ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ሳኡዲ ለዜጎቿ የምትሰጠውን ድጎማ በማቋረጥ ተጨማሪ ዕሴት ታክስን በሦስት እጥፍ ጨመረች
የሳኡዲ አረቢያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የደቀቀውን ኢኮኖሚዋን ለመደገፍ በተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ሦስት አጥፍ ጭማሪ ልታደርግ መሆኑን አስታወቀች።
የአገሪቱ መንግሥት ከዚህ በተጨማሪም ለዜጎቹ ይሰጠው የነበረውን የኑሮ መደጎሚያ ገንዘብ እንደሚያቋርጥም አስታውቋል።
የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሳኡዲ አረቢያ የገቢ መጠኗ በእጅጉ አሽቆልቁሏል።
ሳኡዲ አረቢያ ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር ኢኮኖሚው በነዳጅ ላይ ብቻ እንዳይንጠለጠል በሚል ተጨማሪ እሴት ታክስን ያስተዋወቀችው።
የሳኡዲ አረቢያ ዜና ተቋም እንደዘገበው ተጨማሪ እሴት ታክሱ ከፈረንጆቹ ሰኔ ወር ጀምሮ ከ5% ወደ 15% ከፍ ይላል።
"እነዚህ እርምጃዎች በጣም ከባድ ነገር ግን አሁና ካለው ሁኔታ አንጻር እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የአገሪቱን የገንዘብና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ነው እርምጃዎቹ የተወሰዱት" ብለዋል የገንዘብ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አል ጃዳን።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው አገሪቱ የምታወጣው ወጪ ከምታስገባው ገቢ በማነሱ ምክንያት መንግሥት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የ9 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለት ማጋጠሙን ተከትሎ ነው።
ይህም ሊሆን የቻለው በተጠቀሰው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ከነዳጅ የሚገኝ ትርፍ 22 በመቶ በመቀነሱ አገሪቱ ማግኘት የቻለችው 34 ቢሊዮን ዶላር ብቻ በመሆኑ ነው።
በነዚሁ ሦስት ወራትም የሳኡዲ አረቢያ ማዕከላዊ ባንክ እንዳስታወቀው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ገንዘብ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዝቅ ብሏል።
ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሳኡዲ አረቢያ ኢኮኖሚን ለማነቃቃትና አጠቃላይ የአገሪቱን ገጽታ ለመቀየር እየወሰዱት የነበረውን እርምጃ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ፈተና እንደሚሆንበት ይጠበቃል።