ኮሮናቫይረስ፡ "በኮሮና ተይዣለሁ ብዬ በመዋሸቴ ለእስር ተዳረግኩ"

ብራንደን

የፎቶው ባለመብት, Tyler County Sheriff's Office/ Getty

ሚካኤል ሌን ብራንደን ፌስቡክ ላይ ሊፅፈው ያሰበው ነገር አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል አልተጠራጠረም።

ነገር ግን ሥራዬን ያሳጣኛል፣ እከሰስበታለሁ፣ ለእስር እዳረጋለሁ የሚለውን ሃሳብ በጭራሽ ያልጠበቀው ነው።

በባለፈው ወር ላይ የኮሮናቫይረስ ቢከሰት እንዴት መከላከል ይቻላል? የሚሉ ክርክሮችን በፌስቡክ ገፁ ላይ እየተመለከተ ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለት። ደብሮትም ነበር፤ እናም ለምን 'እስቲ በኮሮናቫይረስ ተይዣለሁ' ብዬ ልፃፍና ሰው የሚያደርገውን ልይ አለ።

በኮሮናቫይረስ ተይዣለሁ ብሎም ፃፈ። በዚህም አላቆመም 'ያዳቆነ ሰይጣን . . ." እንደሚባለው ጭራሽ በቫይረሱ መያዙን ያረጋገጡት ዶክተሮች በአየር ላይ ወይም በትንፋሽ ቫይረሱ እንደሚተላለፍ ነግረውኛልም አለ።

በቫይረሱ የተያዘ ሰው ድንገት በአቅጣጫዎ ቢያስነጥስ ወይም ቢያስል በአቅራቢያው ካሉ ሊያዙ ይችላሉ ብቻ ሳይሆን ቫይረሱ በአየር ላይ ስለሚቆይ በማንኛውም አጋጣሚ ይይዝዎታል ብሎም ፃፈ። ይህ ሁሉ ግን ውሸት ነበር።

ብራንደን ዋናው ማስተላለፍ ፈለግኩ የሚለው ጉዳይ "ማንኛውንም የምታነቡትን ነገር በፍፁም ልቦናችሁ አትመኑ" የሚለውን መልዕከት ነው ይላል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሰዎች በድንጋጤና በሃዘን መልዕክቶችን ያጎርፉለት ጀመር። ጓደኞቹ ደኅንነቱን ሲጠይቁት ግን "ውሸት ነው" የሚል ምላሽ ሰጣቸው።

ብዙዎቹም ተበሳጩበት። ለምን እንዲህ እንዳደረገ ለጓደኞቹ ለማስረዳት እየታገለ ባለበት ወቅት በፌስቡኩ ላይ የፃፈው በኢንተርኔት ላይ ብቻ ሳይሆን በሚኖርባትም ቴክሳስ መነጋገሪያ ሆነ።

ወቅቱም የቤት ውስጥ መቀመጥ አስገዳጅ ባልሆነበት ወቅት ነበር። ገና ስለ ቫይረሱ በርካታ መረጃዎች በሚናፈሱበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የአካባቢው ሰው ሆስፒታሎችንና የጤና ተቋማትን በስልክ አጨናነቀ። በትንፋሽ የሚተላለፍ በሸታን እንዴት መቆጣጠር እንችላለን የሚልም የረብሻ ዜናዎች መሰማት ጀመሩ።

የእስር ትዛዝ

የታይፐር ግዛት ፖሊስ ጣቢያም ጉዳዩን መስማቱን ተከትሎም ፅሁፉን እንዲያስተካክል ጠየቁት። ብራንደንም ፖሊስ ባዘዘው መሰረት አስተካከለ።

ነገር ግን የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ እንዲሉ ጉዳቱን መቆጣጠር አልቻሉም። ፖሊሶች በፌስቡክ ገፃቸው የ23 ዓመቱ ብራንደን ላሰራጨው የሐሰት መረጃ በወንጀል እንደሚጠየቅ ይፋ አደረጉ።

በዚህ ብሔራዊ ቀውስ ወቅት ያሰራጨው መሰረት የሌለው መረጃ ረብሻን በመንዛቱ ሊጠየቅ ይገባዋልም አሉ፤ ብራንደንም እጁን ሰጠ።

"ዳኛው በነገታው እስኪመጡ ድረስ አንድ ቀን በእስር ቤት ማደር አለብህ አሉኝ። ፍራቻዬ ከአቅሜ በላይ ነበር" ይላል ብራንደን።

ከአንድ ቀን እስርም በኋላ በአንድ ሺህ ዶላር ዋስ ከእስር ወጣ፤ ፍርድ ቤትም ቀርቦ ክስ እንደሚጠብቀውም ተነገረው።

"የመጀመሪያ ዲግሪዬን የሰራሁት በኮሚዪኒኬሽን የትምህርት ዘርፍ ነው። ይህንንም ስፅፍ እንዴት ማንኛውም ሰው እውነትም ያልሆነ ነገር በመፃፍ ረብሻን ማነሳሳት እንደሚችል ለማሳየት ነበር" ያለው ብራንደን "ሰዎች የተፃፈውን ሁሉ ከማመናቸውም በፊት የራሳቸውን ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው ለማስረዳት ነው" ብሏል።

ሆኖም በዚህ ፅሁፉ ምክንያት ሥራውን አጥቷል፣ የጤና ኢንሹራንሱንም እንዲሁ፤ የድህረ ምረቃ ትምህርቱንም ገንዘብ ስላጠረው እንዲያዘገይ ተገዷል።

"ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቼም ሸክም ነው የሆንኩት" ብሏል።

ለም አቀፍ የወረርሽኝ ሰተኛ መረጃዎች

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እንደሚለው ከወረርሽኙ ጋር በተያዘ የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ባለስልጣናቱ ፈታኝ ሥራ እንደሆነባቸው ነው።

በህንድ፣ በሞሮኮ፣ በታይላንድ፣ በሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሲንጋፖር፣ ቦትስዋና፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ በመሳሰሉ አገራት ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሮበርት አላይ

የፎቶው ባለመብት, Robert Alai

ከነዚህም ውስጥ አንዱ የ41 ዓመቱ ሮበርት አላይ ነው። ሮበርት በኬንያዋ የወደብ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከስቷል የሚል መረጃን አስተላልፏል።

የኬንያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሕዝቡ ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠብና ይህንን በማያደርጉ ሰዎች ላይ እስር እንደሚጠብቃቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

እናም ይህንን ተከትሎም ሮበርት በአገሪቷ የመረጃ መረብ ሕግ መሰረት በወንጀል ተጠያቂ ሆኗል።

ሐሰተኛ መረጃን ለማሰራጨትም ሆነ ሰዎችን ለማሳሳት ሃሳቡ እንዳልሆነ የሚናገረው ሮበርት በተጨናነቁ እስር ቤቶች ውስጥ መታሰሩም ስጋት ጥሎበት ነበር።

"ሰዎች አይታሰሩ እያልኩ አይደለም ነገር ግን ፖሊሶች ምርመራቸውንና ሥራቸውን በደንብ ሊሰሩ ይገባል። መታሰር የሌለባቸው ንፁሃን ሰዎች ሊታሰሩ አይገባም" ብሏል።

ሮበርት በቅርቡ በዋስ ተለቋል።

ኮሮና