ኮሮናቫይረስ፡ ዶናልድ ትራምፕ በእግር-በፈረስ እየፈለጉት ያለው መድኃኒት

የህንዱ ሞዲና የአሜሪካው ትራምፕ በፍቅር ክንፍ ብለው ነበር ከወራት በፊት.

ትራምፕ ድንገት ከሰሞኑ ሞዲን አስጠነቀቁ። ህንድ ያከማቸችውን ሀይድሮክሲክሎሮኪን ካልሸጠችልን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉም ተናገሩ።

የህንዱ ሞዲ ትንሽ ጊዜ ስጡኝ ላስብበት ብለው ነበር ትናንት። ዛሬ ከጥቂት ሰዓታት በፊት የትራምፕን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ "መድኃኒቱን ልንልክላችሁ ወስነናል" ብለዋል።

ህንድ መድኃኒቱን በኮሮናቫይረስ ለተጎዱ አገሮች ለመስጠት ወስናለች ብለዋል ሞዲ። ይህ ንግግራቸው የትራምፕን የቅጣት ዛቻ ተከትሎ እንደሆነ ተዘግቧል።

የሕክምና አዋቂዎች ይህ የወባ መድኃኒት ኮሮናን ስለመፈወሱ የሚታወቅ ነገር የለም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካና ህንድን ያገናኘው መድኃኒት

ትራምፕ በተደጋጋሚ በሕዝብ ፊት ይህ መድኃኒት ማርሽ ቀያሪ ነው እያሉ ተናግረዋል። እሑድ ዕለት ደግሞ ወደ ናሬንድራ ሞዲ ደውለው ቶሎ ይሄን መድኃኒት ይላኩልኝ ብለዋል።

የህንዱ ሞዲ ደግሞ ጥቂት ቀደም ብሎ ማንኛውም የሕንድ ኩባንያ ይህን መድኃኒት ወደ ውጭ ቢልክ ወዮለት ብለው ነበር። ወዲያውኑ የትራምፕ ዛቻ ውሳኔያቸውን ሳያስቀይር አልቀረም።

የሚገርመው ይህ የሞዲ ውሳኔ በህንድ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ባለበት ሰዓት መደረጉ ነው።

ሆኖም ከአሜሪካ ጋር የሚነጻጸር አይደለም። አሜሪካ የተያዦች ቁጥር አራት መቶ ሺህ እየተጠጋ ነው፡። ሟቾች 10 ሺህ አልፈዋል።

ይህንን መድኃኒት ትራምፕ ለምን አጥብቀው ፈለጉት?

ሃይድሮክሲክሎሮኪን ልክ እንደ ክሎሮኪን ያለ መድኃኒት ነው። ብዙ ዘመን ያስቆጠረና ወባን በመፈወስ የሚታወቅ መድኃኒት ሲሆን በኮሮናቫይረስ ጉዳይ ስሙ እየገነነ መጥቷል።

ይህ መረጃ ኢትዮጵያ በመግባቱም በአዲስ አበባ በርካታ መድኃኒት ቤቶች በዚህ መድኃኒት ፈላጊዎች ተጨናንቀው እንደነበር የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ትራምፕ እንደሚሉት የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ይህንን መድኃኒት ለኮሮና መጠቀምን ፈቅዷል።

ትራምፕ ይህን ይበሉ እንጂ የመድኃኒት አስተዳደሩ እኔ አልወጣኝም ሲል አስተባብሏል።

በኋላ ትራምፕ ቃላቸውን ለውጠው እኔ የተናገርኩት የመድኃኒት አስተዳደር ይህን መድኃኒት እንደው ከርህራሄ በመነጨ ሐኪሞች ለኮሮናቫይረስ በሽተኞች ቢጠቀሙት አልቃወምም ስለማለቱ ነው ብለዋል።

"ከርህራሄ በመነጨ" ማለት አንድ ሐኪም ከመሞት ውጭ አማራጭ ለሌለው በሽተኛ ይህን መድኃኒት ቢሰጥ ክፋት የለውም ማለት ነው።

ሐኪሞች በዚህ አውድ ውስጥ ይህን መድኃኒት ማዘዝ ይፈቀድላቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ መድኃኒቱ በይፋ በምግብና መድኃኒት አስተዳደር የተመዘገበና የሚታወቅ ስለሆነ ነው። ምንም እንኳ የሚታወቀው በኮሮናቫይረስ ፈዋሽነቱ ባይሆንም።

በህንድ ይህ መድኃኒት ውድ ያልሆነና ያለ ሐኪም ማዘዣ ሁሉ በየመድኃኒት ቤቱ የሚገኝ ነው።

ሆኖም ኮሮናን ይፈውሳል የሚለው ወሬ መናፈሱን ተከትሎ መድኃኒቱ ላይ ህንድ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀምራለች።

የሆነው ሆኖ ሐኪም ብዙም የማይሰሙት ትራምፕ እንደ ቅጠል እየረገፈ ላለው ሕዝባቸው "እጅግ አስፈላጊው መድኃኒት ይኸው ነው" ብለው የደመደሙ ይመስላል።