ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስ ምክንያት እየተፈለፈሉ ያሉት ሐሰተኛ መድኃኒቶች
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ተከትሎ በታዳጊ አገራት ሐሰተኛ መድኃኒቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት አስታውቋል።
እነዚህን መድኃኒቶች መውሰድ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉም እንደሚችሉ ድርጅቱ በተጨማሪ አስጠንቅቋል።
ገበያው ላይ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ሐሰተኛ መድኃኒቶች በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸበቸቡ መሆናቸውንም ቢቢሲ ባደረገው የምርምር መረዳት ችሏል።
ይህንንም ሁኔታ በማየት አንድ የጤና ባለሙያ "ከኮሮናቫይረስ ወረርሽን ጎን ለጎን ደረጃቸውን ያልጠበቁና ሐሰተኛ መድኃኒቶች ሊያጥለቀልቁን ይችላል" ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ የዓለምን ሕዝብ ሰቅዞ በያዘበት ሁኔታ ብዙዎች በመስጋት መሠረታዊ የሚባሉ መድኃኒቶችን እያከማቹ ነው። በዓለም ላይ መድኃኒቶችን በማምረትና በማቅረብ የአንበሳውን ድርሻ የያዙት ቻይናና ህንድ ድንበራቸውን መዝጋታቸው ከፍተኛ ክፍተትን ፈጥሯል።
ለመድኃኒቶች ያለው ከፍተኛ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምም ለሐሰተኛ መድኃኒት አቅራቢዎች በርን ከፍቶላቸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው ባለበት ሳምንት ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን አድኖ የሚይዘው ኢንተርፖል ድንበር ዘለል የመድኃኒት ወንጀልን ለመከላከል ባደረገው 'ኦፐሬሽን ፓንጊያ' የሚል ስያሜ በሰጠው ዘመቻ በዘጠና አገራት ውስጥ 121 ሰዎችን ከሐሰተኛ መድኃኒት ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር አውሏል።
ዓለም አቀፍ የመድኃኒት ሽያጭ ወንጀሎች በከፍኛ ደረጃ እየተፈፀሙ እንደሆነ አመልካች ነው የተባለለት ይህ እስር በአንድ በሳምንት ብቻ የተከናወነ ነው። በዚህም ዘመቻ 14 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አደገኛ የሚባሉ መድኃኒቶችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ፣ ከማሌዥያ እሰከ ሞዛምቢክ፣ የፖሊስ አባላት በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሐሰተኛ የፊት ጭምብሎችን፣ ሐሰተኛ መድኃኒቶችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። አብዛኞቹ መድኃኒቶችም ኮሮናቫይረስን ይፈውሳሉ እየተባሉ የሚሸጡ ናቸው።
"የዓለም የጤና ሁኔታ እንዲህ ቀውስ ውስጥ ባለበት ጊዜ፤ እንዲህ አይነት ሐሰተኛ መድኃኒቶችን መሸጥ ለሰው ልጅ ህይወት ግድለሽ መሆን ነው" በማለት የኢንተርፖል ዋና ፀሐፊ ጄኔራል ጀርጅን ስቶክ ተናግረዋል።
ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ጨምሮ፣ የተሳሳተ ወይም የጎደለ ንጥረ ነገር የያዙ በአጠቃላይ ሐሰተኛ መድኃኒቶች በመካከለኛና ታዳጊ አገራት 30 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
እነዚህ መድኃኒቶች ያድናሉ የተባለውን በሽታ መፈወስ አይደለም፤ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚናገሩት በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ የሐሰተኛ መድኃኒቶች ቁጥጥር ላይ የሚሰሩት ፔርኔት ቦርዶሊዮን "እነዚህ መድኃኒቶች በአብዛኛው መርዛማ የሆነ ንጥረ ነገርን ስለሚይዙ ነው" ብለዋል።
ዓለም አቀፋዊው የመድኃኒቶች ስርጭት
የዓለም የመድኃኒት ምርት ዘርፍ አንድ ትሪሊዮን የሚገመት ኢንዱስትሪ ነው። ስርጭቱንም በምናይበት ወቅት ከፍተኛ አምራቾች ከሚባሉት ቻይናና ህንድ ወደ አውሮፓ፣ ደቡብ አሜሪካም ሆነ እስያ ወዳሉ ትልልቅ ማከማቻ ወዳላቸው ማሸጊያ ቦታዎች ይላካል፤ ከዚያም ወደተለያዩ ሃገራት ስርጭት ይደረጋል።
