ በኋላ በብዙ ቁጥር ለመመረት ዝግጁ ይሆናል። ሆኖም ግን የመድኃኒት ቁጥጥርና ሂደት የ18 ወራት የመድኃኒቱን ባህሪና የጎንዮሽ ጉዳት የማጥኛ ጊዜን ይፈልጋል ተብሏል።
"እዚህ አሁን የደረስንበት ደረጃ ለመድረስ'ኮ በተለምዶ 2 ዓመት ይወስድ ነበር" ብለዋል ፕሮፌሰሩ የሂደቱን መፋጠን ሲያስረዱ።
ለምሳሌ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየተሰራ ያለው ክትባት በሌሎች ቤተ ሙከራዎችም እየተካሄደ ነው። ይህም የአሜሪካንን የአዲስ መድኃኒት አሰራር መመሪያን ለመከተል የሚደረግ ነው።
ፕሮፌሰር ድሪው እንደሚሉት አንድ ቤተ ሙከራ ብቻውን አንድ ክትባት ከጅምሩ እስከ ስኬቱ አሟልቶ አያወጣም። የብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሁልጊዜም የሚጠበቅ ነው።
ፕሮፌሰሩ ክትባቱን የማግኘት ተስፋ ምን ያህል ነው ተብለው ሲጠየቁ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ቤተ ሙከራ ውስጥ በሥራ ላይ ሳሉ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ቆይታ ያደረጉ ፕሮፌሰር ጆናታን ሂኔይ የመጀመርያ ለመሆን እሽቅድምድሙ አስገራሚ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሆኖም ግን እጅግ የተሳካ ነገር ይዞ ለመምጣት ጥንቃቄና ጊዜን ይጠይቃል ብለዋል።
በዚያው በኬምብሪጅ ቤተ ሙከራ ሌላኛዋ ሳይንቲስት ዶ/ር ሬቤካ እንደሚሉት የእርሳቸው ቡድን በዋናነት እየሰራ ያለው በቫይረሱ የአጉሊ መነጽር ምስል ላይ የሚታየው እንደ ጨጎጊት ያለ፤ ወደ ላይ የተሰነቀረ አፍሮ ጸጉር የሚመስለው የቫይረሱን ክፍል ማጥፋት ነው።
ይህም አስፈላጊ የሆነው ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ሲገባ ከሰውነታችን ጋር እንዲጣበቅ የሚያደርገው ያ የቫይረሱ ክፍል ስለሆነ ነው። ከአካል ጋር እንደ ጨጎጊት ካልተጣበቀ ደግሞ ጉዳት የማድረስ ኃይሉ ይመነምናል ተብሏል።