ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ ክትባት ለዓለም ሕዝብ በነጻ እንዲቀርብ ግፊት እየተደረገ ነው
ከ140 በላይ የዓለም መሪዎች፣ ባለሙያዎችና ታዋቂ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባትና መድኃኒት ለሁሉም የዓለም ሕዝብ በነጻ እንዲቀርብ ጥያቄ አቀረቡ።
ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ እነዚህ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች በጋራ ባወጡት ደብዳቤ ላይ ማንም ከማንም ሳይለይ ወረርሽኙን ለመመርመር፣ ለመከላከልና ለማከም የሚያስፈልጉ መገልገያዎች ሲገኝ ለሁሉም በነጻ እንዲቀርብ ነው ጥያቄ ያቀረቡት።
የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት እየተደረጉ ያሉት ምርምሮች ውጤታማ ወደ መሆን በተቃረቡበት በአሁኑ ወቅት ሐብታም አገራት ቀድመው በተናጠል ምርቱን በማግኘት ለዜጎቻቸው ለማቅረብ ሽሚያ መጀመራቸውን ተከትሎ ነው ታዋቂዎቹ ሰዎች ደብዳቤውን የጻፉት።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንት የሆኑትን ሲሪል ራማፎሳ፣ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሴኔጋሉና የጋና ፕሬዝዳንቶች፣ የአፍሪካ ሕብረት ዋና ጸሐፊን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ 140 ታዋቂ ፖለቲከኞችና ባለሙያዎች ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የጸረ ኤድስ ድርጅትና በኦክስፋም አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ ደብዳቤ ከኮሮናቫይረስ የሰዎችን ህይወት ለመታደግ የሚረዱ መከላከያዎችና መድኃኒቶችን ለመቆጣጠር የሚደረገው ፉክክር ከባድ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ደብዳቤው የዓለም መሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልገውን ክትባት፣ መድኃኒትና መመርመሪያን ማንም በባለቤትነት እንዳይዛቸውና በስፋት ተመርተው በአግባቡ ለሁሉም አገራት ዜጎች በነጻ እንዲቀርቡ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
"በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙ እንዲያበቃ ቢሊዮኖች ክትባትን ተስፋ አድርገው እየጠበቁ ነው" ያሉት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የአፍሪካ አገራት ክትባቱ ከባለቤትንት ነጻ ሆኖ በቶሎ እንዲቀርብ ይፈልጋሉ በማለት ማንም ቀዳሚ ማንም ከኋላ መሆን የለበትም ብለዋል።
በርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥረት እያደረጉና ተስፋ ሰጪ ውጤት እያገኙ ሲሆን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአውሮፓ ሕብርት አነሳሽነት በተካሄደው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ላይ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለምርምርና ለምርት ቀርቧል።
አሜሪካ ክትባቱን ሊያመርት ይችላል የተባለውን የፈረንሳይ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ሳኖፊ የኮቪድ-19 ክትባትን መስራት ከጀመረ ለአሜሪካ ገበያ ቀድሞ መስጠት አለበት በማለት ግፊት እያደረገች ነው።
ለዚህ ጥያቄዋ ተቀባይነትም "የአሜሪካ መንግሥት ምርምሩ ላይ ቀድሞ ኢንቨስት በማድረጉ በብዛት ቀድሞ የማዘዝ መብት አለው" የሚል ነው።
ይህንንም ተከትሎ አንድ ከፍተኛ የፈረንሳይ ባለስልጣን ጥያቄው "ተቀባይነት የለውም" ሱሉ ተቃውመውታል።