ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስና በነዳጅ ዋጋ መውደቅ ስጋት የተደቀነባት ሳዑዲ አረቢያ
ከግብር ነጻ በመሆኗ በርካቶች ያወድሷት የነበረችው ሳኡዲ አረቢያ የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት በተጨማሪ እሴት ታክክ ላይ የሦስት እጥፍ ጭማሪ በማድረግ ከ 5 ወደ 15 በመቶ ከፍ እንዲል ወስናለች።
በተጨማሪም ለዜጎቿ ይሰጥ የነበረውን የኑሮ ድጎማም እንደሚቆም ተገልጿል።
የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ዓመት ከነበረበት ከግማሽ በታች የቀነሰ ሲሆን በዚህም ምክንያት የሳኡዲ መንግሥት ማግኘት ከነበረበት ትርፍ 22 በመቶ ከስሯል።
ዋነኛው የሳኡዲ ነዳጅ አምራች ድርጅት ሳኡዲ አራምኮ በያዝነው የፈረንጆች እሩብ ዓመት ብቻ ትርፉ 25 በመቶ እንደቀነሰበት አስታውቋል።
‘’የሳኡዲ ኢኮኖሚ እጅግ መጥፎ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው። ለማገገምና ወደነበረበት ለመመለስም ቢሆን ትንሽ የማይባል ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል’’ ብለዋል የባሕረ ሰላጤው አገራት ጉዳዮች ተንታኙ ማይክል ስቴፈንስ።
በሳኡዲ አረቢያ የኑሮ ዋጋ በጣም ከፍ ያለ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ ደግሞ በተቃራኒው እየወረደ ነው።
የኮሮናቫይረስ ስጋት
የሳኡዲ ኢኮኖሚ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ በብዛት ከእሲያ በመጡ ሠራተኞች ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን እነዚህ ሠራተኞች የሚኖሩበት አብዛኛው አካባቢ ለኮሮናቫይረስ ተጋለጠ ነው።
እጅግ ተጠጋግተውና ንጽሀናቸውን መጠበቅ በማይችሉበት ሁኔታ ነው የሚኖሩት። እነዚህ ሠራተኞች መስራት ካልቻሉ በተለይ በርካታ የግንባታ ሥራዎችን ለምታከናውነው ሳኡዲ ትልቅ ፈተና ይሆንባታል ተብሏል።
የኮሮናቫይረስ ስርጭት የሳኡዲን ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ትልልቅ አገራትን ኢኮኖሚም ማሽመድመዱን ቀጥሏል።
ሌላው ቢቀር ሳኡዲ አረቢያ ለእንደዚህ አይነት ጊዜዎች መጠባበቂያ የሚሆን 320 ቢሊየን ዶላር የፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ አላት።
ሳኡዲ አረቢያ በእጅጉ የምትመካበትና በአብዛኛው መንግሥት የሚቆጣጠረው ሳኡዲ አራምኮት ባለፈው ዓመት 1.7 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያወጣ ተገምቶላታል።
ይህ ደግሞ የአሜሪካዎቹ ግዙፍ የበይነ መረብ ተቋማት የሆኑት ጉግልና አማዞን የሚያወጡት ዋጋ አንድ ላይ ተደምሮ እንደማለት ነው።
ሳኡዲ የዚህን ድርጅት 1.5 በመቶ ድርሻ ለገቤያ አቅርባ 25 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ችላ ነበር።
ይህንን እና ሌሎች አገሪቱ በመጠባበቂያነት የያዘቻችውን ሀብቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሳኡዲ የኮሮናቫይረስ ሊያደርሰው ከሚችለው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በቀላሉ ልታገግም ትችላለች ይላሉ በሳኡዲ አረቢያ የቀድሞ የእንግሊዝ አምባሳደር።
የልዑሉ የወደፊት ህልም
ከነዳጅ ጥገኝነት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ እየፈጠርኩ ነው ለሚሉት ልዑል ቢን ሰልማን፤ በዚህ ሳምንት የተላለፈው የግብር ጭማሪና የኑሮ ድጎማ መቋረጥ በበርካታ የሳኡዲ ዜጎች ዘንድ ቅሬታን እንደሚፈጥር ሳይታለም የተፈታ ነው ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ እንኳን ውሳኔውን "በጣም የሚያም ግን በጣም አስፈላጊ" በማለት ነበር የገለጹት። ይህ ውሳኔ ሳኡዲ 26 ቢሊየን ዶላር እንድታድን ሊረዳት እንደሚችልም ይጠበቃል።
ባለፉት አራት ወራት ብቻ በሳኡዲ የ9 ቢሊየን ዶላር የበጀት ጉድለት አጋጥሟል።
ኮሮናቫይረስና የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል በመላው አገሪቱ የሚገኙ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን አሽመድምዷል። ይህ ደግሞ ልዑሉ ለአገራቸው በእጅጉ ይበጃል ያሉትና ራዕይ 2030 እያሉ የሚጠሩትን ፕሮግራም ከባድ ፈተና ውስጥ ይጥለዋል።
ይህ 2030 በመባል የሚጠራው ፕሮግራም ‘ኒዎም’ የምትባል የወደፊቱን ዓለም ልታንጸባርቅ የምትችል ዘመናዊ ከተማ በበረሀው መሀል መገንባት ዋናው እቅዱ ነው።
ነገር ግን ይቺን ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት በዋነኛነት ጥቅም ላይ የሚውለው ከነዳጅ የሚገኝ ገንዘብ መሆኑና ግንባታውን የሚሰሩት ከሌሎች አገራት የመጡ ዜጎች መሆናቸው ደግሞ ፈተናውን ከባድ ያደርገዋል።
ምንም እንኳን የግንባታ ሂደቱ እስካሁን አልተቋረጠም ቢባልም፤ በጊዜ ብዛት እክሎች ማጋጠማቸው አይቀርም።
ወጣም ወረደም የሳኡዲ አረቢያ ኢኮኖሚ ጉዳይ ለአገሬው ሰዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን መላው ዓለም በትኩረት ሊከታተለው የሚገባ ነው እየተባለ ነው።
በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ እድሜ ጠገብና ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች፤ የልዑል ሞሀመድ ቢል ሰልማን ፖሊሲዎች አገሪቱን ወደ አስፈሪ መንገድ እየወሰዳት እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን ማንም ሰው እስካሁን በግልጽ ወጥቶ ፖሊሲዎቹን የተቸ የለም።
በሌላ በኩል ልዑሉ በተቀረው ዓለም ስማቸው የገነና የለውጥ ሐዋርያ ተደርገው ነው የሚታዩት። በሳኡዲ የሚገኙ ወጣቶችም ቢሆን ለልዑላቸው ከፍተኛ ፍቅር አላቸው።
ምክንያቱም በልዑሉ በርካታ የፖሊሲ ለውጦች የተጠቀሙት ወጣቶቹ ስለሆኑ ነው።
ወጣት የሳኡዲ ዜጎች ልዑሉ በአገሪቱ የብሔረተኝነት ስሜት እንዲፈጠርና ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ብዙ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ያምናሉ።