ከመድኃኒት በላይ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ነገር እንደሌለ የሚጠቅሰው የዓለም የጤና ድርጅት አገራት ድንበራቸውን መዝጋታቸውን ተከትሎ ያለው የመድኃኒቶች ስርጭት ሥርዓት ብጥስጥሱ እየወጣ ነው።
በህንድ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መስራት የሚችሉበትን አቅም ቀንሰው ከ50 እስከ 60 በመቶ እያመረቱ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በተለይም ህንድ መሰረታዊ የሚባሉ መድኃኒቶችን 20 በመቶ ብቻ ለአፍሪካ መላኳ ከፍተኛ ተፅእኖን አስከትሏል።
በዛምቢያዋ መዲና ሉሳካ የሚገኝ ኤፍሬም ፊሪ የተባለ ፋርማሲስት የመድኃኒት እጥረት እያጋጠመ እንደሆነ ገልጿል።
"ክምችት ክፍላችን ውስጥ ያለው መድኃኒት በማለቅ ላይ ነው፤ በምን እንደምንተካው አናውቅም። ምንም ማድረግ አንችልም። በተለይም የፀረ ወባ መድኃኒቶችንና የህመም ማስታገሻን የመሳሰሉ መሰረታዊ መድኃኒቶች አቅርቦት የለም" ብሏል።
ፈተናው ለመድኃኒት ሻጮች ብቻ ሳይሆን ለመድኃኒት አቅራቢዎችና አምራቾችም ነው። በተለይም ለመድኃኒት ግብአቶች የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ዋጋ አልቀመስ ከማለቱ ጋር ተያይዞ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች እንደ ቀድሞው ማምረት የማይታሰብ ሆኗል።
በፓኪስታን የሚገኝ አንድ አምራች እንደተናገረው ከዚህ ቀደም ለወባ መድኃኒትነት የሚውለውን የሃይድሮክሎሮኪን ጥሬ እቃ ለመግዛት 100 ዶላር በኪሎ ይከፍል የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን 1150 ዶላር ደርሷል።
አገራት ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸውን ተከትሎ የምርት መቀነስ ችግር ብቻ ሳይሆን የተከሰተው፤ ብዙዎች በፍራቻ መድኃኒት በማከማቸታቸው እጥረት ተከስቷል።
ይህ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣምም ነው ከደረጃ በታች የሆኑ እንዲሁም በአጠቃላይ ለሐሰተኛ መድኃኒቶች ሽያጭ በር የከፈተው።
ሐሰተኛ መድኃኒቶች
በዓለም ላይ ያሉ ፋርማሲስቶችም ሆነ የመኃኒት አምራቾች ዓለም አቀፉ የወባ መድኃኒት ስርጭት አደጋ ላይ እንደወደቀ ይናገራሉ።
በተለይም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በዋይት ሐውስ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የወባ መድኃኒት የሆነው ክሎሮኪን ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት ነው ማለታቸውን ተከትሎ የተፈጠረው ፍላጎት ገበያው ማቅረብ ከሚችለው በላይ ጨምሯል።
ምንም እንኳን የዓለም ጤና ድርጅት የወባ መድኃኒቶች ኮሮናቫይረስን ለመፈወሳቸው ምንም አይነት ማስረጃ የለም ቢልም ትራምፕ አሁንም ቢሆን "ምን ታጣላችሁ? ዝም ብላችሁ መድኃኒቱን ውሰዱ" ብለዋል።
እንዲህ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በናረበት ሁኔታም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፍተኛ መጠን ያለው ሐሰተኛ ክሎሮኪን ቢቢሲ ለማግኘት ችሏል።
በኒጀርም እንዲሁ ሐተኛ የወባ መድኃኒት በዓለም የጤና ድርጅት መገኘት እንደተቻለ ተገልጿል።
አንድ ሺህ እንክብሎችን የሚይዘው ክሎሮኪን የሚሸጠው 40 ዶላር ቢሆንም በኮንጎ 250 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።
መድኃኒቱ ቤልጅየም ያለው ብራውን ኤንድ በርክ የተባለው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ያመረተው ነው እየተባለ ቢሸጥም፤ ኩባንያው በበኩሉ ይህንን መድኃኒት እንዳላመረተና ሐሰተኛ እንደሆነ አሳውቋል።
የኮሮና ቫይረስ እየተዛመተ ባለበት ባሁኑ ወቅት የሐሰተኛ መድኃኒቶች ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል የሚያስጠነቅቁት በሐሰተኛ መድኃኒቶች ላይ ተመራማሪ የሆኑት የኦስክፎርዱ ምሁር ፖል ኒውተን፤ አገራት ከፍተኛ ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባና መተባበርም እንደሚያስፈልግ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አገራት የመድኃኒቶቹን ጥራት በተመለከተ ክትትል እንዲያደርጉና የስርጭቱንም ሁኔታ እንዲቆጣጠሩ አሳስበዋል።